ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያለ ደረሰኝ ግብይት ያከናወኑ ድርጅቶች ክስ ሊያነሳ ነው

0
640

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፌደራል ግብር ከፋዮች ሆነው ያለደረሰኝ ግብይት በመከናወን ምርመራ የተጣራባቸው እና ክስ የተመሰረተባቸው 116 ድርጅቶች ክስ ሊያቋርጥ መሆኑ ተገለፀ።

ድርጅቶቹ በፌደራል ፖሊስ እና በገቢዎች ሚኒስቴር ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ያለደረሰኝ ግብይት በማከነወን ምርመራ የተጣራባቸው እና ክስ የተመሰረተባቸው እንደሆኑ ተገልጿል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻችው የሕግ ባለሙያ ያሬድ ስዮም ክስ ማቋረጥ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ የሕግ መሰረት ያለው ተግባርነው ያሉ ሲሆን በተጠርጣሪዎች ላይ መረጃ ተገኝቶ ቢሆንም እንኳን የክሱ መቋረጥ የሕዝብን ጥቅም ከግምት ውሰጥ ያስገባ ከሆነ ክሱ መቋረጡ ተገቢ ነው ብለዋል ድርጅቶቹ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል፤ የሚከፍሉት ግብር እና የሚያበረክቱት ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅዖ ከግምት ውስጥ መግባት አለበትም ይላሉ። ሆኖም መንግሥት እንዲዚህ ዓይነት የክስ ማንሳት ሒደቶች ሲኖሩ በድርጅቶች መካከል ልዮነት እንዳይፈጠር ሁሉንም ድርጅቶች በእኩል ዓይን መመልከት እንደሚገባውም ይገልፃሉ።

የሕግ ዋናው ዓላማ ዜጎችን ማስተማር ነው ያሉት ያሬድ ስዮም ክሱን ከመቀጠል ይልቅ ቢሠሩ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያመጣሉ ተብሎ ከታሰበ የክሱ መነሳት ተገቢ ነው ብለዋል። መንግስት እንደዚህ ዓይነት ምሕረት ማድረጉ ድርጅቶቹ ሊማሩ የሚችሉበት ተግባር በመሆኑ ሊበረታታ ይገባዋል ብለዋል።

የሰብኣዊ መብት ተሟጋች እና ሕግ ባለሙያ የሆኑት ሔኖክ አክሊሉ በዚህ ሐሳብ የማይስማሙ ሲሆን መንግሥት የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የድርጅቶቹን ክስ የሚያነሳ ከሆነ ግብረ አለመክፈለቸውስ የሕዝብን ጥቅም አይነካም ወይ የሚል ጥያቄን ያነሳሉ በመሆኑም መንግሥት ክሱ የሕዝብን ጥቀም የሚነካ ከሆነ በመጀመሪያም መመስረት አልነበረበትም ብለዋል።

በተጨማሪም እንደዚህ ዓይነት መልኩ ለብዙ ድርጅቶች ክስ ማንሳት ሲደረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ድርጅቶች እና ግለሰቦች በጋራ ብዙ ሆኖ ወንጀል መሥራት ከቅጣት እንደሚያስመልጥ እንዲያስቡ ያደርጋል ብዙ ሆነን ወንጀል ሰርተን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና አሳድረን ከቅጣት እናመልጣለን የሚል አስተሳሰብን ሊፈጥረ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።

ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ግብር ከፋይ በሆኑ በፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ እና በፍርድ ቤት ጉዳያቸው የተያዘ ከ 1 ሺሕ 77 ነጋዴዎች ክስ መቋረጡ የገቢዎች ሚኒስቴር ሕገወጥነት እና ወንጀል ያስፋፋል በሚል ተቃውሞ አቅርቦ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here