ሄሎ ቤል ለኢትዮጵያ ገበያ በአይነቱ ለየት ያለ የሞባይል መተግበሪያና የኢኮሜርስ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው። ቤል ካሽ የተንቀሳቃሽ ስልክን በመጠቀም አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን ሄሎ ብራንድ ስር ከሚጠቃለሉት እንደ ሄሎ ካሽ፣ ሄሎ ዶክተር፣ ሄሎ ደላላና ሄሎ ገበያ በተጨማሪ ሄሎ ማርኬትና ሄሎ ሾፕ የሚባሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመጀመር ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ሄሎ ማርኬት በአገር ውስጥ የሚገኙ ገዢና ሻጮችን የዩኤስኤስዲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚያገናኝ መተግበሪያ ሲሆን የክፍያ ሂደቱ ሄሎ ካሽን በመጠቀም ይከናወናል። ሄሎ ሾፕ ደግሞ ለውጪ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን ኢንተርኔትንና ክሬዲት ካርድን በመጠቀም በውጪ አገር ለሚገኙ ሸማቾች አገልግሎት ይሰጣል። የሄሎ ሾፕ ዳይሬክተር የሆኑት ሶስና ሸዋንግዛው እንደገለጹት ሁለቱ ምርቶች ታህሳስ መጨረሻ ላይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ።
ዳይሬክተሯ ሁለቱ ምርቶች ወደ ገበያ ለመግባት ካሰቡበት ጊዜ መዘግየታቸውን ገልጸው ለዚሁም በአገራችን በኢኮሜርስ ዙሪያ ፖሊሲና ‹ፕሮሲጀር› አለመኖርን እንደ ምክንያት አንስተዋል። በተጨማሪም የኤሌክትሮኒክስ ግብይት የሚባለው ስርዓት ለኢትዮጵያ አዲስ መሆኑ እንዲሁም ሄሎ ሾፕ ሥራውን ለመጀመር ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ ባሰቡት ጊዜ ወደ ገበያ እንዳልገቡ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።