“አድብቶ ገዳዮቹ” ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች

0
1231

እምብዛም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ሲሠራባቸው የማይስተዋሉት ነገር ግን እንደዘበት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በመዲናችን ሕዝብ በብዛት በሚተላለፍበት አደባባዮችና ጎዳናዎች ጥግ ይዘው በሚኒባስ ከወጪ ወራጁ እርዳታ የሚያሰባስቡ የኩላሊት፣ የደም ካንሰር ወይም የልብ ሕሙማንን መመልከት የተለመደ ነው። እነዚህና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በዓለማችን ለሚከሰቱ ከ70 በመቶ በላይ ሞቶች ምክንያት ናቸው። በኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከኑሮ ዘይቤና አኗኗር ለውጥ ጋር ተያይዞ ለእነዚህ በሽታዎች ተጋላጭነት እንደጨመረ ጥናቶች ያመለክታሉ።

የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ስለተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምንነት፣ በኢትዮጵያ አጋላጭ ሁኔታዎችና የስርጭት ደረጃ እንዲሁም የመፍትሔ አማራጮችን ጥናቶች በማገላበጥና የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች በማናገር የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

በየመንገዱና ጎዳናው ከምናየውና ከምንሰማው ብዙ ታሪክ መካከል ተከታዩ አንዱ ነው። እርሷ፤ ነገን ለማየት አብዝታ የምትጠብቅ ወጣት ልጅ ናት፤ ዓይናለም አበራ (ስሟ የተቀየረ)። ከዕለታት በአንዱ ቀን ከየት መጣ ያላሉት የሕይወት ዳገት በእርሷና በቤተሰቧ ፊት ዱብ አለ። የኩላሊት ሕመምተኛ መሆኗን እና በቶሎ ሕክምና ካላገኘች ወደ ሞቷ በፍጥነት እንደምትቀርብ ተነገራት። ከፍሎ ለማሳከም አቅም የሌላቸው ቤተሰቦቿ ከሚኖሩበት ወረዳ የኑሮ ደረጃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ አስጽፈው “ለኩላሊት እጥበት የሚውል ገቢ በተሸከርካሪ እየለመንን ለማሰባሰብ አቅደናልና ፈቃድ ስጡን” ሲሉ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት አቤቱታቸውን አስገቡ።

አልተከለከሉም፤ ኹለት መኪናዎችን ይዘው እንዲወጡና ከማለዳው 3 ሰዓት ጀምሮ በየቀኑ ለአንድ ወር ያህል ብቻ ገቢ እንዲያሰባስቡ በሌላ አገላለጽ ልመና እንዲወጡ ፈቃድ ተሰጣቸው። አንድ ቀን በሕይወት ላይ ለመጨመር፣ ከገንዘብ ጋር ቀን እየቆጠሩ ለመኖር በድምጽ ማጉያው አላፊ አግዳሚው ‘የእርዳታ ጥሪ’ እየተባለ በእንጉርጉሮ በታጀበ ድምጽ እና ከጀርባ እንዲሁም ራሳቸውን ችለው በሚለቀቁ ሆድ በሚያላውሱ፣ ትብብር በሚጠይቁ ዘፈኖች ይቀሰቀሳል። ያውም ሰው በርህራሄ ከሚሰጠው አንድ ብር ላይ ሰላሳ ሳንቲም ብቻ ለማግኘት፤ የቀረው ለመኪና፣ ሞንታርቦ ክራይና መሰል ቋሚ ወጪዎች ስለሚውል።

እንዲህ ያሉ ከኩላሊት ሕመም ጋር የተያያዙ ታሪኮችን መስማት ከጀመርን ውለን አድረናል። ይህም ብቻ አይደለም መንገድ ላይ፣ በተቋማት ውስጥ እንዲሁም በየቤቱ በድንገት ከንበል ብለው ወድቀው በዛው እስከወዲያኛው የማይነሱ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። የዕድሜ ልክ በሽታ ሆኖባቸው በየቀኑ መድኀኒቶችን እየዋጡ ለመኖር የተገደዱም ጥቂቶች አይደሉም። ይህም በአንድ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ጫናው ለአገር የሚተርፍ ነው። ለዚህ ሁሉ ምክንያት የሆኑት ደግሞ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሆነው ተገኝተዋል።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥያሜያቸው ከግብራቸውና ከተፈጥሯቸው የተወለደ ነው። እነዚህ በሽታዎች በንክኪ ወይም በሽታ አምጪ በሆኑ ህዋሳት ከሰው ወደ ሰው አይተላለፉም። ይህንን የነገሩን በጎንደር ሕክምና ሳይንስ የውስጥ ሕክምና ክፍል ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ፤ መምህርት፣ ሐኪምና ተመራማሪ፤ ምርምሮቻቸውንም በኤች አይ ቪ ኤድስ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የሠሩት ፕሮፌሰር ሽታዬ ዓለሙ ናቸው። ሽታዬ እንደሚሉት እነዚህ በሽታዎች በንክኪ ከሰው ሰው አይተላለፉ እንጂ በዘር ሊተላለፉ የሚችሉ ናቸው።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ታድያ እጅግ በርካታ በመሆናቸው በቁጥርም ሆነ ዘርዝሮ ለመጨረስ አታካች ናቸው። ብዛታቸውን በዋና ዋና ክፍሎች ሰብሰብ አድርጎ ለማጥናት፣ ለመመርመርና መፍትሔ ለመፈለግ ይረዳ ዘንድ የዓለም ጤና ድርጅት አንድ መላ ዘይዷል። ይህም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአራት ዘርፍ ተከፋፍለው እንዲታዩ እንዳስቻለ ሽታዬ ይገልጻሉ።

እነዚህም የስኳር በሽታ፣ የልብ እና የደም ሥር በሽታዎች፣ ተከታታይነት ያለው የመተንፈሻ አካል በሽታ እና ካንሰር ናቸው። በዚህ መሰረት ይዘርዘሩ እንጂ በያንዳንዳቸው ሥር በርካታ በሽታዎችን መጥቀስም ይቻላል፤ ሊድኑ ከሚችሉት አንስቶ ፈጽሞ መድኀኒት እስከሌላቸው ድረስ።

በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላ፣ እነዚህ በዋናነት የተቀመጡ አራቱ ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ዓይነቶች ትኩረት ያገኙት በጠቅላላው ካሉ ተላላፊ በሽታዎች መካከል 71 በመቶ ድርሻ ስለሚይዙ ነው ብለዋል። በተጨማሪም በዓለማችን ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል 70 ከመቶ የሚጠጉት በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰቱ ሲሆኑ ከዚህም 85 በመቶ የሚደርሰው ሞት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚታይ ነው።

ኩኑዝ በዋናነት በሚከታተሉት የካንሰር ሕመም ማሳያነት ሲያነሱ፤ ካንሰር ከእነዚህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ውስጥ 6 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይጠቅሳሉ። ከዚህም ውስጥ ደግሞ ሃምሳ በመቶውን የጡት፣ የማሕጸን ጫፍ እና የአንጀት ካንሰር ይይዛሉ። የካንሰር በሽታዎች ለማዳን አዳጋች ከመሆናቸው በተጓዳኝ ብዙውን ጊዜም የበሽታው ተጠቂዎች ወደ ሕክምና አርፍደው የሚሔዱ በመሆናቸው ጥሩ ውጤት ለማግኘት እንደማያስችል ጠቅሰዋል።

“በዓመት ውስጥ 67 ሺሕ ሰዎች በአዲስ ካንሰር ሕመም ይያዛሉ” ያሉት ኩኑዝ፤ ወደ ሕክምና ዘግይቶ መምጣት፣ የሕክምና ተቋማት ዝግጁ ባለመሆን፣ የሠለጠነ ባለሙያና መሣሪያ እንዲሁም መድኀኒት ባለመኖሩ ሞቱ ከፍ እንዲል ሆኗል። ይህን በቅርበት የሚከታተሉት በመሆኑ ጠቀሱ እንጂ ስኳር፣ ከደም ሥር ጋር የሚገናኙ እንደ ደም ግፊትና እሱን ተከትሎ የሚመጡ በሽታዎች እንዲሁም አስም እና መሰል ከመተንፈሻ ጋር የተገናኙ በሽታዎች በዓለም ዐቀፍ ደረጃም በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍተው ይገኛሉ።

አንዳንዶቹ የበሽታ ዓይነቶች በጊዜ ከተደረሰባቸው የሚድኑ ቢሆኑም እንደተባለው ወደ ሕክምና ዘግይቶ መሔድ የመዳን ዕድሉን ያጠበዋል። ከግንዛቤ፣ ከቸልታ እንዲሁም ከምርመራ ወጪና መሰል ምክንያቶች የተነሳ ሕመም ካልተሰማው በቀር ወደ ሕክምና የሚሔደው የማኅበረሰብ ክፍል ጥቂት ነው። ሽታዬ እንደሚሉት ደግሞ ጭራሹን በሽታዎቹ ከፍተኛ ደረጃ ካልደረሱ በቀር ምልክት አያሳዩም። “በዘራችን ስኳር የለም የሚሉ 100 ሰዎች ቢመረመሩ ቢያንስ 10 ሰው ስኳር በሽታ ይገኝበታል።” ያሉት ሽታዬ ሕመም የሌለው መሆኑ እንደሚያዘናጋ አውስተዋል።

ለምን “የሀብታም” በሽታ ተባሉ?
እነዚህን በሽታዎች የሕክምና ባለሙያዎችን ተከትሎ መንግሥት “ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች” የሚል ሥያሜ ባይሰጧቸው ኖሮ ምናልባት ማኅበረሰቡ ‘የሀብታም በሽታ’ ሲል ይጠራቸው እንደነበር አያጠራጥርም። ኩኑዝ በበኩላቸው ይህ አንዱ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው ብለዋል። እንኳን ማኅበረሰቡ በመንግሥት ደረጃም ጥናቶች አቅጣጫ እስኪያሳዩ ድረስ በሽታዎቹ ትኩረት ሳይሰጣቸው እንዲቆይ ያደረገው ይኸው በሽታዎቹን የሀብታም ብሎ በማሰብና በአዳጊ አገር አይከሰትም ብሎ በመገመት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ታድያ ማኅበረሰቡ እነዚህን በሽታዎች የሀብታም በሽታ ማለቱ ለዝንጋኤ ቢዳርገውም እንደዛ ለማለት ግን ምክንያት ነበረው። ይህም በሽታዎቹ ብዙውን ጊዜ ባደጉ አገራት መከሰታቸው እንዲሁም ለሕክምናም ብዙ ወጪ የሚያስወጡ፣ በዘላቂነት ክትትል የሚፈልጉ በመሆናቸው ነው። በተመሳሳይ ሽታዬ በዚሁ ሐሳብ ላይ ሲያክሉ፤ በሽታው በአብዛኛው ባደጉ አገራት መታየቱ በአዳጊ አገራት ሊኖር የሚገባውን ትኩረት እንዳዘገየው አውስተዋል። አሁን ላይ ግን እንደዛ አይደለም፤ በሽታዎቹ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ እንዲሁም አዳጊ የተባሉ አገራት ሰው እየጨረሱ ነው።

“በሠለጠኑ አገራት ነገሩ ቶሎ ታውቆ አሁን እየቀነሰ ነው፤ መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ደግሞ ሳይቀንስ ሳይጨምር ተደላድሎ አለ። ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ባሉ አገራት ግን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው፤ ምክንያቱም አጋላጭ ሁኔታው በዝቷል” ሲሉ ሽታዬ ገልጸዋል።

ኩኑዝ በበኩላቸው፤ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ላይ እነዚህ ተላላፊ ያልሆኑት ታክለው አዳጊ አገራት ላይ ጣምራ ችግር ተፈጥሯል ባይ ናቸው። እናም እነዚህ በሽታዎች ሀብታም ደሃ ብለው የማይመርጡ መሆናቸው ላይ ግንዛቤ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የበሽታዎቹ መነሻ ምክንያት አንዳንዴ በግልጽ ያልታወቀ አንዳንዴ ደግሞ ብዙ ሆኖ ይገኛል። ይህን የተመለከተው የዓለም ጤና ድርጅት ተጋላጭ የሚያደርጉ ናቸው ያላቸውን ዋና ዋና አራት አጋላጮች፤ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል አለአግባብ መጠቀም፣ የአመጋገብ ችግር እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ሲል ዘርዝሯል። እነዚህን መዘርዘር ያስፈለገውም በሽታዎቹን ቀድሞ በቀላሉ ለመከላከል እንዲቻል ታስቦ እንደሆነ ሽታዬ ጠቁመዋል።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ እነዚህ በሽታዎች ትኩረት ያገኙት በቅርብ ጊዜ ነው። ይህም መሆኑን ኩኑዝ ሲያብራሩ፣ ትኩርት የተሰጠው ከረጅም ጊዜ ተሞክሮ በኋላ መሆኑንና ከዛ ቀደም የጤና ፖሊሲው ተላላፊ በሽታዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች በዓለምም ሆነ በአገራችን ደረጃ በሽታዎቹ የሚያደርሱት ጉዳት እየሰፋ መምጣቱን በማመላከታቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ትኩረት ሊስቡ ችለዋል።

“ፖሊሲ በጥናትና መረጃ ይደገፋልና መረጃዎች ሲጠናቀሩ እነዚህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም ችግራችን መሆናቸው ታይቷል።” ያሉት ኩኑዝ፤ የተገኙት መረጃዎች የትኩረት አቅጣጫ ሊያስቀይሩ እንደቻሉ ጠቅሰዋል። ለዚህና ይህንን ተከትሎም ታድያ የተለያዩ ጥናቶች ከዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም ከራሱ ጤና ሚኒስቴር ይፋ ተደርገዋል።

በኢትዮጵያም የኑሮ ዘይቤና አኗኗር መቀየሩ ተጋላጭ ሁኔታዎችን እንደጨመረ ሽታዬ በአንክሮ አንስተዋል። ለውጥ የሚጠላ ባይሆንም በተለይም ከተሜነት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ይታያል፤ ኬክ ቤቶች በየቀኑ መከፈታቸውና ወጣቶች ጣፋጭ ኬኮችን ከለስላሳ መጠጦች ጋር ሲመገቡ በብዛት መታየታቸውን ያነሳሉ። ሥጋ ቤቶች ሰው ሞልቶ ቁርጥ ሲበላ የሚውልባቸው ሆነው መታየታቸውንም እንዲሁ አያይዘው አንስተዋል።

ምንም እንኳ መንግሥት በመገናኛ ብዙኀን ያለውን የመጠጥ ማስታወቂያ ማገዱ መልካም የሚባል እርምጃ ቢሆንም፤ ሰዉን ‘ጠጪ’ ከመሆን አላገደውም። በየመጠጥ ቤቱ በርካታ የቢራ ጠርሙሶች ከፊታቸው ጠረጴዛ ላይ ደርድረው እንደኩራት ሲያዩት የሚታዩ ሰዎች ይህንን ያስመሰክራሉ፤ እንደ ሽታዬ ዕይታ።

በተጨማሪ አጋላጭ ከተባሉ ሁኔታዎች መካከል ሲጋርን በተመለከተ ብዙ አጫሽ ባይኖር እንኳ ያሉት በብዛት የሚያጨሱ መሆናቸው፣ የቂቤ ዋጋ መናር የሚያሳብቀው የቂቤ ፍላጎትና ተጠቃሚነት መጨመር፣ ፒዛ እና በርገር ቤቶች መበራከታቸው ከዘመናዊነት ይልቅ አደገኝነቱ እየጨመረ መሆኑን ልብ ማለት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ከዚህ ብዙም ሳይርቅ ሞባይል ላይ ዓይናቸውን ተክለው የሚውሉ፣ ፀሐይ ወጥታ እስክትገባ ፊልም በመመልከት የሚያሳልፉ ልጆችና ወጣቶች፣ ጫት የሚቅሙ እና አሺሽ የሚያጨሱ እንዲሁም ቢሮ ውስጥና በየቤታቸው ቁጭ ብለው የሚውሉ ሰዎች ተጋላጭ ከመሆናቸው በላይ መብዛታቸው ያሳስባል ብለዋል። በዚህ ጥንቃቄ ጉድለት ውፍረት ሲከሰት አብረውና ተያይዘው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዱካቸውን ማሳረፋቸው አይቀርምና።

የዓለም ጤና ድርጅት ከቀናት በፊት አንድ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁትን አንድ ጥናት ይፋ አድርጎ ነበር። ይህም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልባቸው መንገዶቸ ዙሪያ የተሠራ የ15 ዓመት የኢንቨስትመንት ጥናትን ያካተተ ነው።

በዓለም ጤና ድርጅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኦፊሰር ዶክተር አስማማው በዛብህ ይህንን እና ሌሎች ተያያዥ ዘገባዎችን መሠረት አድርገው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ በዓለም በዓመት ከሚሞተው 57 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 41 ሚሊዮን ለሚሆነው ሞት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ሲሆኑ፤ ከዚህም ውስጥ 80 በመቶ በአራቱ ዋና ዋና በሽታዎች ይያዛል።

በኢትዮጵያ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 የተደረገውን እንዲሁም ከ2016 ጀምሮ የተሰበሰበውን አገር ዐቀፍና ዓለማቀፍ ጥናት መሠረት አድርጎ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው ዘገባ መሠረት ደግሞ፤ 51 በመቶ ሞት በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት ይከሰታል።

በኢትዮጵያ ታድያ በእነዚህ በሽታዎች ላይ በትኩረት መሠራት የተጀመረው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2013 ነው። በዚህ ውስን ዓመት በተያዘ የአምስት ዓመት ዕቅድ መሰረት ስኬታማነት የታየባቸው ለውጦች እንዳሉ ግን ዶክተር አስማማው ገልጸዋል። ይህም በቀዳሚነት በመከላከል ላይ የተደረገ ነው።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለምን ተፈሩ?
እነዚህ በሽታዎች ከሰው ሰው በቀጥታ የሚተላለፉ አይደሉም እንጂ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡና ቋሚ ክትትል የሚፈልጉ በመሆናቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአገርና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ጫና ማስተላለፋቸው አልቀረም። በአንድ ወገን በቅድሚያ ሥጋት የሚሆኑት ለታማሚ ግለሰብ ቢሆንም፤ ከፍ ሲል መዘዛቸው ለአገርም ጭምር የሚተርፍ ነው።

ሽታዬ እንዳሉት፤ እንደ ስኳር ያሉ በሽታዎችና ሌሎቹንም ተያይዘው የሚመጡ ጉዳቶች ለግለሰቦች በጣም ከባድ ናቸው። ይህም ከዓይነ ስውርነት ጀምሮ ሰውነትን ማዘዝም ሆነ ማንቀሳቀስ አለመቻል፣ ተያይዞም የኩላሊት መሥራት መቆምና መሰል በሽታዎች ይከሰታሉ። ይህ የግለሰቦች ፈተና ይሁን እንጂ የሕመሙ ተጠቂዎች ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በታች መሆኑ ለአገር ሌላው የራስ ምታት ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ያደረገው ጥናት አንዱ ዓላማ በሽታዎቹ የሚያስከትሉትን ኪሳራ ማሳየትና በተቋማት መካከል ቅንጅት ተፈጥሮ መከላከል እንዲቻል ማመላከት ነበር። ይህንንም መሠረት አድርገው ዶክተር አስማማው፤ “አጋላጭ የተባሉት ምክንያቶች ከኢኮኖሚ ጋር ይያያዛሉ። አልኮል በራሱ ብዙ ብዙ የሰው ኀይልና ገንዘብ የያዘ ነው፣ ትንባሆም እንደዛው። በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ጫትም እዚህ ጋር ይካተታል። እነዚህ የኢኮኖሚ ፍላጎት አላቸው። ይህንንም የጤናው ዘርፍ ብቻውን ሊከላከል አይችልም። ስለዚህ በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት የሚደርሰውን ጥፋትና ኪሳራን በማሳየት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ብንከላከልና ብናክም የምናወጣው ብር እና ሳናክም ብንተዋቸው የምናወጣው ብር ምን ያህል ይሆናል የሚለው በጥናቱ ታይቷል።”

እርግጥ ነው! ሁሉም ሰው ሊረዳው በሚችለው መጠን የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች ብቻ ብናነሳ እንኳን ለመንግሥት ዳጎስ ያለ ገቢ ከሚያስገኙ ተቋማት መካከል ናቸው። በ2011 በጀት ዓመት ከፍተኛ ገቢ ካስገኙና በገቢዎች ሚኒስቴር ዕውቅና እና ሽልማት ካገኙት መካከልም እነዚሁ የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች ይጠቀሳሉ። ጥናቱ ታድያ በአንጻሩ የሰዎችን ሕይወት በቀላሉ ለመታደግ በሚቻልበት እንደሁም በዘርፉ የሚከሰተውን የሀብት ብክነት ለማስቀረት አቅጣጫ የሚያሳይ እንደሆነ ነው አስማማው የገለጹት።

በትርፍ በምትመራ ዓለም፣ በአንድ ወገን አልኮል ላይ ያለው የኢኮኖሚ ፍላጎት ሲታይ በአንጻሩ በጤና ላይ የሚያደርሰውን ኪሳራም አብሮ ማመዛዘን ያስፈልጋል። ይህም በዓመት እንደ አልኮል መጠጥ ባሉ አጋላጮች በሚከሰቱ በሽታዎች ምክንያት የሚደርሰውን ኪሳራ በማሳየት ‹በሽታዎችን መከላከል ነው ማከም የሚያዋጣው› የሚል ጥያቄ ለማንሳት ያስገድዳል።

የዓለም ጤና ድርጅት ያደረገው ጥናት ታድያ ይህንኑ ያመላከተ ነው። በተለይም በ2016 የተሰበሰቡ መረጃዎች ግብዓት ሆነው በተገኘው ውጤት አራቱ በሽታዎች ምክንያት ብቻ ኢትዮጵያ በዓመት ውስጥ 31 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ አሳይቷል። ይህም ከዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ከሚገኘው ገቢ ውስጥ 2 በመቶ ድርሻ ይይዛል። ይህ ለአንዲት አዳጊ አገር ምን ማለት እንደሆነ ሳይታለም የሚፈታ ነው።

እናስ “ይህ 31 ቢሊዮን ብሩ በምን በምን መንገድ የጠፋ ነው?” አስማማው ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ ከዚህ ገንዘብ መጠን 86 በመቶ ቀጥተኛ ያልሆነ ወጪ ሲሆን የቀረው 14 በመቶ ሰዎች ወይም መንግሥት በድምሩ በተለያየ መንገድ ለሕክምና ያወጡት ነው። 86 በመቶው ውሰጥ ደግሞ ትልቁና 47 በመቶ የሚሆነው የበሽታው ተጠቂዎች በሥራ ላይ ቢገኙም የሥራ አቅማቸውና ውጤታማነታቸው በመቀነሱ ምክንያት የሚደርስ ኪሳራ ነው።

ቀጥሎ ከ60 የዕድሜ ክልል በታች በሚከሰት ሞት ምክንያት የሚደርስ ኪሳራ ሲሆን ይህም 35 በመቶ ይይዛል። በአንጻሩ ሥራ ባለመግባት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጫና የሚፈጥረው 4 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው። ይህ ሁሉ ሲደማመር እነዚህ በሽታዎች ለአገር ሥጋት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

ታድያ ኢትዮጵያ በቀጣይ 15 ዓመት መከላከል ላይ ብትሠራ 1.4 ሚሊዮን ዜጎችን ሕይወት መታደግ ሲቻል፤ ይወጣ ከነበረው ወጪ 62 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ማትረፍ ይቻላልም ተብሏል። ነገሩ ሒሳብ ይመስላል። አስማማው ተከታዩን ማሳያ ያቀርባሉ፤ አንድ ሰው በቀን ከ5 ግራም በታች ጨው እንዲጠቀም የዓለም ጤና ድርጅት ያሳስባል። ይሁንና በኢትዮጵያ 96 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በቀን ከ5 ግራም በላይ ወይም እስከ 8 ግራም ጨው ይጠቀማል። ነገር ግን መጠኑና ጥራቱ የተጠበቀ ጨው ለመጠቀም አንድ ብር ስናወጣ 3 ብር ከ30 ማትረፍ ይቻላል። በሲጋራና በአልኮል ላይ ተመሳሳይ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግም ማትረፍ ይቻላል።

መንግሥት ምን ያድርግ?
መንግሥት ለሕዝቡ ተጠያቂነት ተሰምቶት ከሚንቀሳቀስባቸው የማኅበራዊ ዘርፎች መከላከል የጤናው መስክ አንደኛው በመሆኑና ኀላፊነት ስላለበትም ሥሙ ሳይጠራ አይቀርም። በዚህም መሠረት በእነዚህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ መከላከልን ያዋጣኛል ብሎ መርጧል። ይህንንም ኩሙዛ ሲናገሩ፣ የጤና ፕሮግራሙ መሠረታዊ አካሔድ መከላከል ነው ብለዋል። “መከላከል አዋጭ፣ ተደራሽና ብዙ መዘዞችንም የሚያስቀር ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

በዚህም ካንሰርን 40 በመቶ፣ በጠቅላላ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን 30 በመቶ መከላከል ይቻላል። በጤና ስርዓቱም ሕክምና መስጠት ላይ ድክመትና አቅም ማጣት በመኖሩ መከላከል የተሻለ ሊያግዝ ይችላል ነው ያሉት። በተለይም በቀላሉ ሊድኑ እንዲሁም የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚችሉ በሽታዎች፤ ለምሳሌ የማሕፀን እንዲሁም የጡት ካንሰር በቶሎ ከተገኙና ምርመራ ከተደረገ መቶ በመቶ መከላከል የሚቻልባቸው ናቸው።

“ኢትዮጵያ በመከላከል ደረጃ የተሻለ አቅም ይኖራታል” ያሉት ኩኑዝ፤ ቀጥለውም “የጤና አገልግሎት ዝርጋታውን ስናይ የመጀመሪያ ደረጃ የሚባል ሕክምና የሚሰጡ ጤና ጣቢያዎች 4 ሺሕ ሲሆኑ በጠቅላላው ያሉ ሆስፒታሎች ከ400 በላይ አይደሉም። በአንጻሩ 16 ሺሕ የጤና ኬላዎች አሉ። ይህም ማለት ማንኛውም ጤና ነክ መልዕክት በእነዚህ መዋቅሮች መድረስ ይችላል ነው። ይህን አጋጣሚ መጠቀም ከቻልን በሽታዎቹን ቀድሞ ለመከላከል እንዲያስችል ኅብረተሰቡ ጋር መድረስ ይቻላል” ብለዋል። የሚያስፈልገውና የሚጠበቀው መልዕክቱን ማቀናበርና የማኅበረሰቡን ዕድሜ፣ ጾታ፣ አረዳድ፣ አኗኗር ሁኔታ፣ ባሕልን ያገናዘበ አድርጎ ማዘጋጀት ነው።

ዶክተር አስማማው እንዳሉት ደግሞ፤ ኢትዮጵያ በመከላከል አካሔዷ በትንባሆ ላይ የተሻለና ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጋለች። በዚህ ላይ በአፍሪካ ደረጃ የኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ልምድ የተሻለ የሚባል መሆኑንም ጠቅሰው ኢትዮጵያም ግን በጥቂት ዓመታት ውስጥ የመከላከል አካሔድን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ለሌሎች የምታካፍለው ተሞክሮ አላት ባይ ናቸው። በተለይም ከማህፀን ጋር በተያያዘ የካንሰር ቅድመ ምርመራና መከላከል ላይ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

በተያያዘ ለብዙዎች በሚታይ መልኩ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን መጥቀስም ይቻላል። የጤና ሚኒስቴር ይህንኑ አጋላጭ መንስዔ ለመከላከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲደረግ ርብርብ ማድረጉ አንዱ ነው። በአዲስ አበባ መታዘብ እንደሚቻለው በወር አንድ ጊዜ የከተማ ዋና ዋና መንገዶች ከተሽከርካሪ ፍሰት ነጻ ሆነው የእግር ጉዞዎችና እንቅስቃሴዎች እንዲደረጉ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴም በጋራ የመሥራት ባሕል እንዲለመድ ጥረት ሲደረግ ይታያል። ይህም ከአዲስ አበባ አልፎ በየአካባቢውና በክልል ከተሞች እንደሚስፋፋ ይጠበቃል።

በነገራችን ላይ የጤና ሚኒስቴር ትኩረቱ በእነዚህ አራት ዋና ዋና የተባሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ይሁን እንጂ ሌሎችም ትኩረት የሚሹ ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ትራኮማ፣ ዝሆኔ፣ ፎከት፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች፣ ብላሀርዚያ የመሳሰሉ በሽታዎች አሉ።

ማኅበራት እንደጠጠር
ትልቅ ጋን በጠጠር እንደሚደገፈው ሁሉ መንግሥት አንዳንዴ ወይም ብዙ ጊዜ በሲቪል ማኅበራት ድጋፍ በእግሩ ለመቆም ሲሞክር ይታያል። ያም ብቻ አይደለም መንግሥት ብቻውን የሚያደርገው ጥረት ብዙም ፍሬያማ ላይሆን ስለሚችል ማኅበረሰቡን የሚያሳትፉ ማኅበራት ቀላል የማይባል ድርሻን መወጣት ይችላሉ። ለዚህም የጤናን ዘርፍ እንደ አንድ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

የልብ፣ የኩላሊት፣ የስኳር፣ የካንሰርና መሰል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተመለከተ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት፣ በጎ ፈቃደኞችና ባለሀብቶች ጥቂት አይደሉም። ከመንግሥት ጋር በመደጋገፍ እንዲሁም የአገር ውስጥ የመደጋገፍ ባሕልን በመጠቀምና በማጽናት እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ ድጋፎች በማሰባሰብም ሥራውን ይሠራሉ።
የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ማኅበር የኩላሊት ሕመምተኞች የቀዶ ጥገና ዕድል እስኪያገኙ ድረስ ሕይወታቸውን ለማቆየት የእጥበት አገልግሎትን በነጻ ለመስጠት የሚጥር ማኅበር ነው። በአሁኑ ሰዓት በዘውዲቱ እንዲሁም በምኒልክ የኩላሊት እጥበትን ሙሉ ለሙሉ ነጻ ማድረግ መቻሉም በተለያዩ የዜና አውታሮች ሲሰማ ቆይቷል።

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ፤ ኩላሊትን በተመለከተ መንግሥት ትኩረት መስጠቱን መታዘባቸውንም ጠቅሰዋል። ሰለሞን የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ማኅበርን ጨምሮ በሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የሚሠሩ ማኅበራት በአገልግሎታቸው “ተደራሽነት ላይ መሠራት አለበት” ብለዋል። የኩላሊት እጥበትን መነሻ አድርገው ሲጠቅሱም፤ በፊት አገልግሎቱ አዲስ አበባ ላይ ብቻ እንደነበርና፤ አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እጥበት እንደሚሰጥ የጠቀሱት ሰለሞን፣ በየክልሉ ባሉ የጤና ሳይንስ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንዲሰጥ ሥራዎች በሒደት ላይ ናቸው ብለዋል፤ ይህ የተደራሽነት ማሳያ ነው።
እነዚህ ማኅበራት ከመንግሥት የሚፈልጉት አንዱና ቀዳሚው ነገር ግብዓት ነው፤ ሰለሞን ይህን መንግሥት ማሟላት አለበት ይላሉ። እንዲሁም ለስኳር በሽታ እንደሚደረገው ሁሉ ለኩላሊት ሕመምተኞችም በተለይም አቅም ለሌላቸው በየሆስፒታሉ ነጻ ማድረግ፤ መድኀኒቶቹ ውድ በመሆናቸው አቅም ለሌላቸውና መግዛት ለማይችሉት ነጻ መስጠት ያስፈልጋልም ብለዋል።

የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት ማኅበርን ጠቀስን እንጂ ሌሎችም እንዳሉ እሙን ነው። በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው የሕፃናት የልብ ሕክምና ልበ ቀና በሆኑት ዶክተር በላይ አበጋዝ ማነሳሳትና ብርታት ተቋቁሞ ከዓመታት በኋላ “እጅ አጠረኝ ልዘጋ ነው” ማለቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ምንም እንኳን አሁንም በመተጋገዝና ሰዉም ያለውን በማዋጣት ሕክምና ማዕከሉ ዳግም እንዲቆም ጥረት ቢደረግም ዘላቂ ገቢ ማስፈለጉ ግን ግልጽ ነው። ያሉት ማኅበራትና የበጎ አድራጎት ውጤቶች ላይ መንግሥት እያከለና እያጠናከረ ቢሔድ፣ ከመከላከል ዕቅዱ በተጓዳኝ ሕክምናውን ለማዘመንና ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችለው አያጠራጥርም።

መፍትሔ
ኩኑዝ እንዳሉት፤ እነዚህን በሽታዎች መንግሥት በጤና ሚኒስቴር በኩል ብቻ መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚችለው አይደለም። ይልቁንም የሲቪል ማኅበራት፣ ኅብረተሰቡ፣ የተለያዩ አጋር ድርጅቶችና እያንዳንዱ ቤተሰብም ራሱ መሳተፍ መቻል አለባቸው። “ጉዳዩ ፈርጀ ብዙ ምላሽ ይፈልጋል፤ መንስዔውም ፈርጀ ብዙ ስለሆነ። አጋላጭ የተባሉት መንስዔዎች ከጤናው ዓውድ በላይና ውጪ በመሆናቸው የሚመለከተው ሁሉ መሳተፍ ይኖርበታል” ሲሉም ገልጸዋል።

እንደማሳያም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በተመለከተ ከስፖርት ጋር በተገናኘ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ ተቋማት፣ ትምህርት መስጠት ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ታች ድረስ በሚወርድ መዋቅሩ፣ በአመጋገብ ዙሪያ ግብርና እና ምግብ ላይ የሚሠሩ የሚመለከታው በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ተቋማት ወዘተ ቅንጅታቸው አስፈላጊ ነው። ጤና ሚኒስቴር ምላሹን ለመስጠትና መከላከል ላይ እንዲያተኩር ለማስቻል ሁሉም የየራሱን ሚና የሚወስድበት የትብብር እቅድና ስልት እየተዘጋጀ መሆኑንም ኩኑዝ ጠቅሰዋል።

ፕሮፌሰር ሽታዬም በበኩላቸው፤ ስለ በሽታዎቹ መነሻና አጋላጭ ሁኔታ ከታችኛው የዕድሜ ክልልና ትምህርት ደረጃ ጀምሮ ጎልማሳ እስከሚባለው የዕድሜ ክልል እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ እውነቱን እንዲያውቁ በአቅማቸው መጠን ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል። መልዕክቶቹም እንቅስቃሴ አድርጉ፣ ጣፋጭ አታብዙ፣ ኮምፕዩተር ላይ ብዙ አትቀመጡ ከማለት ጀምሮ ሳይንሳዊ መንገድን በማሳየትና በማስተማር ጭምር መሆን ይገባዋል።

እዚህ ላይ የመገናኛ ብዙኀን፣ ይልቁንም እያንዳንዱ ሰው በሚገባው መንገድና ቋንቋ፣ በሬዲዮ የሚደረስበትንም በዛ እየደረሱ ማስተማር ያሻል ብለዋል። ከዚህ በተጓዳኝ ከከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ ገጠራማ ጥሩ ነገር እንዳለ ሽታዬ ገልጸዋል። ይህም ተፈጥሮአዊ የሆኑና ማቆያም ሆነ መሰል ኬሚካል ያልነካቸውን ምግቦች የሚመገቡ፣ ብዙ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ ውፍረት የማይጠጋቸውና የአልኮል መጠጥም ቢሆን የቤት ውስጥ ምርትን የሚጠቀሙ፣ ሲጋራን አብዝተው የሚጸየፉ መሆኑ ጥሩ ስለሆነ ያንን ጠብቆ ማቆየት ያስፈልጋል ሲሉ አስታውሰዋል። “የሚያስፈልገው ማስተማር ነው፤ ማስጠንቀቅና ማባበል አይሠራም።” ሲሉ አክለዋል።

ማኅበራትም መንግሥትን ማገዙ ላይ ሚናቸውን በስፋት እንዲወጡ ለማስቻል የመድኀኒትና ግብዓት አቅርቦትን በተመለከተ ቅድሚያ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ደግሞ ያነሱት ሰሎሞን ናቸው። ለምርመራ ብቻ ወጪው ከባድ እንዳይሆን መመርመሪያ መሣሪያዎች በመንግሥት ተቋማት እንዲገኙ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።

አያይዘውም በትምህርት ስርዓቱ የጤናን ጉዳይ ማካተትና ይልቁንም ተላላፊ ስላልሆኑ በሽታዎች መረጃዎችን ማቀበል፣ የጤና ባለሙያዎች በትምህርት ቤቶች አጫጭር የጤና ግንዛቤዎችን እንዲሰጡ ማድረግና በድምሩ ሁሉም በቅንጅት መሥራት አለበት ብለዋል። ይህ ሲሆንና ጤናማ የኑሮ ዘይቤ ሲፈጠር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል፣ የዜጎችን ሕይወት ማትረፍና መታደግ እንዲሁም የአገር ኢኮኖሚን ከኪሳራ ማዳን ይቻላል፤ የሁሉም ጥሪም በቅንጅት መሥራት ላይ እናተኩር የሚል ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here