በድሬዳዋ አስተዳደር ግጭት 22 ተጠርጣሪዎች ታሰሩ

0
764
  • አስተዳደሩ በግጭቱ የተሳተፉ የመንግሥት አመራሮችን ለሕግ አቀርባለሁ ብሏል።

ሰሞኑን በድሬዳዋ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት ከፊትም ሆነ ከጀርባ ሆነው የነዋሪዎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የጣሉ ማንኛውንም የመንግሥት አመራር፣ የፀጥታ አስከባሪ፣ በዋናነትም ፀረ ሰላም ሆኖ እራሱን ያደራጀ ቡድንም ሆነ ግለሰብ በንፁሐን ነዋሪዎች ሕይወት ላይ በመቆመር የቆሸሹ እጆችን ሰብስቦ ለህግ እንደሚያቀርብ የአስተዳደሩ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

በጸጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ሦስት መድረሱን አዲስ ማለዳ ከድሬደዋ ነዋሪዎች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። በግጭቱ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን እና በውል ያልታወቀ ንብረት መዘረፉን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

የድሬደዋ ከተማ ነዋሪ የሆኑና በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ብርሃኑ ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ችግሩን የፈጠሩት ወጣቶች የአካባቢው ነዋሪዎች አይደሉም። ከሌላ ቦታ በአይሱዙ መኪና ተጭነው የመጡት ወጣቶች የአካባቢውን ወጣት ለማሳደም ጊዜ አልፈጀባቸውም። ጥቃቱ ብሔርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ስለነበር በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሱቃቸውን ሳይዘጉ መሸሻቸውንና መዘረፋቸውን ተናግረዋል።

አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ግጭቱን ያነሳሱት አካላት ከዓመት በፊት የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፤ የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል።

በድሬዳዋ ደቻቱና አምስተኛ ከተባሉ አካባቢዎች ተነስቶ ወደ ሌሎች እየተስፋፋ በመጣው ግጭት ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙንና ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ከመቶ ሃምሳ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም የአስተዳደሩ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ገልጿል።

በድሬደዋ ከተማ በቀበሌ 06 ልዩ ሥማቸው ቀፊራ፣ ደቻቶ እና አምስተኛ ተብለው በሚታወቁ አካባቢዎች ኹከትና ግጭቶች ተፈጥሯል። የአዲስ ዓመት ዋዜማን አስመልክቶ በተዘጋጀ የመዝናኛ ዝግጅት በወጣቶች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ፀብን መነሻ በማድረግ በተደራጀና በተጠና በሚመስል መልኩ ወደ መንደሮች በማስፋፋት የሰላማዊ ነዋሪዎችን ንብረት ማውደምና መዝረፍ የተሸጋገረበት ሁኔታ እንደነበር ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዋዜማ እለት ኹከት ፈጥረዋል የተባሉትን 32 ተጠርጣሪዎች ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እንዲታይ እየተደረገ በሚገኝበት ወቅት በድጋሚ መስከረም 10/2012 ቅዳሜ ማምሻውን ቀደም ሲል ግጭት በነበረባቸው ስፍራዎች በድጋሚ ኹከትና ፀብ ተቀስቅሶ የብሔርና የሃይማኖት መልክ እንዲኖረው ለማድረግ የተደረገው ጥረት በማኅበረሰብና በፀጥታ ኀይሉ ቅንጅት አለመሳካቱን የቢሮ ተወካይ ሚካኤል እንዳለ ገልፀዋል። በተመሳሳይም ባንኮችን ለመዝረፍ የተቃጣው ድርጊትም ሳይሳካ መቅረቱን ጠቁመዋል።

እንደ ኀላፊ ተወካይ ገለጻ፣ በግጭቱ የተጎዱ ነዋሪዎችን በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታልና በሳቢያን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ፖሊስ ግጭቱን ለማረጋጋት ባደረገው እንቅስቃሴ አንድ ወጣት በተባራሪ ጥይት ሕይወቱ ማለፉን ገልፀዋል።

ሚካኤል መስከረም 10/2012 በዝርፊያና በኹከቱ የተሳተፉ 22 ተጠርጣሪዎችን በሕግ ጥላ ሥር የማዋሉ ሥራ በፀጥታ አካላት እየተከናወነ ሲሆን የተዘረፉ ንብረቶችን የማስመለሱ ሥራ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here