ማዕከላዊ ሙሉ ለሙሉ አልተዘጋም

0
444

ዮርዳኖስ ሆቴል ላይ ለሚገኘው ቢሮው፥ ኮሚሽኑ በወር ሁለት ሚሊዮን ብር ይከፍላል

ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት የሰቆቃ ማዕከል ሆኖ የቆየው ማዕከላዊ እስር ቤት ሙሉ ለሙሉ እንዳልተዘጋና በከፊል ለቢሮ አገልግሎት እየዋለ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ ፌዴራል ፖሊስ ከሚገኙ የተለያዩ ምንጮች አረጋገጠች።
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቢሮ በተለያየ ደረጃዎች የሚገኙ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዳረጋገጡት፥ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ተጠርጣሪዎችን ለመመርመር የሚጠቀምበትን ‹ዘመናዊ› ክፍሎች መዝጋቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን ለማሰር ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ይጠቀምባቸው የነበሩ ክፍሎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ተብለው ቢታቀድም እጥረት በማጋጠሙ ከፊሎቹን ክፍሎች ለቢሮ አገልግሎት ብቻ ለመጠቀም መገደዱን አስረድተዋል።
“ታሳሪዎችን ደግሞ ማዕከላዊን እንዳንጠቀም የተሰጠንን ትዕዛዝ ተከትሎ እስረኞችን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ አዛውረናል። ነገር ግን ከቢሮ መጣበብ ጋር በተያያዘ እስር ቤቱን ለቢሮነት ለመጠቀም ተገደናል።” ሲሉ የምርመራ ቢሮው ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ አስረድተዋል።
ማዕከላዊ ስምንት ሺሕ ካሬ ሜትር የሚጠጋ መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፥ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት በጣሊያን ዲዛይነሮችና ኮንትራክተሮች የተገነባ ሲሆን በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን “የፖሊስ ሠራዊት ልዩ ምርመራ” ተብሎ ይጠራ እንደነበር መዛግብቶች ያሳያሉ።
ሂዩማን ራይትስ ዎች “They Want Confession” በሚል ርዕስ በ2013 ስለማዕከላዊ ባወጣው ሪፖርቱ ማዕከላዊ በእስረኞች በቅዝቃዜው ሳቢያ ሳይቤሪያ፣ በአንፃራዊ ምቾቱ ሸራተን እና በወለሉ ጣውላ ቤት በመባል የሚጠሩ ሦስት የእስረኛ ማቆያዎች ያሉት ሲሆን እያንዳንዳቸው የሚጨምር እና የሚቀንስ ቁጥር ያላቸው እስረኞችን የሚይዙ በርካታ ክፍሎች አሏቸው።
ከ11 ወራት በፊት የቀድሞ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ጋር በሰጡት መግለጫ፣ ማዕከላዊ የምርመራ ማቆያ ሥፍራ ሆኖ እንደማይቀጥልና ሙዚየም ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በማዕከላዊ ምትክ “ዓለም ዐቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የምርመራ ማዕከል” በተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ መቋቋሙን ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቶ ከሰባት ወራት በፊት በተሾሙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህ የዜጎች ማቆያ ሥፍራ የነበረው ማዕከላዊ እስር ቤት እንዲዘጋ ተደርጓል ተብሎ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ተዘግቦ ነበር።
በተጨማሪም ማዕከላዊ ሙዚየም እንደሚሆን በይፋ ከዚህ ቀደም ቢነገርም እስካሁን የተጀመረ እንቅስቃሴ እንደሌለ አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ማረጋግጥ ችላለች። ምክትል ኮሚሽነር ተኮላ እንደገለጹት ቢሮው ከመንግሥት አጥፊዎችን ለይቶ ሕግና ሰብኣዊነት በማስከበር አኳያ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት ተልዕኮ ቢሰጠውም የተሟላ ቢሮዎችና መመርመሪያ ክፍሎች ስሌለው ግዴታውን ለመወጣት እየተቸገረ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የወንጀል ምርመራ ቢሮ ዋና መሥሪያ ቤት በቀድሞ ዮርዳኖስ ሆቴል ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ቢሮው በወር ሁለት ሚሊዮን ብር ሕንፃውን ለመከራየት ያወጣል። ከዚህ በተጨማሪ የቢሮው ፎረንሲክ መርማሪዎች እና የሌሎች ሠራተኞች ቢሮ በጥቁር አንበሳና በኮልፌ አካባቢ ይገኛሉ። ነገር ግን በቢሮ እጥረትና የራሱ የሆነ እስር ቤት ስለሌለው መቸገሩን ምክትል ኮሚሽነር ተኮላ ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here