የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አራት ፈጣን መንገዶችን ሊገነባ ነው

0
745

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አዲስ አበባን ከክልል ከተሞች ጋር የሚያገናኙ አራት ፈጣን መንገዶችን ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገለፀ።
ፈጣን መንገዶቹ አዲስ አበባን መዳረሻ በማድረግ ደብረ ማርቆስ፣ ጅማ፣ ነቀምት እና ኮምቦልቻ የሚገነቡ ሲሆን አዲስ አበባ አዳማ ፈጣን መንገድን ጨምሮ በከተማዋ እና በፈጣን መንገዶች መገናኛ ቦታዎች ላይ የማሻሻያ ሥራዎችን የሚጨምር ነው።

ግንባታውን ለማከናወን የአዋጪነት ጥናት ለማድረግ እየተሠራ ሲሆን ጥናቱ እንደተጠናቀቀ በግል እና በመንግሥት አጋርነት አሊያም የግንባታ እና የዲዛይን ሥራ ውጤቱ በሚያመላክተው አዋጭ መንገድ ለመገንባት ባለሥልጣኑ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የመንገዶች ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል።

ከጥናቱ በሚገኘው ውጤት በመነሳትም የግንባታ ወጪ ምንጮች፤ የመንገዶቹን የኪሎ ሜትር ርዝመት እና የሚፈጥሩትን የሥራ ዕድል ለመረዳት እንደሚቻል የገለጹት ሳምሶን፥ መንገዶቹ በክልል ከተሞቹ የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል። ፈጣን መንገዶቹ መዲናዋን ከአጎራባች ከተሞች ጋር ለማገናኝት ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።

የአለርት ኢንጅነሪንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አለምገና አለነ (ዶ/ር) መንገድ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ መሰረተ ልማት መሆኑን ገልጸው፥ እንደዚህ ዓይነት ፈጣን መንገዶች የትራፊክ ፍሰቱን ለማቀላጠፍ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።

የሚገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች መዳረሻቸው አዲስ አበባ መሆኑ ከተማዋ በታሪክ አጋጣሚ አብዛኛው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚከናወንባት በመሆኗ የሚገነቡ መንገዶች ሁሉ መዳረሻቸውን አዲስ አበባ እንደሚደርጉ ገልጸዋል። ከወደብ የሚገቡ ዕቀዎች ሳይቀሩ አዲስ አባባ ገብተው ነው ወደ ሌሎች ክልሎች የሚከፋፈሉት፤ ሌሎች ክልል ከተሞችን እርስ በእርስ ማገናኝቱ ተገቢ እና በክልሎች የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ትልቅ ጥቅም ስለሚኖረው ወደፊት በርካታ ጥናቶች ተደረገውበት ሊሠራበት ይገባል ብለዋል።

አሁን ባለው የመንገድ ሽፋን ከአዲስ አበባ ደብረ ማርቆስ 305 ኪ/ሜ፤ ኮምቦልቻ 365 ኪ/ሜ ሲሆን ጂማ 354 ኪ/ሜ ፤ ነቀምት 318 ኪ/ሜ ርቀት ከአዲስ አበባ አላቸው በመኪና እያንዳንዳቸው በአማካኝ ከ 3 እስከ 4 ሰዓት የሚወስዱ ሲሆን ፈጣን መንገዶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ የጉዞ ሰዓቱን እንደሚያሳጥሩ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2012 የበጀት ዓመት 150 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ 91 ፕሮጀክቶችን እንደሚጀምር አስታውቆ የነበረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 46 አዳዲስ 16 ከባለፈው በጀት ዓመት ተላለፈው የመጡ እና 26 ባለፈው ዓመት መጀመር የነበረባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ናቸው። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ ከመንግሥት በጀት ተይዞለታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here