የትግራይ ክልል በወሰን እና ማንነት ጉዳዮች አዋጅ ላይ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ

0
426

የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ክልል ተወካዮች አማካኝነት፣ የወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ የቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ፣ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ውድቅ ተደረገ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ የቀረበለትን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን በታኅሳስ 2011 በ33 ተቃውሞና በ4 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁ ይታወሳል።

በወቅቱ የትግራይ ክልል ተወካይ የሆኑ የሕወሓት አባላት ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ፣ መፅደቅ የለበትም በማለት ከፍተኛ ክርክር በምክር ቤቱ ውስጥ አድርገው ነበር። የሙግታቸው ማጠንጠኛ ሆኖ የቀረበው የወሰንና የማንነት ጉዳይ ኮሚሽን አዋጅ በሕገ መንግሥቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ በመሆኑ፣ ተመሳሳይ ኃላፊነት ለኮሚሽኑ ሊሰጥ አይገባም የሚል ነበር።

በተጨማሪም ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶች ከፍተኛ ለሆነ አለመረጋጋት መንስኤ በመሆናቸው፣ ለእነዚህ ችግሮች ገለልተኛ በሆነ፣ ከፍተኛ ሞያዊ ብቃት ባለውና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ማፈላለግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ኮሚሽኑ የተቋቋመ እንደሆነ በአዋጁ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 መሠረትም የድንበር አለመግባባት በኹለት ክልሎች መካከል ሲፈጠር በቀዳሚነት ክልሎቹ በስምምነት እንዲጨርሱ የተደነገገ ነው በሚል ነበር ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበረው።

ክልሎቹ በራሳቸው መስማመት ካልቻሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን ይህ አዋጅ ግን የክልሎቹን እና ምክር ቤቶቹን ኀላፊነት የሚነጥቅ እንደሆነ በማንሳት ነው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታው የቀረበው።

አዋጁ ከሥሙ ጀምሮ ሙሉ ይዘቱ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን የክልሎችን ሥልጣን የሚፃረር እና በሕግ መንግሥቱ ላይ የተጠቀሱ የተለያዩ ድንጋጌዎችን የሚጥስ በመሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጠው በሚል የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጥያቄ ማስገባቱን የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ አማኑኤል አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፣ አዋጁ ምንም አይነት የሕግ ትርጓሜ አያስፈልገውም በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ዘረአይ ወልደ ሰንበት በማህበራዊ ገፃቸው እንዳጋሩት፣ በጉዳዩ ላይ የሚያደርጉትን ትግል እንደሚቀጥሉ የገለፁ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት ለመስጠት አዲስ ማለዳ በስልክ ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የኮሚሽኑ አዋጅ መግቢያ እንደሚያትተው አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከአስተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ማስተዳደር እና ከማንነት ጋር የተያይዙ ግጭቶችንና መንስኤያቸውን በመተንተን የመፍትሔ ሐሳቦችን ለሕዝብ እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማቅረብ ዓላማው እንደሆነ ተቀምጧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here