የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልልደ ደንቢ ዶሎ ከተማ አዲስ በረራ ሊጀምር መሆኑ ታወቀ። በረራው በቀጣዩ ጥቅምት 2012 እንደሚጀምርም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አስራት በጋሻው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የደንቢዶሎ ኤርፖርት ግንባታው ቢጠናቀቅም፣ የአጥር ሥራዎችን ጨምሮ መጠናቀቅ ያለባቸው ሥራዎች ገና ባለማለቃቸው በረራው እንዲዘገይ መደረጉን ያወሱት አስራት፣ ከተቋሙ አንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስፍራው በማቅናት ክፍተቶቹን ለይቶ በመምጣቱ ያንን የማስተካከል ሥራ በመሠራት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። ህብረተሰቡ በረራው ቶሎ እንዲጀመርለት እየጠየቀ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
ደንቢዶሎ ከአዲስ አበባ 624 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝ ሲሆን በአካባቢው በርካታ የፍራፍሬና የሰብል ምርቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የወርቅ ምርትም እንዳለ ይታወቃል።
ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012



