ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) “ተማሪዎች ዘንድሮ በያላችሁበት ትደግማላቸሁ” በሚል የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በ2014 የትምህርት ዘመን ማጠቃለያ ላይ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው ማጠቃለያ ፈተናዎችን ለመውስድ እየተዘጋጁ ባለበት ወቅት፣ ማህበራዊ ኃላፊነት በጎደላቸው አካላት ሆን ተብሎ ተማሪዎችን ለማዘናጋት በዘንድሮ ዓመት ከክፍል ወደ ክፍል መዘዋወር የለም ተብሎ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የሚናፈሰው ወሬ ፍፁም ከእውነት የራቀ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የወረደ አቅጣጫ የሌለ መሆኑን የገለፀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ባለድርሻ አካላት “ተማሪዎች ዘንድሮ በያላችሁበት ትደግማላቸሁ” በሚል አሉባልታ ሳይጠለፉ እና ሳይምታቱ ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው ለተሻለ ውጤት እንዲተጉ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አሳስቧል።