ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ ድርጅቱ አሳሰበ

0
1094

በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ አሠራሮች ካልተወገዱና የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠ የዋጋ ግሽበቱና ኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሔ እንደማይገኝለት የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አስታወቀ።
ድርጅቱ የኑሮ ውድነቱ እና የዋጋ ግሽበቱ ለአገር አደጋ የደቀነ በመሆኑ በዚያው ልክ ተገቢ መንግሥታዊ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል።

መንግሥት በንግድ እና በገቢ ስርዓቱ ላይ የሚታየውን ሕገ ወጥነትና የሕግ የበላይነትን የሚጻረሩ ተግባራትን በአግባቡ በማጤን የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ያለው ድርጅቱ፣ በአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ የቀሰቀሱት ጦርነትና አለመረጋጋት ለኑሮ ውድነቱ ያለው አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ፣ ኮቪድ ወረርሽኝ፣ የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈጠሩ ዓለማቀፍ ሁኔታዎችም ለዋጋ ግሽበቱና ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል ሲል አመላክቷል።

ድርጅቱ አክሎም አገራችን ነጻ ገበያ ብትከተልም ደላላውን ከግብይት ሰንሰለት ማውጣት፣ ጊዜያዊ የትርፍ ሕዳግ ማዘጋጀት እንዲሁም የቤት ኪራይ ተመን መውጣት አለበት ነው ያለው።

ሸማቹ፣ አምራቹና መንግሥት ወይም አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት በገበያው ሊፈታ ይገባል ሲሉም አሳስቧል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ እንዳስታወቀው፣ የሚያዝያ ወር 2014 ከአምስት ዓመት ወዲህ ከፍተኛ የተባለው አጠቃላይ የዋጋ ግሸበት የታየበት ወር ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here