ግብፅ የሕዳሴው ግድብ ይፈርሳል ማለቷን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ‹ሟርት ነው› ሲሉ አጣጣሉት

0
612

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሾክሪ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ከኢትዮጵያ አቻቸው ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ተወያዩ፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ አዲስ አበባ የተገኙት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግድቡ ግንባታ ላይ ከኢትዮጵያው አቻቸው ጋር ያደረጉት ውይይት በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ተገልጿል፡፡ በሁለቱ አገሮች የተቋቋመው ብሔራዊ ገለልተኛ የጥናት ተቋም ሥራ በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ መመካከራችውን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አሕመድ ሀፈዝ ገልፀዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ዙሪያ የተቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን ሪፖርት ላይም ባለፈው መስከረም ወር ላይ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ መወያየታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ግድቡ በግብፅ ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ማረጋገጫ የሚሆናትን ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር መፈራረም እንደምትፈልግ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አበዱልፈታህ ኤል ሲሲ መግለፃችው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ የጎላ ተፅእኖ እንደማያደርስ በተደጋጋሚ ስትገልፅ ቆይታለች። ነገር ግን የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የግብፅ የውሃ ሃብት ጥናትን ዋቢ በማድረግ ግድቡ በቅርብ ዓመታት ሊፈርስ እና የጎርፍ አደጋ በሱዳንና ግብፅ ላይ ሊያስከትል ይችላል ብለው መተንበያቸውን ‹ኢጂፕት ኢንድፔንደንት› ባለፈው ወር ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡ አቶ መለስ ዓለም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባለፈው ሳምንት ከአዲስ ማለዳ ባቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ትንበያው ከሟርት ያልዘለለ ተራ ወሬ ነው›› በማለት አጣጥለውታል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here