ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚጀመረው የታለመ የነዳጅ ድጎማ የገንዘብ ልውውጥ አጠቃቀሙን በተመለከተ ለነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች ማብራሪያ መሰጠቱን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በታለመ የነዳጅ ድጎማ አተገባበር ዙሪያ ለነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች ገለፃ ተደርጓል።
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር እና የታለመ የነዳጅ ድጎማ አስተባባሪ አብዱልበር ሸምሱ፣ የቴሌ ብር በመጠቀም የታለመ የነዳጅ ድጎማን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል እና የታለመ የነዳጅ ድጎማው ተግባራዊ ሲሆን፤ ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች የሚጠበቀውን ሚና በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የታለመ የነዳጅ ድጎማው አተገባበር በቴክኖሎጂ ተደግፎ እንዲከናወን ለማስቻል በከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየሰራ እንደሚገኝም አብዱልበር ተናግረዋል።
የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች በኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማዕከላት በአካል በመቅረብ የቴሌ ብር መጠቀም የሚያስችላቸውን መረጃ ሲደራጁ መቆየታቸውን አስተባባሪው አብራርተዋል።
የታለመ የነዳጅ ድጎማ አጠቃቀምን በተመለከተ ከኢትዮ ቴሌኮም የመጡ ባለሙያዎች ለነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች ተግባራዊ ገለፃ ሰጥተዋል፡፡
ከሰው ንክኪ በራቀ መልኩ የቴሌ ብርን በመጠቀም ግብይት እንደሚፈፀም እና አጠቃቀሙ ቀላልና ምቹ ሆኖ በመዘጋጀቱ አሽከርካሪዎች በፍጥነት ሊላመዱት እንደሚችል ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።








