የሲዳማ ግጭት መንስኤ ምርመራ ቶሎ እንዲጠናቀቅ ኢሰመኮ ጠየቀ

0
550

ባሳለፍነው ሳምንት በሐዋሳ ከተማና አካባቢው ጉብኝት ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “በግጭቱ የተጐዱ ሰዎችንና ቤተሰቦችን በተገቢው መጠን ከመርዳት እና መልሶ ከማቋቋም በተጨማሪ የምርመራው በፍጥነት መጠናቀቅ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል” ሲሉ አሳሰቡ።

ኮሚሽነሩ በሐዋሳ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ እስረኞችንና አያያዛቸውን ጐብኝተዋል።

ከሐዋሳው ጉብኝት ቀደም ብሎ በግጭት ከተጐዱ ቤተሰቦች ጋር የተወያዩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ “ለችግሩ መነሻ የሆነው ዋነኛ ምክንያት በሲዳማ ዞን ምክር ቤት ለቀረበው የክልልነት ጥያቄ በሚመለከታቸው አካላት ሲሰጥ የነበረው ምላሽ ወቅታዊ እና ስልታዊ አለመሆንና በሌላ በኩል ጥያቄውን በተናጠል ውሳኔ እና በኀይል ጭምር ለማስፈፀም የፈለጉ ቡድኖች ባራመዱት አስተሳሰብ የተነሳ በተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት እና ቀውስ ነው” ብለዋል፤ ዳንኤል።

ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ሌሎች ምንጮችም በተገኘው መረጃ መሠረት እስከ አሁን በተደረገው የፖሊስ ምርመራ፤ በሦስት ማዕከሎች በእስር ይገኙ ከነበሩ ወደ 1 ሺሕ 500 ገደማ እስረኞች ውስጥ ከግማሽ በላይ የተለቀቁ መሆኑን መረዳት ተችሏል።

አሁንም በኅዳር 2012 ይካሔዳል ተብሎ ከታቀደው ሕዝበ-ውሳኔ አስቀድሞ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ማዕቀፎች በማዘጋጀት፣ እንዲሁም ተአማኒ በሆነ የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስቀድሞ መግባባት ላይ በመድረስ ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር እጅግ አፋጣኝ እርምጃ ይሻል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ በኮሚሽኑ የፌስቡክ ገጽ አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here