መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናባለሥልጣኑ የገባውን ቃል አልፈጸመም ተባለ

ባለሥልጣኑ የገባውን ቃል አልፈጸመም ተባለ

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ እየደረሰበት ያለውን ጉዳት በማስመልከት ለጉዳቱ መከሰት ምክንያት የሆኑ ክፍቶችን ለማሟላት ቃል ቢገባም አለመፈጸሙን የፓርኩ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የፓርኩ ሠራተኛ ተቋሙ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳው አመራሮች፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር ሚያዚያ 1/2014 ጉዳት እየደረሰበት ላለው ለቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ አራት መሠረታዊ ነገሮች ለማድረግ ቃል ቢገባም አልፈጸመም ብለዋል።
ይሟላሉ ተብለው ከነበሩት አራት መሠረታዊ ነገሮች አንደኛው መጠኑ ባይገለጽም ለፓርኩ የሚያስፈልገው በጀት እንደሚበጀት ነው። ያም እንዳልተሰጣቸውና ወረዳው አቅም ስለሌለው ይህንኑ በጀት በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በጦርነቱ ምክንያት ከ70 በላይ የፓርኩ የጥበቃ ሠራተኞች መበተናቸውን ተከትሎ በስብሰባው ወቅት በኹለተኛ ደረጃ ይፈጸማል ተብሎ የነበረው የሠራተኞች ቅጥር እንደሆነም ተጠቅሷል።
ፓርኩ 130 ሠራተኞችን ይሠራ ነበር የሚሉት ሠራተኛው፤ በስብሰባው ወቅት ቢያንስ 30 ሠራተኞች እንደሚቀጠሩ ቃል ቢገባም እስከ አሁን ምንም የተደረገ ነገር የለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የፓርኩ ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ በገለጹት መሰረት፣ በጦርነቱ ምክንያት ከተበተኑት መካከል አገልግሎት የሚሰጡት ስምንት የጥበቃ ሠራተኞች ብቻ ሲሆኑ፤ የፓርኩ ከግማሽ በላይ ሄክታር ደን እንደተመነጠረና የአካባቢው አርሶ አደር ለማረስ ዝናብ እየተጠባበቀ ነው።
ለደኑ መመንጠር ምክንያትም የጥበቃ ሠራተኞች በመበተናቸው ፓርኩ ለኹለት ዓመት ባለቤት አልባ ስለሆነ ነውም ተብሏል።

ሦስተኛው ለፓርኩ ይሟላል ተብሎ የነበረው ቁስ ተሽከርካሪ መሆኑን የፓርኩ ሠራተኛ የተናገሩ ሲሆን፤ አንድ መኪና እንደተገዛና አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር የጉዞ ሙከራ ተደርጎበት እንደሚሰጣቸው ተነግሯቸው እየጠበቁ ነበር። ሆኖም ግን አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር እስከሚጓዝ እየጠበቁ ቢቆዩም ድርጅቱ “አይ መኪናውን መስጠት አንችልም። ለጊዜው እዚህ ይቆይ ብለው ከለከሉን” ሲሉ ተናግረዋል።

በስብሰባው በተደረገው ውይይት መሠረት ብሔራዊ ፓርኩ ቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ከተሰኘ ነባር መጠሪያ ሥም ወደ ‹‹ቃብትያ ሁመራ ብሔራዊ ፓርክ›› ቅያሬ እንደሚደረግለት ስምምንት ላይ ቢደረስም፣ እስከ አሁን የተቀየረ ነገር የለም ነው የተባለው።
በስብሰባው ከላይ የተዘረዘሩትን አራት መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማሟላት ስምምነት ላይ ቢደረስም፣ ኹለት ወር ሊሞላ ቀናት እየቀሩት ምንም ነገር ሳይደረግ መቆየቱና ስልክ ሲደወልም እሺ ከማለት ውጭ መሬት ላይ ጠብ ያለ ድርጊት አለመኖሩ ፓርኩን ለመታደግ የሚታገሉ ቀሪ የጥበቃ ሠራተኞች ላይ ቅሬታ አሳድሮባቸዋል።

በመሆኑም ይበልጥ ማልማት ተገቢ ሆኖ እያለ ሕገ ወጥ አደኑ፤ የደን ምንጠራው እንደተባባሰና ፓርኩ እየተራቆተና እንስሳቱ እየተሰደዱ መሆናቸውን በማየት የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጥበት ጥሪ ተላልፏል።
ቅሬታውን በተመለከተ ከዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር እንደተነጋገሩና፣ አራቱንም መሠረታዊ ጉዳዮች ተፈጻሚ ለማድረግ አንድ ቡድን በጉዞ ላይ መሆኑን የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አብርሃም ማርዬ ምላሽ ሰጥተዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ባስነበበቻቸው እትሞቿ ጥበቃ ባለመኖሩ፤ ሕገ ወጥ አደን በመስፋፋቱ፤ ወቅቱ ሙቀት የሚበረታበት በመሆኑ ከ300 በላይ ዝሆኖች ወደ ኤርትራ መሰደዳቸውንና የአካባቢው አርሶ አደር ደኑን እየመነጠረው መሆኑን መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች