30 የደለል ወርቅ አለኝታ ቦታዎችን ለማግኘት ጥናት ሊደረግ ነው

0
855

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ 30 የደለል ወርቅ አለኝታ ቦታዎችን ለመለየት የቅኝት ጥናት በመጀመርያ ዙር በትግራይ፣ በጋምቤላ እንዲሁም በደቡብና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ሊጀመር መሆኑን አስታወቀ።

የድርጅቱ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ታምሩ መርሻ እንደተናገሩት ተቋሙ የመንግሥት እንደመሆኑ መጠን የመንግሥት ትኩረት አቅጣጫ የሆኑትን የውጪ ምንዛሬን ለማሳደግ፤ የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት እንዲሁም ደግሞ ማዕድኑ በሚገኝበት አካባቢ ለሚኖሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።

በተጨማሪ የቅኝት ጥናቱም ለኢንቨስትመንት አስተዋጽዖ ያላቸው አራት የብረት ማዕድናት፣ ሰባት የኢንዱስትሪ ማዕድናት 4 የጀምስቶን ማዕድናት እንዲሁም አንድ የድንጋይ ከሰል ማዕድናትን የሚገኙበትን አለኝታ ቦታዎች ለመለየት እስከ ታኅሣሥ መጨረሻ ድረስ በሁሉም ክልል የቅኝት ጥናት የምናደርግ ይሆናል። የቅኝት ጥናቱ ከተካሔደ በኋላ በአካባቢው ከሰላምም ሆነ ከመንገድ ጋር በተያያዘ ለሠራተኞቹ አመቺ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በጥር 2012 ማዕድኑን የመለየት ሥራ ይጀመራል ብለዋል።

ማዕድናቱን የመለየት ሥራ ከሦስት እስከ አራት ወራት ያህል ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ማዕድኑ ተለይቶ ከታወቀ በኋላ ይህን ፍቃድ ወስዶ የሚሠራ ኩባንያ ካለ ሙሉ መረጃውን ከተለያዩ አስፈላጊ ድጋፎች ጋር የምናቀርብ ይሆናል። በተጨማሪም ደግሞ ለክልሉ እና ለአካባቢው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ምቹ እንዲያደርግ እናስተላልፋለን ተብሏል።

እነዚህን ማዕድናት ለመለየት የሚጀመረው የመለየት ሥራ ሙሉ ወጪውን የሚሸፍነው የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚንስቴር፤ 132 ሚሊዮን ብር በጀት የመደበልን ሲሆን ተቋሙ ከሌሎች አገራቶች ጋር በትብብር የምንሠራቸው ፕሮጀክቶች እና የአፈርን ለምነት በሚጨምሩ ማዕድናት ጋርም የምንሠራው ሥራ ሰፊ አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ማዕድናቱን ለማግኘት ባለፈ አመላካች ሥራ ስንሠራ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ የመለየት ሥራ ግን መጠኑንም ለማወቅ እየተዘጋጀን ነው የሚሉት ታምሩ፣ ይህ ሥራ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሬን የሚያስገኝ ይሆናል። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ አገራት ጋር የትብብር ሥራ በመሥራት ዘመናዊ መሣርያዎችን መጠቀም አለብንም ብለዋል።

የማዕድንና ኢነርጂ ሚንስቴር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሚካኤል መንገሻ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገት የኢትዮጰያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የሚሠራው ማዕድናትን የመለየት ሥራ መጀመሩ የሚደገፍ ነገር ነው። በአካባቢው ላሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባለፈ አገሪቱ አሁን ላይ እያጣች ያለውን የውጪ ምንዛሬ እንድታገኝ ይረዳታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ለኢንዱስትሪ፣ ለኮንስትራክሽን፤ ለግብርና እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች ግብዓት የሚሆኑ መረጃ የሚያመነጭ ሲሆን የአገሪቱን ሥነ ምድር መረጃ ቀልጣፋ በመሆን የጂኦ ሳይንስ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here