ስድስት የጥንብ አንሳ አሞራ ዝሪያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል

0
806

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ስምንት የጥንብ አንሳ አሞራ ዝሪያዎች ውስጥ ስድስቱ በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ታወቀ። ይህም ሥነ ምህዳርን ፅዱ ከማድረግ ረገድ መዛባቶች ሊፈጥር እንደሚችል ተገልጿል።

የዱር እንስሳትና ልማት ጥበቃ ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሰለሞን ወርቁ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በአፍሪካ ብቻ እንደሚገኙ ከሚነገርላቸው አስራ አንድ ዓይነት የጥንብ አንሳ ዝርያዎች ስምንቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቢሆንም ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹ አደጋው አንዣቦባቸዋል።

ለጥንብ አንሳዎቹ ሞት ምክንያት ከሆኑ ችግሮች መካከልም በመርዝ የሚሞቱ እንደ ውሾች ያሉ የቤትና የዱር እንስሳትን ስለሚመገቡ በቀላሉ ለሞት እየተዳረጉ እንደሆነ ሰለሞን ተናግረዋል። በተጨማሪም በትላልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ላይ በማረፍ በኤሌክትሪክ አደጋ የሚሞቱት ጥንብ አንሳ አሞራዎችም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል። ‹‹በአንዳንድ አካባቢዎች ባሉ የአምልኮ ስርዓት ሳቢያ ጥንብ አንሳዎችን በመግደል ለባእድ አምልኮ መጠቀማቸውም ለመጥፋታቸው ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎች ደርሰውበታል›› ብለዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት በመርዝ የሚሞቱ የቤትና የዱር እንስሳትን ጉድጓድ ቆፍሮ መቅበር ላይ የፓርክ ጠባቂዎች እና ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ያወሱት ሰለሞን፣ በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችንና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በፕላስቲክ እንዲሸፈኑ ለማድረግ ከኢትዮጵያ መብራት ኃይል ጋር በውይይት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዱር እንስሳትና አእዋፍ ጥበቃ ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች (ስካውቶች) በጥንብ አንሳ አሞራ እንክብካቤ፣ መለየት፣ ጥበቃና ምዝገባ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

የጥንብ አንሳ አሞራዎች በስፋት የሚገኙት በአዋሽና አዳጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርኮች በመሆኑ በፓርኩ የሚገኙ የጥበቃ ሠራተኞች በአሞራዎች እንክብካቤ፣ መለየት፣ ጥበቃና ምዝገባ ላይ በቂ እውቀት አግኝተው ዝርያቸውን ከጥፋት ለመታደግ እየተሠራ መሆኑን ሰለሞን ተናግረዋል። ዝሪያቸውን ለመታደግም ባለሥልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ስለ ጥንብ አንሳ አሞራ በህብረተሰቡ ዘንድ የነበረው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ምንም ዓይነት እንክብካቤና ጥበቃ ሳይደረግላቸው ለጥፋት መዳረጋቸውን ያወሱት ሰለሞን፣ በአሁኑ ወቅት ሥነ ምህዳርን ፅዱ ከማድረግ አንፃር ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን በስልጠና የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here