“2012 ኢትዮጵያ ወዴት?”

0
1102

ኢትዮጵያ ከ2008 ጀምሮ የሕዝባዊ አመጽ በርትቶባት “ነባሩን” ኢሕአዴግ “በአዲሱ” ኢሕአዴግ እንዲተካ በማስገደድ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው አስተዳደር ሥልጣነ መንበሩን ተረክቧል። የአመራር ለውጡን ተከትሎ ለብዙዎች ተስፋ የፈነጠቀ ሁኔታ ተፈጥሯል፤ የኋላ ኋላም ተስፋን ያጠየሙ ብሎም ያጨለሙ ነገሮችም እንዲሁ። 2011 ብዙ ወሳኝ አገራዊ ኩነቶች የተፈጠሩበት፤ ሥጋትም ተስፋም የተፈራረቁበት እንደነበር መታዘብ ይቻላል። የአዲስ ማለዳ ባልደረቦች የሃይማኖት አባቶችን፣ ፖለቲከኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ ጋዜጠኞችን እንዲሁም ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍል አባላትን “ኢትዮጵያ 2011 እንዴት አሳለፈች? አዲሱ 2012ስ ወዴት ይወስዳታል?” ለሚሉ ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ አሰባስባለች።

ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የኢ/ኦ/ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የሰላም አባት የሆነው እግዚአብሔር እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሳችሁ። 2011 ዓመት አገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ተስፋ ሰጪ የሚመስሉ ምልክቶች የታዩባት ቢሆንም፣ ዘርን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች በርካታ ልጆቿን በሞት ከማጣቷም ባለፈ፣ ብዙዎች ቀዬያቸውን ጥለው ተፈናቅለውባታል። ሕፃናት መጠለያ አጥተው ተንከራተዋል፣ የሚበሉት አጥተው ምጽዋት ተለምኖላቸዋል። ትምህርታቸውን አቋርጠው ከእኩዮቻቸው የበታች ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችንም ለጥቃት ሰለባ ሆና በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል። የእምነቱ ተከታዮቿም ተገድለዋል፤ ተሰደዋል። ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ አስተዋጽዖ የነበራትና ያላት እናት ቤተክርስቲያን የዘረኞች ጥቃት [ሰለባ] ከመሆኗም ባለፈ ሊበትኗትና ሊከፋፍሏት የተነሱ ወገኖችም አድብተውባታል።
በ2012 መንግሥት በተለይ ዘርን መሰረት ተደርገው በሚደረጉ ጥቃቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይኖርበታል። እነዚህ ጥቃቶች ቶሎ እልባት ካልተበጀላቸው አገርንና ሕዝብን ከመበታተን ወደ ኋላ የሚሉ አይደሉም። የሰው ልጅ ፀር የሆነውን ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት በእንጭጩ መቅረፍ ካልተቻለ በኋላ ላይ መመለሱ ከባድ ስለሚሆን፣ ሁሉም በማንነቱ ኮርቶና በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ ሰላም የሆነች ታላቅ አገር ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት መነሳት ይኖርበታል። ኢትዮጵያዊነት ከሌለ ኢትዮጵያዊም አይኖርም።
አዲሱ ዓመት የሰላም ከጥላቻ፣ ከመለያየትና እርስ በርስ ከመጠፋፋት የጸዳ፣ የመፈቃቀር፣ የመደጋገፍና እንዲሆን እግዚአብሔር ይርዳን። አንዱ አንዱን የሚደግፍበት፣ አንዱ የአንዱ ወንድም መሆኑን የሚረዳበት፣ የተማረው ሕዝብ እርስ በርሱ የሚከባበርበትና ለአገሩ የሚያስብበት፣ ሃይማኖቶች ለአገራቸው የሚጸልዩበት፣ ተከታዮቻቸውን በትጋት የሚያስተምሩበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ።

_____________________________

ካርዲናል ብርሃኢየሱስ ሱራፌል ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ/ካ/ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት
የጊዜና የዘመን ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አባታችን እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን እገልጽላችኋለሁ። ከሁሉ በፊትም እግዚአብሔር አምላካችን መጠጊያ ሆኖን በሕይወት እንኖርበት ዘንድ ዕድል ስለተሰጠን በአዲስ ዓመት አምላካችንን እናመሰግነዋለን።
ባሳለፍነው ዓመት ብዙ መልካምና እና ያዘንባቸው ተግባራት አሳልፈናል ቢሆንም በአዲሱ ዓመት የሚስተካከሉትን በማስተካከል በአገራችንና በሕዝቦቻችን ላይ ለምን ሆኑ በማለት ማኅበረሰቦቻችንን በሰፊው በማወያየት ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን በብልኀት ማጥራትና ማስተካከል ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት ይገባናል።
አዲሱ ዓመት እግዚአብሔር ከተስፋ መቁረጥ ከችግርና ከጥላቻ፣ ከመለያየትና እርስ በርስ መጠፋፋት ፋንታ የመረጋጋት፣ የማስተዋል፣ የመደጋገፍና በአንድ አምላክ የአንድ አገር ልጆች መሆናችንን አውቀን ከጥፋት መንገድ በመውጣት ሰብኣዊ ቀውስን በራሳችን ከማምጣት ይልቅ በአንድነት በኅብረት እና አገራችን ለእኛ ሆና በሰላምና በፍቅር የምንኖርባትና የምንሠራበት እንድትሆን እግዚአብሔር ውስጣችንን እንዲያድስልንና እውነተኛ የፈጣሪ ልጆችና ወዳጆች መሆናችንን የሚያስመሰክር ሥራና ተግባር እንድንፈጽም አደራ ማለት እወዳለሁ።

_____________________________

መራራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) የኦፌኮ ሊቀመንበር

እንደሚታወቀው 2011 ተስፋ ሰጪና ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ጎን ለጎን የተስተናገዱበት ዓመት ነው። ምርጫ ቦርድን፣ የፖለቲካ ማስፋትን፣ አንዳንድ ሕጎችን የመለወጥ ተስፋ ያዘሉ እርምጃዎች ሲወሰዱ ነበር። ነገር ግን ከተስፋው የበለጠ አገሪቷ ወዴት ታመራለች የሚለውን መመለስና መተንበይ አስቸጋሪ ሊያደርጉ በሚችሉበት ሁኔታ የሔዱ ነገሮች አሉ። በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ የተፈጸሙት ነገሮች ተስፋ ሊያጨልሙ የሚችሉ አነጋጋሪ የሆኑ ክስተቶችን አስተናግደዋል። ስለዚህ ገዢው ፓርቲ አገሪቷንና ሕዝቦቿን ወዴት እየወሰዳት ነው የሚለውን በርግጠኝነት ለማወቅ ባልቻልንበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። በአጠቃላይ አገሪቷ አስቸጋሪ መስቀልኛ መንገድ ላይ ናት። ተስፋም አለ፤ ተስፋ አስቆራጭ ብዙ ነገሮችም አሉ። እንዲያውም ሥጋቶቹ እየሰፉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። እኔ ብሔራዊ መግባባት ላይ እንደርሳለን በሚል ተስፋ አድርጌ ነበር፤ አልቻልንም። ገዢው ፓርቲ ብሔራዊ መግባባት በሚፈጥር ደረጃ መምራት የቻለ አይመስልም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ዓመትን በተለየ ሁኔታ ይጠብቀዋል። እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን። አዲሱ ዓመት የሰላምና የብልጽግን ይሁንልን።
በአዲሱ ዓመት ኹለት ነገሮችን እጠብቃለሁ። አንደኛ በፖለቲካ ኀይሎች መካከል ብሔራዊ መግባባት የምንለውን መውሰድ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ መጪው ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ማድረግ ያስቸግራል። ስለዚህ በቅድሚያ በተቻለ ፍጥነት የፖለቲካ ኀይሎች አቅጣጫ ይዘው በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ፣ ሕዝቡንም ለማንቀሳቀስ ሁላችንም በቁርጠኝነት መነሳት ይጠበቅብናል።
በዓመቱ መጨረሻ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳካ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እናካሂዳለን የሚል ተስፋ ይዣለሁ።
ኹለት ነገሮች ማሳካት የኢትዮጵያን ታሪክ ለመቀየርም፤ የተሻለ አቅጣጫ ለመያዝም ለዘመናት ሕዝቡ ሲጠብቅ የነበረው ሰላምና መረጋጋት ብቻ ሳይሆን የተሻለ አስተዳደር፣ የተሻለ ልማትና ብልጽግናን ተስፋ አድርጎ እንዲሔድ ያግዘዋል። የኢሕአዴግ የመጨረሻ ውለታ የምለው ይሔንን እንዲያደርግ ነው።

_____________________________

ዳንኤል ብርሃነ የመብት ተሟጋች

2011 ከ2010 የተንከባለሉ ነገሮች የመጡበት ዓመት ነው። ይሔ ለውጥ የሚባለው ነገር ምንም እንኳን ነዳጁን የጨረሰ ቢሆንም ዓመቱ ሲጀምር መስከረም ላይ በተወሰነ ደረጃ ሙቀት ላይ ነበር። ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲን እናስቀጥላለን፤ መሥመራችንም ልማታዊ መንግሥት ነው ቢልም በውዝግብ እየዳከሩ ይገኛሉ።
ብአዴንና ሕወሓት ዓመቱ ሲጀመርም ጥሩ መንፈስ ላይ አልነበሩም፤ በመሐልም ያንን መግለጫም አውጥተዋል። በብአዴንና ኦሕዴድ መካከል ዓመቱ ሲጀመር ከነበረው ግንኙነት እየላላ ሔዶ አሁን በግልጽ የሚዘላለፉበት መግለጫ እስከማውጣት ደርሰዋል። ኢሕአዴግ ዓመቱን በጉባዔ ጀምሮ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ግን ጉባዔ ማካሔድ ይቻል አይቻል ግራ የሚያጋባ ሆኖ ነው ያለቀው።
በአዲሱ ዓመት የሥልጣን ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም [የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች] የሚቀጥለውን ምርጫ ለመሻገር አብረው ይሠራሉ፤ ነገር ግን የዛኑ ያክልም የመበተን ዕድል ሊኖር ይችላል። ኢሕአዴግ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለው።
ኤርትራን በተመለከተ ዓመቱን በመተቃቀፍ ነው የተጀመረው፤ ዓመቱ ሲያልቅ ምን ውስጥ እንደተገባ አይታወቅም። ኢሳያስ እስካልቸገረው ድረስ በአዲሱ ዓመት ባለበት ሁኔታ ይቀጥላል። በአዲሱ ዓመት ኢሳያስ ሥልጣን ላይ ካለ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀውስ እስኪፈጠር ይጠብቃል።
አሁንም እጁን ይከታል። በከፍተኛ ጉልበት የተጀመረው የሰላም ግንኙነት እየተቀዛቀዘ ሔዶ አሁን ዜሮ ማርሽ [ላይ] ነው ያለው።
ተቃዋሚዎችን በተመለከተ ዓመቱ ሲጀመር ተደምሪያለሁ የሚሉ አለበለዚያም ድምጻቸውን ያጠፉበት ሁኔታ ነበር። ሁሉም ሕወሓትን ለማውገዝ ዝግጁ ነበሩ። አሁን በዓመቱ መጨረሻ ላይ ግን ዐቢይ ከኢዜማ እና ከሌሎች ጋር ተመሳጥሮ ፓርቲዎቹን ለማጥፋት ይፈልጋል በሚል በዓመቱ መጨረሻ ዐቢይ የኅልውና ሥጋት ሆኖባቸዋል፤ በሚቀጥለው ዓመትም ግንኙነታቸው እንደተበላሸ ይቀጥላል። ምክንያቱም ዐቢይ ጥሩ ኢሕአዴግ ስለሆነ ጥቂት ፓርቲዎችን ነው መቆጣጠር የሚፈልገው።
በአጠቃላይ 2012 ከ2011 በምን መልኩ ይለያል የሚለውን ግራ ያጋባኛል። መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ነገሮች የማይቀለበሱበት ሁኔታ ላይ ሆነው ተሻሽለዋልም፤ ተበላሽተዋልም። የሚቀጥለው ዓመት ላይ ጠጋግነው እና ሁሉም ድርሻውን ይዞ ነው መቀጠል የሚፈልጉት።
2011 አገሪቱ ካተረፈችው የከሰረችው ይበልጣል። በመሆኑም 2011 ለአገሪቷ ብዙ የቤት ሥራዎችና አዳዲስ ጣጣዎችን አስረክቦ የሚሔድ ዓመት ነው። 2012 ፈታኝ ነው የሚሆነው፤ ቁልፍ ውሳኔዎች ለመወሰን እና ለዚያ የሚመጥነውን ለውጥ ለማድረግ ፍላጎት ያለው ባለድርሻ በክልልም በፌደራልም አለ ብዬ አላምንም። ሁሉም ጥጉን ይዞ እየቆመረ 2012ን እንደዚሁ እናሳልፋለን።

_____________________________

ስዩም ተሾመ የመብት ተሟጋች
ኢትዮጵያ ውስጥ አፋኝ፣ ጨቋኝና ዘረኛ የሆነው ስርዓት ተወግዶ፤ የሕወሓት የበላይነት አክትሞ ቢያንስ ሐሳባችንን በነፃነት መግለጽ የቻልንበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሥር ነቀል የሆነ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ወይም ላለማምጣት፤ ለመለወጥ ወይም ላለመለወጥ የምንወስንበት ወሳኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመናል።
በዚህ መስቀለኛ መንገድ ላይ ልንወስን የምንችልበት አንድ ዓመት አባክነናል። ሥር ነቀል ለውጥ የሚባሉ ሥራዎችን ለመሥራት ቁርጠኝነቱ የለም፤ ዳተኝነት በስፋት ይስተዋላል። እኔ የማምነው ኢትዮጵያ ከተመሠረተች ጀምሮ ሥር ነቀል ለውጥ መጥቶ አያውቅም፤ የሚፈለገው ለውጥ አልመጣም። ጨቋኝ ስርዓቶች ናቸው ሲፈራረቁብን የከረሙት።
ሥር ነቀል ለውጥ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥር ከሰደደ ድኅነት ማላቀቅ ነው። ከአምባነንና ጨቋኝ ስርዓት ማላቀቅ ነው። ለዚያ ደግሞ ዘላቂ፣ ተከታታይ እና ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ነው። ለውጥ ማለት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ማዕቀፍ ማቆም ነው።
ካለፉት 100 ዓመታት ውስጥ የመጣ ለውጥ ካለ ኢትዮጵያ እንደ አገር መመሥረቷ ብቻ ነው። ከዛ በኋላ የተሠሩ ሥራዎች ድኅነትና አምባገነንነትን ነው የወለዱት። ይህንን ለመቀየር የምንችልበት መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን። አንድ ዓመት ግን አባክነናል። ቀጣዩ አንድ ዓመት አርቀን የምናይበት እና የምናስተውልበት ይህንን ሥር ነቀል ለውጥ ለመጀመር አንድ ተጨባጭ የሆነ እርምጃ የምንወስድበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

_____________________________

እስክንድር ነጋ የኢትዮጲስ ጋዜጣ ሥራ አስኪያጅ

2011 ስንጀምር እኔ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁበት ጊዜ ነበር። ለኹለት ወር እዛ ቆይቼ ኢትዮጲስን ለመጀመር የምንቀሳቀስበት ጊዜ ነበር። አስታውሳለሁ ያኔ ተስፋ ነበር። ያ ተስፋ አምባገነናዊ ስርዓት ላይ በሩን ዘግተን ያንን ምዕራፍ አጠናቀን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንሸጋገራለን የሚል ብሩህ ተስፋ ነበር። ውስጣችን ትንሽ ጥርጣሬ ቢኖርም ትልቁ ስሜት ግን የሚገለጸው በተስፋ ነበር።
365ቱን ቀናት ወጣ ገባ እያልን፤ እየወደቅን እየተነሳን መቋጫው ላይ ያለንበትን ሁኔታ ስንገመግም ዋነኛው መገለጫ በሐሰት ላይ የተመሰረቱ የሽብር ክሶች ናቸው። በሐሰት ስል መንግሥት እያወቀ ሕዝብን ለማስፈራራት ብሎ የሽብር ክሱን እንደማስፈራሪያ መሣሪያ እየተጠቀመበት እንገኛለን። እናም ያ የነበረው ተስፋ እየጨለመ ለመሔዱ ትልቅ ማሳያ ነው። ስለዚህ ከብርሃን ወደ ጨለማ ተጉዘናል በሚለው ልገልጸው እችላለሁ።
ይህን ስል ግን ፊታችን ያለው 2012ን በሚመለከት ደግሞ ምንም እንኳን ነገሮች ሊበላሹ አፋፍ ላይ ቢደርሱም ወደ ኋላ ለመመለስ አልረፈደም።
መንግሥት በዚህ ትንሽ ወደ ፊት የሚቀጥል ከሆነ መመለስ የማይችልበት
ቦታ ላይ ይደርሳል፤ ሕወሓት እንደዛ ነው የሆነው። አንድ ጊዜ ገባበትና ወደ ኋላ መመለስ አልቻለም፤ እስከውድቀቱ ድረስ በዛው መንገድ ላይ ቆይቷል።
አሁን ደግሞ ሥልጣን ላይ ያለው ኀይል የጥፋት መንገድን ገና አንድ ብሎ ጀምሯል። አልረፈደም፤ መመለስ ይችላል። ተስፋ የማደርገው ሳይረፍድ፣ ሳይዘፈቅበት፣ ሊመለስ በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሳይገባ ወደ ኋላ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
የዛሬ ዓመት የነበረው ተስፋ ሙሉ ለሙሉ አልተዳፈንም፤ ጭላንጭሉ አለ። ከጥፋቱ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህ መንገድ ከቀጠለ ግን በአገራችን ሊከሰት የሚችለው ችግር በጣም ከፍተኛ ስለሆነ፤ ለአንድ መንግሥት ወይም ለአንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ህልውና የሚያሳስበን ስለሆነ፤ ተስፋ አለማድረግ አልችልም፤ የግድ ተስፋ ማድረግ አለብኝ። ምክንያቱም የአገራችንን ቀጣይነት ከልቤ እፈልጋለሁ፤ ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ አልፈልግ።

_____________________________

ትንሣኤ ታደሰ የ5ኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ

2011 በኢትዮጵያ ካለፉት ዓመታት አዲስ ይዟቸው የመጣቸው እጅግ አስከፊ እና ከባድ ሁኔታዎች ነበሩ። በዋነኝነት የዘር ፖለቲካ የገነነበት ዓመት ነበር፤ እንደማሳያም በደብረ ብርሃን፣ በአምቦ፣ በደብረ ማርቆስ እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተው ችግር ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት እስከማጥፋት ደረጃ ደርሷል። የሰው አካል መጉደል እና የንብረት መውደምም ወጤቶቹ ነበሩ። በተጨማሪም የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ለብዙ ሰዎች ኅልፈት እና መፈናቀል ምክንያት ነበር፤ እነዚህ ችግሮች በቀጣይነት የሚቀጥሉ ከሆነ ወደ አስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ ያስገባናል። ይህንንም ለመቅረፍ በተለያዩ የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች መሪነት የሚደረጉት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ጉባኤዎች መቀጥል አለባቸው።
አዲሱ ዓመት 2012 ካለንበት ጥላቻ እና የመከፋፈል ስሜት ወጥተን በአዲስ መንፈስ የኔ የምንለውን ነገር ትተን በጋራ ለአገራችን ዕድገት እና ብልፅግና የምንሠራበት የሕዝቡ ጥያቄ መልስ የሚያገኝበት ተስፋ የተሞላበት ዓመት ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

_____________________________

ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ የኅብረት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር እና የኅብረት ኢንሹራንስ የፋይናንስ አማካሪ

እኔ ብዙ ነገር ባይታየኝም የምመኘውን ለመናገር ሁሌም መጀመሪያ የት ነበርን የሚለውን ማሰብ መልካም ይመስለኛል። የአሁኑ ኢሕአዴግ ይህንን አቋም ከመያዙ በፊት አገራችን ኹለት ጊዜ አስቸኳይ አዋጅ ውስጥ የገባችበት እና በአብዛኛው የአገራችን ክፍል ያሉ እና ከችግር ያወጡናል ያልናቸው መሪዎቻችን ከጥንት ጀምሮ የመጣውን የእኔ አውቅላችኋለሁን ሥሜት የጫኑበት እንዲሁም ተዳክመው ያዳከሙን ወቅት ነበር።
በተለይም ምርጫ 1997 ከተጨናገፈ በኋላ ወጣቱ በድንጋይ እና በጎማ መንገድ እየዘጋ ተቃውሞውን ሲገልፅ በመንግሥት ድጎማ የወጣት ማዕከል በመገንባት እና ጉቦ በሚሰል ሁኔታ የወጣቶች የፖለቲካ አደረጃጀት እንዲፈጠር በማድረግ ጉዳዩን ቢያድበሰብስም ዳግም ገንፍሎ ወጥቷል።
በኢኮኖሚውም ቢሆን መንግሥት ብቻውን አድራጊ ፈጣሪ የነበረበት እና የግሉ ዘርፍ ያለው ተሳትፎ የተገደበበት ነበር። የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ልቅ ይሁን ብዬ አላውቅም ነገር ግን መንግሥት ሲደርግ የነበረው ግልፅ አፈና ነው። ብድር የሚፈልግ አንድ ባለሀብት መንግሥት በሚፈልገው ዘርፍ የሚሠማራ መሆን አለበት ብለው የማይፈልገው እና የማያውቀው ዘርፍ ውስጥ ይዘፍቁት ነበር።
ኢሕአዴግም በታሪኩ የመጀመሪያውን ዴሞክራሲያዊ ስብሰባ አድርጎ ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) በ108 ድምፅ መምረጡ እስከዛሬ መሪዎቹን በሙሉ ድምፅ ሲመርጥበት ከነበረው አካሔድም የተለየ ነበር። ነገር ግን ዐቢይ የግንባሩ ውጤት እንጂ ከሰማይ የወረደ ሰው አድርጎ ማሰቡም ትክክል አይመስለኝም።
አሁን የተነደፈው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግን እስከዛሬ ካየሁት ሁሉ ተስፋ የሚሰጥ ነው። አንዳንዴ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመፍጠናቸው እና የሚገቡት ቃልም ከመብዛቱ አንጻር ይህ ሰው ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ነው ወይስ የሚሉትን ነገር ያምኑበታል ብዬ እጠይቃለሁ። ይህንንም ይዤ በቅርብ የሚያውቋቸውን ሰዎች አነጋገሬ የሰጡኝ መልስ ግን እኛንም ያስደነግጡናል የሚል ነበር።
ታዲያ ይሔ ሁሉ መሻሻል ባለበት ስንት ዋጋ የከፈልንበት እና ከትምህርት ቤት ጀምሮ የታገልነት የብሔር ጉዳይ መልኩን ቀይሮ እንዲህ የእግር እሳት መሆኑ ያሳስበኛል። አሁን ያለው አካሔድ እንደሩዋንዳ ሳያደረገንም በጊዜ መታረም አለበት። ማንም ሰው ሴት ወይም ወንድ፣ የዚህ ብሔር አባል ወይ የዛ፣ የተማረ ወይ ያልተማረ ከመሆኑ በፊት ሰው ነው።
አሁን ያለው ችግር ሁላችንም የተሳተፍንበት እንጂ ፖለቲከኞች ብቻቸውን የፈጠሩት አይደለም። በተለይ የእኛ ልኂቆች ሌላውን ከመኮነን ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ዛሬ ለተፈጠረው ሁኔታ የራሳቸውን ድርሻ መውሰድ አለባቸው። ለሦስት ሺሕ ዘመን አብረው የኖሩ ሕዝቦች አጠፋለሁ በሚል ሲዛዛቱ መስማት መቼም አሳቃቂ ነው።
እኔ በዚህ ዕድሜዬ ሕዝብ ተጣልቶ አይቼ አላውቅም የሚጣላው መሪ እና ልኂቁ ነው። ስለዚህ ይህንን ድርጊት ችላ ማለቱ ቀርቶ የኢትዮጵያ ሕዝብን ወደ ባሰ ስቃይ ሳያስገባ መታደግ አለባቸው።
እንደ ኢንሹራንስ ሰውነቴ መልካም መልካሙን መመልከት ለምዶብኝ ይሆናል መጪው ጊዜ ይሔ ሁሉ ችግር ተቀርፎ በተፈጥሮ ሀብቷ አና በሕዝቦቿ ብዙዎች የሚቀኑባት አገራችን ኢትዮጵያ በልጽጋ እንመለከታለን ብዬ አምናለሁ።

_____________________________

ጃዋር መሐመድ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክትር
ያለፈውን ዓመት የምመለከተው የሽግግር ዓመት ከመሆኑ አንጻር የባከነ ዓመት ብዬ ነው። በጊዜ መሠራት የነበረባቸው ነገሮች ያልተሰሩበት እና በተፈጠሩት ስህትቶችም ለሽግግሩ እንቅፋት የተፈጠረበት ዓመት ነበር ማለት እችላለሁ። ነገር ግን ሊደርስ ይችላል ብዬ ከገምትኩት አደጋ ያነሱ ክስተቶች የተፈጠሩበት እና በአማራ ክልል እንደነበረው ዓይነት ደግሞ ቀላል የማይባሉ ጉዳቶችንም ያስተናገድንበት ነው።
በሽግግሩ ሒደት ላይ ሊኂቃኑ እና መንግሥት ቀድመው በመወያየት እና አንድ የጋራ ፍኖተ ካርታ ባለመያዛቸው ዋጋ አስከፍሏል ብዬ አምናለሁ። ትንንሽ ችግሮችን በማጋነን እና በመካረር የሚፈጠሩ የፖለቲካ ችግሮች ወደ ኢኮኖሚ ችግርነት እስከሚያድጉ ድረስ የተመለከትንበት ዓመት ነበር።
መጪው ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወይ የትንሳኤ ወይ ደግሞ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የምንገባበት ይሆናል። ለዚህም የመጀመሪያው የሕዝብና የቤት ቆጠራ ጉዳይ ነው። ቆጠራው በተያዘለት ጊዜ መካሔድ የሚኖርበት ሲሆን ታዓማኒነት፣ ግልፅነት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች የሚተገበሩበት መሆን አለበት።
በተጨማሪም ምርጫውም ቢሆን ተወዳዳሪዎች ለመሸናነፍ ብቻ ሳይሆን አገር ለማሻገር ሲሉ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ማከናወን አለባቸው። ባሳለፍነው ዓመትም ይህንን ምርጫ በተመለከተ ብዙ ቅድመ ዝግጅቶች መከወን የነበረባቸው ነገሮች እንዲሁ የታለፉ ሲሆን በመጪው ዓመትም ትኩረት ተሰጥቶበት ውይይቶች ተደርገው መግባባት ላይ መደረስ አለበት። ይህም በፌደራል ብቻ ሳይሆን በክልል መንግሥታትም በኩል በትኩረት መፈፀም ያለበት ሲሆን ሕዝቡም የራሱን ጫና ማሳደር ይኖርበታል።
መልካም ነገር ነው ብዬ የማስበው ያሳለፍነው ዓመት ለመንግሥት የሚሰጠው ከምክንያታዊነት ርቆ በስሜታዊነት ውስጥ የነበረው ድጋፍ የቀዘቀዘበት እና ወደ ማመዛዘን የተገባበት ጊዜ መሆኑ መጪውን ዓመት ረጋ ብለን የምንመለከትበት ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

_____________________________

ፀዳለ ለማ የአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ

2011 በተለይ ለመደበኛ ሚድያው እጅግ አስቸጋሪ ዓመት ነበር፤ በተወሰነ ደረጃም እንደዚሁ ይቀጥላል የሚል ግምት አለኝ። ካለው የፖለቲካ ለውጥ ጋር ተያይዞ መንግሥት ለውጥ አደርግባቸዋለሁ ብሎ ከተነሳባቸው መስኮች አንዱ ሚድያው ነው። የሚድያ ምኅዳር ነጻ መደረጉ ምንድን ነው የፈጠረው ለሚለው ለብዙ ዓመታት ጫና ሥር ለነበረ ዘርፍ በድንገት ነጻ ሚድያ ለማቋቋም መነሳቱ፤ ከነጻነቱ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ክስተቶችን ለመቋቋም አቅም አንሶታል።
በተለይ ማኅበራዊ ሚድያው የመደበኛውን ሚዲያ ሚና ወስዶና የራሱን ባሕሪ ጨምሮበት መደበኛ ሚድያውን ሽባ አድርጎታል።
የማኅበራዊ ሚዲያው ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ ሚዲያ ባልተዘጋጀበት ጊዜ መንግሥት የሚድያውን ምኅዳር ነጻ ሲያደርገው፤ ሕዝበኛ የሆነው የፖለቲካ ባሕል ተፈጠረ፤ ይህም መደበኛ ሚድያው ተጠንቅቆ፣ እውነታ ላይ መሠረት አድርጎ ለመሥራት በሚል መጀመሪያ በነበረው ፍጥነት ወይም አካሔድ ነው የቀጠለው።
ማኅበራዊ እንዲሁም ሌሎች ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉት ሚድያዎች መረጃን ሳያረጋግጡ፣ ለሕግና ለሥነ ምግባር ሳይገዙ መረጃ ይለቃሉ። ይህም መደበኛውን ሚድያ ዋጋ ቢስ አደረገው።
የእነዚህ ተያያዥነት ከፖለቲካው ሕዝበኝነት (‘ፖፕሊስት’) እንቅስቃሴ ጋር የሚያያዝ ነው። ይሔ ደግሞ መደበኛው ሚድያ የነበረበት የብቃትና የሰው ኀይል አቅም ዝቅተኛነት ራሱን መከላከል በማይችልበት በብዙ አቅጣጫ ፈተና የበዛበት እና አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ነው።
ይህ ሁኔታ በ2012 ይቀጥላል። ምክንያቱም በሚድያው አቅም ላይ የመጣ ለውጥ የለም። አንዳንድ ሚድያዎች ራሳቸውን በተቋም ደረጃ ዳግም የመቃኘት ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ምናልባትም አዲሱ የሚዲያ ሕግ ሥራ ላይ ሲውል የገንዘብ አቅማቸውን ለማጠናከር ዕድል ሊሰጣቸው ይችላል።
ሌላው በ2011 አስቸጋሪ የነበረው ራሱ በዋናው ሚድያ ውስጥ የታየው ውድቀት አለ። በተለይ አዳዲስ የመጡ ሚድያዎች ውስጥ የገቡ የሚዲያ ውጤቶች ራሳቸው ለዚህ ተጽዕኖ የተንበረከኩበትና ራሳቸውን ፉክክር ውስጥ ያስገቡበት ነው። ከማኅበራዊ ሚድያና ሕዝበኛ ሚድያ ባሕል ጋር ፉክክር ገጥመው እንደውም ማኅበራዊው ሚድያው ከሚያደርገው ጥፋት በበለጠ በራሳቸው ላይ ጥፋት አድርገዋል የሚል እምነት አለኝ። ማኅበራዊ ሚድያው ለሙያዊ ሥነ ምግባር ይገዛል ተብሎ አይጠበቅም። ተፈጥሮውም አይደለም።
የሚድያ ካውንስል መቋቋሙና ወደ ሥራ መግባቱ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ተጠናክሮ ወደ ሥራ መግባት ከቻለ፤ ቢያንስ በመደበኛ ሚድያ ሥር የሚመጡት የሚያመጡትን ጥፋት መቀነስ ይችላል፤ ጨርሶ ሊያጠፋው ይችላል ባንልም። ካውንስል ውስጥ መግባት ሚዲያዎች የሚገዙበት የሥነ ምግባር መመሪያ አለ። በመሆኑም መረጃ አጠቃቀም ባሕል ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል።
ሚድያ ማለት የኅብረተሰቡ ነጸብራቅ ነው፤ ሁሉም ሰዎች በአገራችን እየተፈጠረ ያለውን ነገር በሥጋት፣ በጉጉት፣ በፍርሃት ነው እየተመለከቱ ያሉት፤ የእኛ ሥራ ይህን ማሳየት አለበት። የሃይማኖት ውጥረት ውስጥ ነው ያለነው፤ እዚህ ላይ ስንዘግብ ምንድን ነው መዘገብ የምንፈልገው፤ ዘገባችን ምን ተጽዕኖ ይፈጥራል የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል። በፊት ኤዲቶርያል ፖሊሲ ለስታንዳርዱ ነበር የሚገዛው። አሁን እንደተለመደው ቢዝነስ አይደለም፤ ይህን ልናስተውል ይገባል።

_____________________________

አያልነህ ሙላት ጸሐፌ ተውኔት፣ ገጣሚና መምህር

2011 በአገራችን የሆነው የተበጠበጠ ውሃ ነበር፤ ድፍርስ ውሃ። የከረምነውም እዛ ድፍርስ ውሃ ውስጥ ነው። ውሃን ጥራ ብለው በነኩት ቁጥር ደግሞ የባሰ እየደፈረሰ ነው የሚመጣው፤ ደግሞም ለማጥራት አልሞከረም። እናም እንዲሁ እንደደፈረሰ ነው ወደ አዲሱ ዓመት የምንሸጋገረው፤ እስከ አሁን የጠራ ነገር አላየንም።
የሚቀጥለው ዓመት ደግሞ የምመኘውና የምንጠብቀው ይሄ ውሃ በራሱ ጊዜ ጠርቶ ተጨማሪ ችግር ሳይፈጠር፣ አሁን ከተያዘው በትዕግስት ሁኔታዎችን ከመመልከት፣ ሕዝብም በጠብ መንጃ ሳይሆን በራሱ ህሊና ተመራማሮ ሰላም የሚያገኝበት እንዲሆን ነው። ውሃው የግድ መጥራት አለበት፤ ግን አጠራለሁ ብሎ የሚሰደፈርስ እጅ እንዳይገባበት እንመኛለን። ድፍርሱ እንዲጠራ ምኞታችን ነው፤ ምክንያቱም ‹‹ውሃ ለራሱ ሲል ይጠራል›› የሚል አባባል አለ።

 

 

_____________________________

አበበ መለሰ ግጥምና ዜማ ደራሲ

በ2011 ቆይታዬ ከአገር ውጪ በእስራኤል የነበረ ቢሆንም፤ በዛ ሆኘየ በኢትዮጵያ ያየሁት ነገር ጥሩ አልነበረም። በተከሰቱት አስከፊ ነገሮች ሁሉ የማላወቀውን ዓይነት ኢትዮጵያዊነት ነው ያየሁት። ዓመቱንም ሙሉ የሰማናቸው ነገሮች የማያስደስቱና ‹‹እንደዚህ ነን እንዴ?›› የሚል ሀሳብና ጥያቄ በውስጣችን የሚጭሩ ናቸው።
በሙያዬ እኔም የተወሰነ ነገር ለመሥራት እየተዘጋጀሁ ነው፤ አንድነታችን ማንነታችን፣ ፍቅራችን መዋደዳችን አብሮ መብላት መጠጣታችን፣ መረዳዳታችን ላይ የሚያተኩር። እኔን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የደረሰልኝ፤ አልቅሶ ገንዘብ አውጥቶም ያዳነኝ። የማውቀው ያንን ሕዝብ ነው እንጂ እርስ በእርሱ የሚጨካከን አይደለም። በአጭር ጊዜ ተለውጦ እንዲህ መሆኑ፤ በ2011 የታየውና የተሰማው በጣም የሚሳዝን ነው።
በአዲሱ ዓመት እኔ በሙያዬ ላስተምርና መልዕክት ላስተላልፍ ብቻ ነው የምችለው፤ ይህን ሁሉ የሚፈታ ጸሎትና የእግዚአብሔር እርዳታ ነው ብዬ አምናለሁ።

 

_____________________________

አደስታ ሐጎስ ስዓሊ

በ2011 የነበረው በጣም አስቸጋሪና ሰላም የጠፋበት፤ ስደትና ችግር የተፈጠረበት ነው። በእርግጥ ወደማብቂያው እየተሻለ መጥቷል። በበኩሌ ተስፋ የማደረግው የሚመጣው ዓመት በጣም ደኅና እና ጥሩ ይሆናል ብዬ ነው። እስከአሁን የሆነው ‹‹ካልተበጠበጠ አይጠራም›› እንዲሉ ሕዝቡ ጋር የነበሩ ነገሮች መውጣታቸው ነው። ከዚህ ባለፈ ፈጣሪ ለክፉ አይሰጠንም የሚል እምነት አለኝ።
ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። መልካሙ የመጣል የሚለው ተስፋ እውን እንዲሆንም በጎ ማሰብ ያስፈልጋል። እንዲሁም ወጣቱ ልብ ገዝቶ መኖር፤ ወሬ እንደማያዋጣ ማወቅ አለበት። አክቲቪስት ነን ብለው የሚበጠብጡትንም ማሳረፍ ይገባል። ሰዉ የሚበጣበጠው የውጪ ወሬ እየሰማ ነው፤ የሚያወሩት ሰዎች ደግሞ ለራሳቸው ጥቅም ነው። ኢትዮጵያ ሰላም ከሆነች አገራችሁ ተመለሱ ስለሚባሉ አገራቸው ሰላም እንድትሆን የማይፈልጉ ናቸው።

_____________________________

ፀደንያ ገብረማርቆስ ድምጻዊት

ኢትዮጵያን እንደ ሰው እንውሰዳትና፤ በአንድ ዓመት ውስጥ የተለያየ አመል የነበራት ሴትዮ ነበረች፤ ለእኔ። የመጀመሪያው ስድስት ወር ላይ ፍቅር የሰፈነባት፤ ፍቅር የምትሰጥ ሴትዮ ነበረች። ከዛ በኋላ እየጎረበጣት፣ አልመች ብሏት የምትነጫነጭ ጸብ የበዛባት ሴትዮ ነበረች፤ ደም መፋሰስና ግብግብ ያስተናገደች። አሁን ደግሞ ያንን በትዕግስት ለማሳለፍ የምትሞክር ሴት እየመሰለች ነው። እየተገላበጠች እንዳለች፤ በአንደኛው ጎን ሳይመቻት በሌላው ጎን እየተመቻት ብቻ በትዕግስት ለማለፍ እሞከረች እንዳለች ይሰማኛል።
በ2012 የተሻለና ጥሩ ነገር ይመጣል ብዬ አስባለሁ። ይህም ‘እገሌ እንዲህ ያድርግ እገሌ ያንን ያድርግ’ የምንባባልበት ጉዳይ አይደለም። ሕግና ስርዓት ይስፈን። በተፈጥሮ ሕግ ሁሉን ማስደሰት አይቻልም ግን አብዛኛውን ህብረተሰብ ያማከለ አስተሳሰብ ማምጣት እንዲሁም አብዛኛውን ያማከለ ሕግና ስርዓትን ማስፈን የሚያቅት አይመስለኝም።

 

_____________________________

መሀሪ ገላው የአማጋ ጮራ ጋዝ ፋብሪካ ሠራተኛ

ጥሩ ዘመን ነው ያሳልፍነው ክረምቱም አንደ ክረምት ጥሩ ሆኖ ነው ያለፈው በመሐል ግን የገበያ ንረት አጋጥሞናል ቀስበቀስ በጊዜ ሒደት ይስተካከላል ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን ሁላችንም ፍቅር ቢኖረን ይበጃል አንተ ትብስ መባባል ለአገር ማሰብ የተቸገሩ ወገኖችን ማሰብ ይገባናል።
የሚመ ጣው ዓመት 2012 ሰላም እንደሚሆን ይታየኛል ምርጫውም ጥሩ እንደሚሆን አምናለሁ። ብርሃን የሆነ ሰላም፣ ፍቅር፣ እርስ በእርስ መተሳሰብ ያለበት፣ የአገር ፍቅር ኢትዮጵያዊነት ስሜት ይኖራል ብዬ አስባለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here