ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ ስማርት ቆጣሪዎች ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
ስማርት ቆጣሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት የተጀመረዉ ለጊዜዉ ከፍተኛ የሃይል ተጠቃሚ ለሆኑ ኢንዱስትሪዎች ሲሆን፤ በመድናዋ ብቻ ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስማርት ቆጣሪዎች የመቀየር ሥራ እንደተጀመረ ተገልጿል።
መደበኛ ነበረውን ቆጣሪ ወደ ስማርት ቆጣሪዎች የመቀየር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚውኒኬሽን ዳሬክተር የሆኑት መላኩ ታዬ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
መላኩ እንዳሉት ከፍተኛ በጀት ተይዞለት ወደ ሥራ የገባውና ነባሩን ቆጣሪ ወደ ስማርት የመቀየር ሥራ ያስፈለገው፣ የሃይል መቆራረጥ ሲኖር ለመከታተል እና ከዚህ ቀደም ከቆጣሪ አንባቢ ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ቅሬታ ይፈታል ተብሎ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ በፓይለት ደረጃ የተጀመረው ነባሩን ቆጣሪ የመቀየር ሥራ፣ ኑርፍሌክስ በተባለ የደቡብ ኮርያ ኩባንያ እየተከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በኹለት ምዕራፍ ተከፍሎ ወደ ተግባር የገባው አሰራር በመጀመርያው ዙር 5 ሺህ የሚሆኑ ቆጣሪዎችን የመግጠም ሥራ እንደሚሰራ እና በኹለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 45 ሺህ የሚሆኑት ነባር ቆጣሪዎች የሚተኩ መሆናቸዉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭ የአለም ባንክ መሆኑን የተናገሩት መላኩ፤ በብድር የተገኘው 12 ሚሊዮን 546 ሺህ 54 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፣ ቀሪው 9 ሚሊዮን 640 ሺህ 450 ብር ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን መሆኑ ነዉ የተገለጸዉ፡፡
መጋቢት 2 ቀን 2014 ወደ ሥራ የገባው ስማርት ቆጣሪዎችን የመቀየር ሥራ፣ እስካሁን 107 የሚሆኑ ቆጣሪዎች መተከላቸውን ዳይሬክተሩ ለሬዲዮ ጣቢያው ተናግረዋል፡፡
ይሁንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ የመቀበል ልምዳችን ዝቅተኛ በመሆኑ፣ አገልግሎቱ ይህን የመቀየር ሥራ ሲሰራ አንዳንድ የከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ስማርት ቆጣሪዎን ለማስቀየር ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሥራችንን እያጓተተው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡



