ኢትዮጵያ ለሕፃናት ከማይመቹ የአፍሪካ አገራት ተርታ ተመደበች

0
836

ኢትዮጵያ ለሕፃናት ባላት ምቹነት ከአፍሪካ 43ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የ2018 የአፍሪካ የሕፃናት ደኅንነት ሪፖርት አመለከተ። በትምህርት ጤናና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲሁም ደኅንነት ላይ ለሕፃናት የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ እየተሞከረ ነው ያለው የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ከሕፃናት ጉዳይ ጋር ተያይዞ በሌሎች ተቋማት ላይ ከድጋፍና ክትትል ባለፈ ጣልቃ የመግባት ሥልጣን አለመኖሩ አንዱ ችግር መሆኑን አመልክቷል።
ሪፖርቱ ላለፉት 10 አመታት አምስት ተመሳሳይ ሪፖርቶችን ይፋ ያደረገ ሲሆን ሪፖርቱ በዋናነት የአፍሪካ አገራትን የሕህፃናት ምቹነት ደረጃን በማውጣት አገራቱ የሕፃናት መብቶችን በማክበር ረገድ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ይገመግማል።
ይፋ በሆነው ሪፖርት ኢትዮጵያ 43ኛ ደረጃን ያገኘች ሲሆን ይህም በ2013 ከነበረችበት 37ኛ ደረጃ በስድስት ዝቅ ብላለችው። በሪፖርቱ ሞሪሽየስ፣ አልጄሪያና ቱኒዚያ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ በተቃራኒው ቻድ፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክና ደቡብ ሱዳን ደግሞ በተከታታይ የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል።
የሕህፃናት ምቹነት ደረጃው የሚወጣው በተባበሩት መንግሥት የሕፃናት መብቶች ስምምነት እና የአፍሪካ ሕፃናት መብት እና ደኅንነት ቻርተርን መሰረት ባደረጉት ሦስት መለኪያዎች ላይ በመመስረት ነው። መለኪያዎችም የሕፃናት ጥበቃ፣ አቅርቦትና አሳታፊነት ናቸው።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዳኜ ተግይበሉ፤ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመለከተ እስካሁን ባለው አሰራር ዕቅድ ተይዞ ጥናቶች እየተደረጉ በመንግስት እንደሚፈረሙ ገልፀው፤ የሕፃናት መብቶች ስምምነትን ሶስተኛ ፕሮቶኮል በተመለከተ በተለየ የተያዘ ዕቅድ አለመኖሩ ተናግረዋል።
የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተም ከሪፖርቱ በተጨማሪ የአፍሪካ ሕፃናት መብት እና ደኅንነት ቻርተር መደበኛ የአፈፃፀም ሪፖርት ላይም ኢትዮጵያ ላይ ከተነሱ ነጥቦች መካከል አንዱ ይህ እንደሆነ ገልፀው የወንጀል ሕጉ በሚሻሻልበት ወቅት መካተት ከሚኖርበቸው የሕግ ክፍሎች ውስጥ ሊካተት እንደሚችል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እንደተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት በአቅርቦት በኩል ደግሞ የአፍሪካ አገራት ለህፃናት መሰረታዊ ፍላጎቶች፣ ትምህርትና የጤና አገልግሎት መዳረስ ከጠቅላላው በጀታቸው ምን ያህሉን መድበዋል፤ ምንስ ውጤት አምጥተዋል የሚለው ይለካል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ሦስት ነጥብ አምስት በመቶውን ብቻ ለማህበራዊ ጥበቃ እንደምታውል ተገልጷል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ለጤናው ዘርፍ የምትመድበው በጀት ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነፃፀር ስድስት በመቶ ድርሻ ብቻ እንዳለው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በዚህ ረገድ የሴቶች፣ ህፃትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊነት ውስን መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳኜ፤ ይሁንና በሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሁሉ የህፃትና ሴቶች ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ በትምህርት ጤናና ሌሎች አገልግሎቶች ላይ ለህፃናት የተለየ ትኩረት የሚሰጥበት ሁኔታ እና የተቋማቱ እቅዶች ከህፃናት ደህንነት አንፃር የሚኖራቸውን ተፅእኖ እንደሚከታተል ገልፀዋል። ሚኒስቴሩ በሌሎች ተቋማት በዚህ ረገድ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ ጣልቃ የመግባት ስልጣን እንደሌለው አቶ ዳኜ አክለዋል። ይህም የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አንዱ ችግር ሆኗል ተብሏል።
በዚህ ሪፖርት የአፍሪካ አገራት ለሕፃናት ካለቸው ምቹነት አንፃር በአምስት ደረጃዎች የተመደቡ ሲሆን ኢትዮጵያ አራተኛውን ወይም ዝቅተኛውን የምቹነት ደራጃ አግኝታለች። ኤርትራን ጨምሮ ዘጠኝ የአፍሪካ አገራት የመጨረሻው ወይም እጅግ ዝቅተኛ የተባለው የምቹነት ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የተባበሩት መንግስታት አስቀምጧቸው ከነበሩ የምዕተ ዓመቱ ግቦች እና ካስቀጠላቸው የዘላቂ እድገት እቅዶች መካከል ሁሉ አቀፍ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትና ማስፋትና የህፃናትን ሞት መቀነስ ይገኙበታል። ኢትዮጵያ በእነዚህ ግቦች የተሻለ ስኬት ካስመዘገቡት አገራት መካከል መሆኗንም የተበባበሩት መንግስታት ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here