ብሪታኒያ ዜጎቿ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክሯን አስተላለፈች

0
656

የብሪታኒያ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩም ሆነ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚያመሩ ዜጎቹ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከደኅንነት ስጋት ጋር በተያያዘ እንዳይዘዋወሩ አስጠንቅቋል። ማስጠንቀቂያውም አምስት ክልሎችን ያካተተ ሲሆን ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሱማሌ እና ጋምቤላ ናቸው።

የውጭ እና ኮመን ዌልዝ (common wealth) ቢሮ ይፋ እንዳደረገው በጋምቤላ ክልል አራት ወረዳዎች እና ከደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ድንበር ዐስር ኪሎሜትር ድረስ መቅረብ እንደሌለባቸው አስጠንቅቋል። በሱማሌ ክልል ጃር ጃር፣ ቆራሔ እና ደሎ የተባሉ አካባቢዎችን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በምትዋሰንበት የሱማሌ ክልል 100 ኪሎ ሜትር መራቅ እንደሚኖርባቸውም አሳስቧል። በትግራይ ክልልም ከኢትዮ- ኤርትራ ድንበር ዐስር ኪሎ ሜትር እንዲሁም ደብረ ዳሞ እና የሓ የጎብኝዎች መዳረሻዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ ሲል አስጠንቅቆ፥ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ፀገዴ፣ ምዕራብ አርማጭሆ እና ታች አርማጭሆ አካባቢዎች ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ ዜጎቹን አሰጠንቅቋል።

ቢሮው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞን ከአዲስ አበባ ጋምቤላ ከሚወስደው ዋና መንገድ ውጪ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት እንዳለ ይፋ አድርጓል።

መግለጫው በየዓመቱ ከአገረ እንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ እስከ 20ሽሕ የሚደርሱ ጎብኝዎች እንደሚመጡ ገልፆ ኹሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ጉብኝቶች ከችግር እና ከደኅንንት ስጋት የፀዱ እንደነበሩና አሁንም ዜጎች ችግር እንዳይገጥማቸው ቅድመ ጥንቃቄ መውሰድ ጠቃሚ እንደሆነ አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here