የ2015 በጀት ባነሰ ወጪ ብዙ ሥራ ለማከናወን በሚያስችል መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ

0
700

የፌዴራል መንግሥት የ2015 በጀት ባነሰ ወጪ ብዙ ሥራ ለማከናወን በሚያስችል ጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ ማዕቀፍ በመመራት እየተዘጋጀ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።
የ2015 በጀት በጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ ማዕቀፍና የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ባገናዘበ መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑ ነው የተነገረው።

በዚህም 170 የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በተሰጣቸው የበጀት ጣሪያ መሠረት የ2015 በጀታቸውን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አቅርበዋል ተብሏል።
የበጀት ዝግጅቱ ስትራቴጂያዊ ለሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማዕድን፣ ለቱሪዝምና ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን የጠቆመው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ከመደበኛ በጀት ላይ እስከ 40 በመቶ የሚሆን ቅናሽ እንደሚደረግ ተብራርቷል።

የበጀት ጉድለትን በተመለከተም ከውጭ የሚገኘው ሀብት በታሰበው መጠን ላይገኝ ስለሚችል መንግሥት ከአገር ውስጥ ከሚመነጨው ሀብት ማለትም ከግምጃ ቤት ሰነድና ከሌሎች የአገር ውስጥ ምንጮች ለማሟላት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነድፎ ተግባራዊ በማድረጉ አበራታች ውጤት በመገኘቱ የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ግሽበትን በማያባብስ ሁኔታ ለማሟለት ጥረት ይደረጋል ነው የተባለው።

በ2015 በጀት ዓመት አዳዲስ ካፒታል ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደማይደረጉ እና ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የካፒታል ፕሮጀክቶች በአነስተኛ ወጪ በትጋት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እንዲቻል የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የ2015 በጀታቸውን ባስገመገሙበት ወቅት ጥብቅ መመሪያ እንደተሰጣቸውም ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here