‹ታላቁ ጥቁር› በሚል ርዕስ በንጉሤ አየለ የተጻፈው የታሪክ መጽሐፍ በቅርቡ ለሥርጭት ከበቁ እና አንፃራዊ ተነባቢነትን ከተጎናፀፉ መጽሐፍት አንዱ ነው፡፡ ብርሃኑ ሰሙ በሰሜን አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ቀደምት የግንኙነት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነውን ይህንን መጽሐፍ በማንበብ ምልከታቸውን እነሆ ቅምሻ ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው 2010 ለሕትመት የበቃው እና ዛሬ ለዚህ ገጽ የቅኝት ዳሰሳ ላደርግበት የመረጥኩት መጽሐፍ፥ አሁን ብቻ ሳይሆን ዘመን ተሻግረው ሊነበቡ ከሚችሉ መጻሕፍት ተርታ የሚመደብ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በንጉሤ አየለ ተካ ተጽፎ ለአንባቢያን የቀረበው “ታላቁ ጥቁር” የተሰኘ የታሪክ መጽሐፍ የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አነሳስና ጉዞን በርዕሰ ጉዳይነት የያዘና በ473 ገጾች ተቀንብቦ የቀረበ ዳጎስ ያለ ጥራዝ ነው፡፡ ለመጽሐፉ ዝግጅት ግብአት ሆነው ያገለገሉት መረጃዎች በሙሉ ከአሜሪካ አብያተ መጻሕፍት የተገኙ ናቸው፡፡
ደራሲው በገጽ 32 እንዳሰፈሩት፣ “የመረጃ ፍለጋው በሦስት የሩቅ ዘመናት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ አንደኛው፣ በ1808 ‹በኒውዮርክ ነበሩ› በተባሉ የሐበሻ ተወላጆች ዙሪያ ተጨባጭ ሪከርዶችንና ዝርዝሮችን መፈለግና ዙሪያ ገባውን ማጥናት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያና አሜሪካ መንግሥታት መሐል የኦፊሴል ግንኙትና ወዳጅነት ለመመሥረት መነሻ እስከሆነው እስከ 1900 ድረስ ባለው ጊዜ የአበሾችና የሐበሻነት አሻራ (ዱካ) በምዕራቡ ዓለም ውስጥ መልቀም ነበር፡፡ሦስተኛው ትኩረት የኢትዮ-አሜሪካ የኦፊሴል ግንኙነት ምሥረታና ተያይዘው ያሉ መንግሥታዊና የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብሮች እና ግንኙነቶች ዱካቸውን በጥልቀት መቃኘት ነበር፡፡”
ደራሲው ይህን መሠረት ባደረገ ፍለጋቸው ያገኟቸው መረጃዎች ስፋት፣ ጥልቀትና ብዛት “ያስገርማል” የሚለው ቃል የሚገልጸው አይደለም፡፡ የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኙነት አጀማመር፣ ጉዞና ዕድገቱን ለማሳየት በተገለጸው ገጽ ከተነገሩ አስደማሚታሪኮች መሐል፣በቀዳሚነት ወደ አሜሪካ የሔዱት ኢትዮጵያዊያን፣ በ1808 በተሰደዱበት አገር ቤተክርስቲያን ስለማቋቁማቸው የሚነገረው አንዱ ነው፡፡
ይህን እውነት የሚያረጋግጥመረጃ ያቀረቡት ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ፣ ባገኙት መረጃ ብቻ ሳይሆን፤በአሜሪካ የአቢሲኒያ ቤተ ክርስቲያን ስላቋቋሙት ሰዎች አርቆ አሳቢነት፣ ያስገረማቸውን በሚከተለው መልኩ በመጽሐፋቸው ውስጥ አስፍረውታል “የአቢሲኒያ ባፕቲስት ቤተክርስቲያን መሥራቾች በ1809 ለኒውዮርክ ማዘጋጃ ቤት ባስገቡት የፈቃድ ምዝገባና የምሥረታ ማፅደቂያ ሰነድ ላይ ‹አቢሲኒያ› የሚለው መጠሪያ ከትውልድ ትውልድ እንኳ ሲተላለፍ እንዳይለወጥ፣ የትኛውም መጪ ትውልድ ሥሙን የመለወጥ ሥልጣን እንደሌለው መሥራቾቹ በጉባዔ መወሰናቸውና ይህም ድንጋጌ ከምዝገባና የፈቃድ ማፅደቂያ ሠነድ ጋር አብሮ ተመዝግቦ መገኘቱ ነው፡፡”
ከ1905 እስከ 1909ባለው ጊዜ ከኢትዮጵያ ቦረና አካባቢ የተንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካ መግባታቸው መረጃውን በፎቶ ግራፍ አስደግፎ ያቀረበው“ታላቁ ጥቁር” መጽሐፍ ስለነዚህ ሰዎች የሚከተሉትን ጥያቄዎችን አንስቷል፡-ሐበሾቹ በዚያን ዘመን ከየት መጡ? የት ደርሰው ይሆን? በየት በኩልና እንዴትስ አድርገው መጡ? ለተወላጆቻቸው ያስተላለፉት ምን ታሪክ ይኖር ይሆን? ተወላጆቻቸውንስ በምን ጥናት፣ እንዴትስ ማግኘት ይቻል ይሆን?› የሚል፡፡ ለጥያቄው ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ “ለወደፊት የሚገኝ የተጨበጠ ነገር ካለ፣ የዚህ ታሪክ ጸሐፊ ይከታተላል”የሚል ቃል ገብተዋል፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት “የአቢሲኒያ ቡና” በአሜሪካ ዝነኛና ታዋቂ የነበረውን ያህል፥“የአሜሪካኒ” ካኪ ጨርቅና አቡጀዴ ደግሞ በኢትዮጵያ ተወዳጅ ነበሩ፡፡ይህ ደግሞ አሜሪካዊያን ከኢትዮጵያዊያን ጋር የንግድ ወዳጅነት ስምምነት ለመመሥረት አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡“በአቢሲኒያ ሰፊ ሕዝብ የሚኖር፣ የፖለቲካ ነጻነቱም የተጠበቀና ምርቶቻችንን ሊገበይ የሚችል ሁኔታ ያለ ሆኖ፣ ነገር ግን በእኛ በኩል ኢፊሴላዊ ተጠሪ እንኳን የሌለን መሆናችን” በሚል ለመንግሥታቸውየጥናት ሪፖርትየሚያቀርቡና ለክፍተቱ መፍትሔ እንዲፈለግለት የሚያሳስቡ አሜሪካዊያን ነበሩ፡፡
የንግድ ስምምነትን ለማስቀደም፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን የማስጀመሩ እንቅስቃሴ የተጀመረው ዐፄ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ድል ከተቀዳጁ በኋል ስለነበር፣ አሜሪካ ብቻ ሳትሆን ሌሎች አገራትም ለዐፄ ምኒልክ፣ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ልዩ ክብርና ዕውቅና ይሰጡ እንደነበር በ“ታላቁ ጥቁር” መጽሐፍ ውስጥ በስፋት ይታያል፡፡በዚህ ምክንያት አሜሪካ አዘጋጅታ ወደ ኢትዮጵያ በላከችው ቀዳሚው የንግድ ስምምነት ውል ሰነድ ላይ “በውጫሌ ውል” የተፈጠረው ዓይነት ስህተት እንዳይደገም ስትጠነቀቅ ይታያል፡፡ዐፄ ምኒልክ በአሜሪካን አገር ለሚካሔድ ታላቅ ዓመታዊ ኤግዚቢሽን በክብር እንግድነት ተጋብዘዋል፡፡የዐፄ ምኒልክ በንግድ ትርኢቱ ላይ መጋበዝ የአውሮፖ ጋዜጦችን ትኩረት ስቦ በስፋት አወያይቷል፡፡ ስለ ዐፄ ምኒልክ የንግድ ዕውቀት ከተሰጡ ምስክርነቶች መሐል የሚከተሉት ይገኙበታል፡- “እውነተኛውን የነጋዴ ልዑል ማግኘት ከፈለጋችሁ፣ወደ አቢሲኒያ መሄድና እራሳችሁን ለምኒልክ ማስተዋወቅ አለባችሁ”፤ “ምኒልክ ታላቅ ንጉሣዊ ነጋዴ ናቸው፡፡የአሜሪካ የኢንዱስትሪ አስፋፊዎችን እምነት ለማግኘት፣ ፈቃድ ከመስጠት ባሻገር አካፋ እስከማቀበል ሊደርሱ የሚችሉ ሰው ናቸው”፤ “በምኒልክ ዘንድ ያልረባ ነው የሚባል የንግድ አካባቢ የለም፡፡ከውጭ በማስመጣትም ሆነ ወደ ውጭ በመላክ፣ የአገሪቱ ዋናው ነጋዴ እራሳቸው ናቸው”፤ “ለዙፋናቸው ደኅንነትና ለምቾታቸው የሚነግዱ ሳይሆኑ፣ ንግድ ለሚሰጠው ጥቅም ሁሉ (for all it is worth) የሚሠሩ ናቸው”፤ “በንግዱ የውጭ ምንዛሪ ወደ እርሳቸው ይጎርፍላቸዋል፡፡ ገንዘቡን ለሕዝባቸው ጥቅም ለማውጣት ደግሞ እጃቸው ክፍት ነው”፤ “አብዛኞቹ የዓለማችን ነገሥታት፣ ንግድን ሥም የሚያጎድፍ (derogatory) አድርገው ያዩታል፡፡ምኒልክ ግን እንደሌሎች ነገሥታት ኩራቱም ዘውዳዊ ማዕረጉም ያላቸው ሆነው፣ ነገር ግን የተለየ አመለካከት ነው ያላቸው”፤ “ምኒልክ በአገሪቱ ውስጥ ኃያልና ግዙፍ ነጋዴ እንደሆኑ ሁሉ፣ ንግዱን ሲያካሒዱ ግን እንደጉልበተኛ ሆነው አይደለም፡፡ከሕዝባቸው ዕቃን ሲገዙም ሆነ ሲሸጡለት፣ በተገቢውና በተተመነ ተመጣጣኝ ዋጋ ነው፡፡”
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በዋነኛነት ንግድን ማዕከል ያደረገ ስምምነት ማድረግን ዓላማ አድርጋ መንቀሳቀሷን ያዩት ፈረንሳይ፣ ኢጣሊያና እንግሊዝ… የመሳሰሉት አገራትከኢትዮጵያ ማግኘት የሚፈልጉትን ጥቅም ላለማጣት እርስ በእርስ መፋጠጣቸውና በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከዐፄ ምኒልክ ጋር ለመወዳጀት መጣራቸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን መጥቀሙ በደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ መጽሐፍ ይታያል፡፡ የ“ታላቁ ጥቁር” አመራር የአውሮፓ ጋዜጦችን ትኩረት በምን ያህል ስፋትና ትኩረት ስቦ እንደነበር የሚከተለው ዘገባ ያመለክታል፡- “ንጉሥ ምኒልክ ከዓለም ጎን እየተሰለፉ ነው፡፡ መጀመሪያ መሀዲስቶችን አስወገዱ፡፡ ቀጥሎ ኢጣሊያኖችን ከግዛታቸው አስወጡ፡፡ ከዚያም የአውሮፓ መንግሥታት ዲፕሎማቶችን እርስ በእርስ በሚያቃርን ዘዴ እየጋበዙ ተቀበሏቸው፡፡ አሁን ደግሞ ለግዛታቸው የራሳቸውን ገንዘብ ሊሠሩ ነው፡፡”
ስለሁለቱ አገራት ሕዝብና መንግሥታት ግንኙነት የቀድሞውን ብቻ ሳይሆን የቅርብ ገጠመኝና ታሪኮችን ያስቃኛል – “ታላቁ ጥቁር” መጽሐፍ፡፡ ዛሬ የአሜሪካንን የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ከባድእንደሆነው ሁሉ በ1940ዎቹም ተመሳሳይ ችግር ነበር፡፡“የ2ኛው የዓለም ጦርነት ተቀጣጥሎ አሜሪካ በጦርነቱ ውስጥ ስትገባ… ሕገ-ወጥ ስደተኞች በዩናይትድ ስቴትስ አርሚ (ሠራዊት) ውስጥ ተመዝግበው በወታደርነት ካገለገሉ፣ ከተመዘገቡበት ዕለት ጀምሮ ዜግነት ይሰጣቸዋል የሚል አዋጅ ተነገረ፤” በዚያ ዘመን በዚህ ዕድል ተጠቅመው አሜሪካዊ ዜግነት ያገኙ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ የኒውኩሊየር ኬሚካል ጦር መሣሪያ የሚያግድ ሕግ እንዲወጣ እ.አ.አ. በ1958 የመጀመሪያውን ሐሳብ አቅርባ ነበር፡፡በወቅቱ ደራሲ ክቡር ሐዲስ ዓለማየሁ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ነበሩ፡፡ “የኒውኩሊየር ቦንብ እንዳይሠራ ማገጃ መውጣት አለበት” ብለው ጹሑፍ አቅርበው ውይይት እንዲካሔድበት ጠየቁ፡፡ጉዳዩ የኃያላን መንግሥታቱን ኃይልና ጥቅም የሚጎዳ ስለሆነ ድንጋጤና ጭቅጭቅ አስነሳ፡፡ “የሐዲስ ሐሳባቸውን አላነሳም ማለት ደግሞ ለይፋ ክርክርም የማይመች ስለሆነ፣ ከትላልቆቹ መንግሥታት ጉዳዩ ወደ አዲስ አበባ ለንጉሡ ተነግሮ ሐዲስ ነገሩን እንዲተውት ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ ተላለፈላቸው፡፡ሐዲስም ሐሳቡን ዊዝድሮው አላደርግም (አልለውጥም) ሆኖም ግን በጥያቄው አልገፋበትምና በሪከርድ ፋይል ሆኖ ይቀመጥልኝ በማለታቸው ሐሳቡ ፋይል ተደርጎ በሪከርድ እንዲቀመጥ ሆነ፡፡”
ይህ ታሪክ ከተፈፀመ ከአምስት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ያመለጣት ትልቅ ዕድልም በመጽሐፉ ሰፍሯል፡፡ “በቅርቡ የተመድ ሀምሳኛ ኢዮቤልዩ በዓል ሲከበር የመሥራች አባል አገራት ታሪካዊ ንግግር አንዲያደርጉ ሰዓት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ሌሎች ያንን ዕድል አላገኙም፡፡በተጠባባቂነት ጊዜ ካገኙ ሊናገሩ የተዘጋጁም ነበሩ፡፡ኢትዮጵያ ግን በመሥራችነቷ ዕድል ነበራት፡፡ አቶ መለስም ተገኝተው ትላልቆቹ አገራት ከተናገሩ በኋላ አቋርጠው ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡››
መጽሐፉ የንግድ ውል ስምምነትን ማስቀደም ዋነኛው ዓላማው አድርጎ የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አነሳስና ሒደቱን ሲያስቃኝ እግረ መንገዱን በርካታ የኢትዮጵያፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ… ጉዳዮችንም ያነሳል፡፡ የአባይ ወንዝን ለማጥናት ወደ ኢትዮጵያ ስለመጡ የተለያዩ የውጭ አገር ዜጎች፣ ለዚሁ ጥናት ከመጡት መሐል አንዱ ፈረንሳዊ ኢትየጵያ ውስጥ ስለመሞቱ፣ ግብር የማብላት ስርዓት ምን ይመስል እንደነበር፣ ለልማት የሚነሱ ነዋሪዎች ስለሚስሰጣቸው ጥቅማ ጥቅምና ካሣ፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ስለነበረው የንግድ እንቅስቃሴ፣ የአረብ ነጋዴዎች በኢትየጵያ ስለነበራቸው ሚና ሰፊ መረጃ ይሰጣል፡፡ መጽሐፉ ስለትላንቱ ሕዝብ፣ አገርና ታሪካችን አዳዲስ መረጃዎችን ከመያዙም ባሻገር፥‹ትላንት በነበርንበት ከፍታ ላይ ዛሬ እንገኛለን ወይ?› የሚል ጥያቄ በውስጣችን ያጭራል፡፡
ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ የሕትመት ብዙኃን መገናኛዎች ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የሠሩ ሲሆን፣ የመጽሐፍት ደራሲም ናቸው፡፡ በኢሜይል አድራሻቸው ethmolla2013@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ፡፡