ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብስክሌትን እንደ አንድ የትራንስፖርት አማራጭ አድርገው እንዲገለገሉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ የብስክሌት ግልቢያ ንቅናቄ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ሊካሄድ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በመጪው እሁድ በሚካሄደው በዚሁ የብስክሌት ግልቢያ ንቅናቄ ላይ ህብረተሰቡ የብስክሌት ትራንስፖርትን እንደባህል እንዲያጎለብተው ለማስገንዘብ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለድርሻ አካላት እና ልምድ ያላቸው ብስክሌተኞች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡
ፕሮግራሙ ብስክሌት መጠቀም ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ እና ዘላቂነት ያለው የመጓጓዣ ሞዳሊቲ መሆኑን ለማሳየት እድል ይፈጥራል፡፡
እንዲሁም በአዲስ አበባ ብስክሌት የመጠቀም ባህልን ለማሳደግና፤ የሚታዩትን ኢኮኖሚያዊ እና ጾታዊ አመለካከቶችን ለማሸነፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ቢሮው ገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት የፊታችን እሁድ ግንቦት 21 ቀን 2014 ከጠዋቱ 3፡00 ፒያሳ ላይ ፕሮግራሙ የሚጀመር መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።