በመቶ ዓመት ውስጥ 90 በመቶ የሰብል እና 50 በመቶ የእንስሳት ዝርያዎች ጠፍተዋል

0
1168

ባለፉት 100 ዓመታት በኢትዮጵያ 90 በመቶ የሰብል ዝርያዎች እንዲሁም 50 በመቶ የእንስሳት ዝርያዎች ለደን፣ ለእንስሳትና የደቂቅ አካላት ብዝሃ ሕይወት ትኩረት በመነፈጉ ጠፍተዋል ሲል የብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በየጊዜው እየተራቆተ ያለውን የብርቅዬ እንስሳት መኖሪያ የሆነውን ደን መልሶ እንዲያገግም ባለመደረጉ ሰፊው የብዝሃ ሕይወት ሃብት አደጋ ላይ ሊወድቅ ችሏል።

በተጨማሪም መጤ እና ወራሪ የሆኑ ዝርያዎች በስፋት መሰራጨታቸው ምክንያት መሆኑን ኢንስቲትዩቱ በጥናት ማረጋገጡን ያስታወቀ ሲሆን፣ መጤ እና ወራሪ የሆኑ እንደ እንቦጭና ሌሎችም አረሞች በኢትዮጵያ በስፋት ሲበቅሉ ትኩረት ስላልተሰጣቸው አደጋ ሊያደርሱ መቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

እነዚህ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎች በመጥፋታቸው አገር በቀል መድኃኒቶችን ማግኘት አልተቻለም ሲል ያስታወቀው ኢንስቲትዩቱ፣ ከዚህ በተጓዳኝም አገሪቷ ዝርያዎቹን በማጣቷ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች ብሏል።

በኢትዮጵያ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የመድኃኒትነት ይዘት ያላቸውን ምግቦች የሚመገብ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ፈለቀ፣ ባህላዊ መድኃኒት የሚያዘጋጁ በርካታ ተቋማት መድኃኒት የሚያዘጋጁት ህብረተሰቡ ከሚያውቃቸው ምግቦች መሆኑን አውስተዋል። ይሁን እንጂ የሚመለከታቸው አካላት ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠታቸው ሰብሎቹ ለጥፋት ተዳርገዋል ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በተለይ ከተለያዩ አዝርዕትና ከሆርቲ ካልቸር ሌላ የደን፣ የእጽዋት፤ የእንስሳትና የደቂቅ አካላት ብዝሃ ሕይወትም ትኩረት ተነፍጓቸው ቆይቷል። እየተባባሰ ለመጣው ችግር እልባት ለማበጀት ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑም ታውቋል። በዚህም ለመጥፋት ተቃርበው የነበሩ ከ80 በላይ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል የማራባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት ፈለቀ።

አገር በቀል የሰብል ዝርያዎችን በውጭ አገር የሰብል ዝርያዎች በመተካት ምርታማ መሆን ይቻላል የሚለውን የተዛባ አመለካከት ለማስትካከልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ፈለቀ ገልጸዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በቀጣይ ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ እንዲቻል ከአስፈፃሚ እሰከ ፈፃሚ አካላት አስተባብሮ ለመሥራት ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል። ለውጭ አገር ምርምር የሚፈለጉ የሰብል ዝርያዎች ተለይተው በኢንስቲትዩቱ እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲተላለፉ እየተደረገ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች የባለቤትነት ጥያቄ እንዳይነሳባቸው በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የብዝሃ ህይወት ስምምነት ከፈረመች በኋላ፣ 89 አዝርዕትና የሆርቲ ካልቸር ዝርያዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፤ ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ ናሙናዎች መሰብሰቡን ገልጿል።

በተለይ በየጊዜው እየተራቆተ ያለውን የብርቅዬ እንሰሳት መኖሪያ የሆነውን ደን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል። በመሆኑም ፓርኮች አካባቢ የልማት ሥራን በመሥራትና የግንዛቤ ማስጨበጫን በመፍጠር ሰፊውን የብዝሃ ሕይወት ሃብት ለማስጠበቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተለያዩ አዝርዕትና ከሆርቲ ካልቸር ሌላ የደን፣ የእጽዋት፤ የእንስሳትና የደቂቅ አካላት ብዝሃ ሕይወትም ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተጠቁሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here