የባህር ዳር ቀጥታ የአበባ ጭነት አገልግሎት ተቋረጠ

0
727

አምስት የአበባ አምራች ኩባንያዎች ከባህር ዳር ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት በሳምንት ኹለት ቀናት 30 ቶን አበባ ለማቅረብ የሚያደርጉት የቀጥታ በረራ መቋረጡን የአበባ አምራች ኩባንያዎቹ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራው የተቋረጠው አቅርቦቱ በመቀነሱ ነው ብሏል።

የጣና ፍሎራ የእርሻ ልማት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ክንዳለም ፀጋዬ፣ የአበባ ልማቱ በዓመት 58 ሚሊዮን ዘንግ በማምረት ከ40 ሚሊዮን እስከ 48 ሚሊዮን ዘንግ ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እያስገባ መሆኑን ገልጸው፣ ይሁን እንጂ አምስት አበባ አምራች ድርጅቶች በሳምንት ኹለት ቀን 30 ቶን አበባ ለማቅረብ በተስማማነው መሰረት ሥራ ብንጀምርም ሦስቱ ድርጅቶች በገቡት ቃል መሰረት ማቅረብ ባለመቻላቸው የባህር ዳር ቀጥታ ጉዞው መቋረጡንና ይህም በድርጅቶቹ ላይ መስተጓጎል መፍጠሩን ተናግረዋል።

አበባዎቹ ከባህርዳር ተነስተው አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ አውሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ እንደሚንገላቱና ከፊሎቹ እንደሚጠወልጉ በማውሳት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቀጥታ በረራው መጀመሩን አስታውቀዋል። የጣና ፍሎራ እርሻ ልማት ለ950 ዜጎች የሥራ እድል እንደፈጠረም ነው የገለጹት።

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አስራት በጋሻው፣ ኩባንያዎቹ እናቀርባለን ያሉትን ምርት በሚፈለገው ደረጃ ባለማቅረባቸው በረራው መቋረጡን አስታውቀዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የፕሮሞሽን እና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ይኼነው ዓለም፣ ቀጥታ በረራው የተቋረጠው ኩባንያዎቹ በጋራ እንዲያቀርቡ የተተመነባቸውን 30 ቶን አበባ ማቅረብ ባለመቻላቸው ነው ብለዋል።

እንደ ይኼነው ገለጻ፣ አበባ እና ፍራፍሬ የሚያመርቱ ኩባንያዎችን ለማበረታታት የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ ጋር በመሆን በ2010 አምራቾቹ ከባሕር ዳር ወደ አውሮፓ የቀጥታ በረራ እንዲያደርጉ ታስቦ የግዙፍ የጭነት አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ተሠርቶ፣ በባህር ዳር አየር ማረፊያ ግዙፍ ማቀዝቀዣ ተገንብቶ፣ ጥር 2011 የአበባ ምርቶች ከባሕር ዳር ወደ አውሮፓ በቀጥታ እንዲላኩ ተደርጎ ነበር።

ይሁን እንጂ አምስቱ የአበባ አምራች ኩባንያዎች ተቀናጅተው በሳምንት ኹለት ቀናት 30 ቶን አበባ ማቅረብ ባለመቻላቸው የቀጥታ በረራው ቀጣይ መሆን አልቻለም።
የአበባ ምርቶቹ በተገቢው መንገድ ለውጭ ገበያ አለመቅረባቸው አገሪቱንም ክልሉንም እንደሚጎዳ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ይኼነው፣ ችግሩን ለመፍታት አምስት የሆላንድ የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ አምራች ድርጅቶች በቁንዝላ አካባቢ ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉንና ኩባንያዎቹ ማምረት ሲጀምሩ በማቀናጀት የቀጥታ በረራው ሊጀምር እንደሚችል አውስተዋል።

ኩባንያዎቹ ለሚያስገቡት ግብዓት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስፈላጊውን ትብብር እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ይኼነው የተናገሩት። በክልሉ ተገንብተው ሥራ የተጀመረባቸው እና እየተገነቡ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም የሥራ ዕድል መፍጠሪያ፣ የቴክኖሎጂ ማሸጋገሪያ እና የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ እንዲሆኑ ታስቦ እየተሠራ እንደሆነ ቢሮው አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here