የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ 353 ሚሊየን ብር ማባከኑ ታወቀ

0
884

የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በአገሪቷ 17 መጋዘኖች፣ መድኃኒት ማከማቻና ቢሮዎች ግንባታዎች ባካሔደበት ወቅት ያልተገባ 353 ሚሊየን ብር ማውጣቱ ታወቀ። አዲስ ማለዳ ከፌዴራል ኦዲተር ዋና መሥሪያ ቤት ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው ኤጀንሲው የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖችና ቢሮዎች ለማስገንባት ከአራት ሥራ ተቋራጮች ጋር በ152 ሚሊየን ብር ውል የተፈራረመ ቢሆንም ግንባታው በመዘግየቱ ክፍያው ወደ 311 ሚሊየን ከፍ ብሏል።
ክፍያው በ159 ነጥብ 1 ሚሊየን ከመጨመሩም ባሻገር ግንባታው ከ475 እስከ 1542 ቀናት የዘገየ መሆኑን መረጃው ያሳያል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኤጀንሲው ከሥራ ተቋራጮች ሲፈራረም ትልቁ የውል ጊዜ 240 ቀናት ነበር።
በተጨማሪም የግንባታው መዘግየትና በታሰበው መሠረት ፕሮጀክቶቹ በ2003 ተጠናቀው ሥራ አለመጀመራቸው ከ2004 እስከ 2010 መጀመሪያ ድረስ ለመጋዘን ኪራይ ከ194 ሚሊየን ብር በላይ አገሪቷን አላስፈላጊ ወጪ አስወጥቷል።
መድኃኒት ማከማቻ እና ቢሮዎች አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ በሥራ ላይ መሆናቸውን የገለጹት የኤጀንሲው የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አድና በሬ በበፊቱ አመራሮች መጋዘኖችን በአግባቡ የአለመጠቀም ችግር ነው ብለዋል።
“የመጋዘኖቹ ግንባታ ከዓመታት በፊት ቢጠናቀቅም የነበሩት አመራሮች ባልታወቀ ምክንያት መከራየት ላይ ትኩረት የማድረግ ችግር ነበር” ብለዋል። አጄንሲው በተጠቀሱት ዓመታት እስከ 2007 ድረስ በኃይለሥላሴ ቢሆን የተመራ ሲሆን ከዚያም እስከ የካቲት 2010 ድረስ በመስቀላ ሌራ ተመርቷል።
አዲስ ማለዳ የሰበሰበችው መረጃ እንደሚያሳየው ለፕሮጀክቶቹ ተገቢው ግንባታው ከመጀመሩ በፊት የአዋጭነት ጥናት ባለመጠናቱ፣ የግንባታ ዲዛይን ፅንሰ-ሐሳብ ቀርቦ ያልተተቸ በመሆኑና የፀደቀ ዲዛይን ባለመኖሩ የግንባታ መጠኑን በወቅቱ የነበሩት አመራሮችና ተቋራጮቹ መጨመራቸውን ያመለክታል።
በውሉ መሠረት ግንባታውን ያላጠናቀቁት ተቋራጮቹ በየቀኑ የውሉን 0.1 በመቶ ኤጀንሲው መቅጣት ቢገባውም ሆን ተብሎ ተቋራጮች እንዳይቀጡ ለማድረግ የማይመስልና ተቀባይነት የሌለው ከ475 እስከ 1542 ተጨማሪ የውል ማራዘሚያ መደረጉን ባለፈው ዓመት ታትሞ የወጣ የፌዴራል ኦዲተር መረጃ ያሳያል። አዲስ ማለዳ የተቋራጮችን ማንነት ከኤጀንሲው ለማግኘት በተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሊሳካ አልቻለም።
ነገር ግን የኤጀንሲው የኮሚኒኬሽን ኃላፊ እንደገለጹት በመጋዘን ኪራይ ላይ በበፊቱ አመራር ላይ ያለውን ችግር በመረዳት ኤጀንሲው ሙሉ ለሙሉ መጋዘን መከራየት ማቆሙን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም የወለል ጥገና በተለያዩ የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖች እየተካሔደ መሆኑን ገልጸዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መድኃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያዎችና ሌሎች ግብአቶችን ለመንግሥት የጤና ተቋማት እንዲያቀርብ በ2000 የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ከገንዘብ ብክነት ጋር በተያያዘ በፌዴራል ኦዲተር ቅሬታ በተለያየ ጊዜያት ቀርቦበታል።
በ2008 ትክክለኛውን የግዢ ሒደት ባልተከተለ መልኩ ሁለት ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ 69 ሚሊየን ኮንዶም ‹ኤች ኤል ኤል› ከተባለ የሕንድ ድርጅት ከገዛ በኋላ በመበላሸቱ ምክንያት ለማስወገድ መገደዱ አይዘነጋም። በተመሳሳይ ዓመት በወጣ ኦዲተር ሪፖርት ላይም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶች፣ ኬሚካሎችና ሌሎች የሕክምና ዕቃዎች በአግባቡ ባለመሠራጨታቸው ጊዜያቸው ሊያልፍ እንደቻለ ያሳያል።
የዛሬ 11 ዓመት ሥራ የጀመረው ኤጀንሲው፥ በወቅቱ 640 ሚሊዮን ብር በጀት የነበረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የጤና ግብአት ያሠራጫል። ኤጀንሲው በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች 19 ቅርንጫፎች አሉት።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here