መልክሽ አይብለጥሽ!

0
1238

ራስሽን እንዴት ታይዋለሽ? ራስሽን በምንስ ትመዝኛለሽ? ቆንጆ ነኝ ማለት ነው ወይስ ጎበዝ ነኝ ማለት ነው የሚቀናሽ? በውበት አንደኛ ነኝ ወይስ የማልችለው የማልጋፈጠው ፈተና የሌለ ጀግኒት ነኝ የሚለውን ነው በሐሳብሽ የምታመላልሺው? የሰውነትሽ ክብደት መጠን ማነስ ወይም መብዛት ነው የሚያስጨንቅሽ ወይስ ስለጉዳዮች ያለሽና የሌለሽ መረጃ ነው የሚያሳስብሽ?

መስፈሪያችን የማኅበረሰብ ስሪት ነው። አንድ ሰው ራሱን ‹እንዲህ ነኝ!› ለማለት ወይም እንዲያ እንደሆነ ለማመን፣ ሚዛኑ ማኅበረሰቡ ጋር ነው። በዚህ መሠረት የሴት መመዘኛ ውበት እና የቤት ውስጥ ሙያ ሲሆን፣ የወንዱ ደግሞ አልደፈር ባይነትና ኃይለኝነት ነው። ሁለቱም የማኅበረሰቡን መስፈርት አሟልተው ተቀባይነት ለማግኘት በየተመደቡበት ይለፋሉ።

ግን እንደዛ መሆን የለበትም፤ ለሴቶችም ለወንዶችም። ሴቶች ራሳችንን ሌሎች እንደሚያዩን ማየት የለብንም። ሌሎች ስል ወንድሞችን ብቻ ሳይሆን ስርዓትንና አስተሳሰብን ጭምር ነው። በተለይም በመልክ ወይም በሚታይ ውበት አንጻር እንድንመዘን መፍቀድ የለብንም። አልፎም እኛም እህቶቻችንን በዛ መንገድ ልንመዝን አይገባም።

እውነተኛ ሁኔታ ውስጥ ራሳችንን አስገብተን ቀጥሎ በምጠይቀው ጥያቄ ራሳችንን እንፈትን። ጥያቄው ይህ ነው፣ አንዲት ሴት መድረክ ላይ ስትወጣና ንግግር ስትጀምር፣ ከዐይናችን እና ከጆሮአችን የትኛው ነው ለዚህች ሴት የሚቀርበው?

ብዙዎቻችን ዐይናችን እንዲያሸንፍ ነው የምናደርገው። ምንድን ነው የለበሰችው? ምንድን ነው የተቀባችው? ፀጉሯ ምንድን ነው? አረማመዷ እንዴት ነው? ውይ ቅጥነት/ውፍረት…ወዘተ የመሳሰሉ ሐሳቦችን እናሰላስላለን። ከዛ ከመድረክ ውጪ ሰብሰብ ብለን ስናወራ፣ ‹እርሷ ያነሳችው ሐሳብና የተናገረችው ንግግር…!› ከማለት ይልቅ፣ ‹የለበሰችው ልብስ አልተመቻትም፣ የተቀባችው ቀለም ደምቆባታል› የሚልና መሰል አስተያየት እናበዛለን።

ይህ ዓይነቱ አስተያየት ከምንናገረው ይልቅ መስለን ለምንታየው እንድንጨነቅ ያስገድደናል። ምን ልናገር፣ ምን ልማር፣ ምን ልወቅ፣ ምን ሐሳብ ልስጥ ሳይሆን፤ ምን ልልበስ፣ ምን ልቀባባ ወዘተ የሚለው የበለጠ እንዲያሳስበን ያደርጋል።

እንዲያ ባንሆንስ ግን?! ራሳችን ላይ ሥራ ላለማብዛት ከከንፈራችን ቀለም ይልቅ ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል፣ ከራስ ቅላችን ጸጉር ይልቅ ከአእምሯችን ሊገኝ የሚችለው ሐሳብ፣ ከጆሮ ጌጣችን ይልቅ ልብ ብለን ማዳመጣችን፣ ከለበስነውና ከተጫማነው ይልቅ ሮጥ ሮጥ ብለን የመሥራታችን ነገር ጎልቶ እንዲታይና እንደሚሰማ ብናደርግ!

ያንን ማድረግ የምንችለው ታድያ ባለሐሳቧን እህታችንን ‹በርቺ!› ስንላት ነው። ውበትን አንጠብቅ ማለት አይደለም፣ ግን ከዛ የሚቀድም ብዙ ነገር እንዳለና አንዲት ሴት ለዐይን ከሚቀርብ ውበት በላይ መሆኗን መገንዘብ ይገባል። ድምጻዊ ጌቴ አንለይ ‹መልክሽን አይበልጥሽም› በሚለው ሙዚቃው እንዳወሳት ገጸ ሰብእ፣ እህቶች! መልካችን አይበልጠንምና እንዲበልጥ አንፍቀድ!
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014ቹ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here