በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ጆሀንስበርግ መጤ በተባሉ እና የደቡብ አፍሪካ ዜግነት በሌላቸው የውጭ አገራት ዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት የደቡብ አፍካው ፕሬዘዳንት ሲሬ ራማፎዛ በይፋ አውግዘዋል። ፕሬዘዳንቱ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከፀጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሆነና ዕልባት ላይ እንደሚደረስም ጨምረው አስታውቀዋል።
‹‹ሥራችንን ወሰዳችሁብን›› በሚል ደቡብ አፍሪካዊያን በውጭ አገር ዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ይህንም ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረትና አባል አገራት ድርጊቱን በፅኑ ኮንነዋል። በጥቃቱ እስካሁን የአምስት ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ኢምባሲዎችም ዜጎቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ዕርዳታ የሚያገኙበትንም መንገድ እና የአስቸኳይ ጊዜ ስልክ ቁጥሮችን ለዜጎቻቸው አስታውቀዋል።



