ባለፉት አምስት ወራት ለትግራይ ክልል 269 ሜትሪክ ቶን በላይ የህክምና ቁሳቁስ ተልኳል

0
1179

ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ለትግራይ ክልል በአጠቃላይ ከ269 ነጥብ 55 ሜትሪክ ቶን በላይ የህክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት መላኩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ሴክተር መስርያ ቤቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ለትግራይ ክልል ህዝብ የሚያደርጉት የተቀናጀ የጤና አገልግሎት ድጋፎች መቀጠላቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ጤና ሚኒስቴር ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን፤ ለትግራይ ህዝብ ከጥር እስከ ግንቦት 2014 ድረስ አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶች፣ ግብኣቶችን እና የስነ ምግብ አቅርቦቶችን በማመቻቸት እና በማድረስ በኩል በቅንጅትና በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

ከጥር እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ ውስጥም የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን የመድሃኒት እና የስነ-ምግብ አቅርቦቶችን በማመቻቸት ለትግራይ ክልል በሳምንት ዉሰጥ በአለም አቀፍ ድርጅቶች በሚደረጉ የተለያዩ በረራዎች ያቀረበ ሲሆን፤ የጤና ሚኒስቴር በአጠቃላይ ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒት እና የህክምና ቁሳቁሶችን በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩል ወደ ትግራይ ክልል መላኩን አስታውቋል።

በዚህም ፀረ-ካንሰር፣ የልብ ህክምና መድሐኒቶች፣ ART እና OI መድሃኒቶች፣ የቲቢ ህክምና መድሃኒቶች፣ የስኳር ህክምና መድኃኒቶች (ኢንሱሊን) እና ደም-ግፊት ህክምና መድኃኒቶች ፣ አስፈላጊ አንቲባዮቲኮች እና ሌሎች አስፈላጊ መድሃኒቶች መላካቸውን ነው ሚኒስቴሩ የገለፀው።

በተጨማሪም በአለም ጤና ድርጅት በኩል በአጠቃላይ 135 ነጥብ 45 ሜትሪክ ቶን የጤና እና አልሚ ምግብ አቅርቦቶች ለ1 ሚሊየን 128 ሺህ 750 ግለሰቦች ለ3 ወራት አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ድጋፎች ተደርገዋል።

አስፈላጊ ለሆኑ የጤና አገልግሎቶች ግምታቸው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ የህክምና ግብዓቶች ድጋፍ ተደርጋል። የኮሌራ ሕክምና መስጫ 43 ነጥብ 28 ሜትሪክ ቶን፣ የፀረ-ወባ 0.215 ሜትሪክ ቶን፣ ኮቪድ-19 1 ነጥብ 25 ሜትሪክ ቶን፣ የተመጣጠነ ምግብ 8 ነጥብ 852 ሜትሪክ ቶን፣ ተንቀሳቃሽ ህክምናና አልሚ ምግብ 10 ነጥብ 849 ሜትሪክ ቶን በጠቅላላ 64 ነጥብ 446 ሜትሪክ ቶን ለትግራይ ክልል ድጋፍ መደረጉም ተነግሯል።

እንዲሁም በአለምአቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር (ICRC) በኩል ለ484 ሺህ 167 ግለሰቦችን ለ3 ወራት ሊያገለግል የሚችል 58 ነጥብ 1 ሜትሪክ ቶን አስፈላጊ መድሃኒት600 ሄሞዳያሊስስን ለማካሄድ የሚረዱ የህክምና አቅርቦቶች እና የፍጆታ እቃዎች መቅረባቸውም ተገልጿል።

ከሌሎች አጋሮችም ከ76 ሜትሪክ ቶን በላይ የህክምና ግብዓቶች መቅረባቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ወራት ለትግራይ ክልል 269 ነጥብ 55 ሜትሪክ ቶን ጭነት መላኩንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

እነዚህ ድጋፎች ቢደረጉም አሁንም ካለዉ ተጨማሪ ፍላጎትና ከአይደር ሆስፒታል በቀረበው ጥያቄ መሰረት ጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት መጋዘን በአለምአቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር እና በአለም ጤና ድርጅት በኩል የሚላኩ የማደንዘዣ መድሃኒቶችን ጨምሮ ተጨማሪ ጭነቶችን ማዘጋጀቱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

እንደ ዳያሊስስ ፍጆታ ያሉ ሌሎች ልገሳዎች እንዲሁ በአለምአቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር (ICRC) በኩል ለመላክ በሂደት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here