ብርሃን እና ሰላም በጋዜጦች ላይ የኅትመት ዋጋ ጭማሪ አደረገ

0
821

ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በጋዜጦች መጠን እና የኅትመት ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉ ታወቀ።
ድርጅቱ ለጋዜጣ እና ለሌሎች ኅትመቶች የሚውል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆን የወረቀት ግብዓት ከውጪ አገራት እንደሚያስገባ የተገለጸ ሲሆን 35 በ 45 ሳንቲ ሜትር የኅትመት መጠን የሚታተሙ ጋዜጦችን ለማተም የሚጠቀምበት የወረቀት ክምችት በማለቁ የኅትመት መጠኑን 42 በ 30 ሳንቲ ሜትር ለማሳደግ መገደዱን ገልጿል።

በመሆኑም ጋዜጦቹ የሚታተሙበትን የገጽ እና ጠቅላላ ብዛት መሰረት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ መገደጉን የድርጅቱ ሕዝብ ግኑኙነት ኀላፊ ዳንኤል ኀይሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጋዜጦቹን ለማተም የሚጠቀምበትን ወረቀት ለማስገባት ከዘጠኝ ወር በላይ ለንግድ ባንክ የውጪ ምንዛሬ ጥያቄ ብናቀርብም ካለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ እስካሁን ማግኘት አልቻልንም ያሉ ሲሆን በወረቀት እጥረት ምክንያት የጋዜጦቹ ሥራ ከሚስተጓጎል የተሻለ የወረቀት ክምችት ባለው 42 በ 30 ሳንቲ ሜትር ሥራውን ለማስቀጥል መወሰኑን ተናግረዋል።

ለውጡን አስመልክተን እንደ ፕሬስ ድርጅት ላሉ አሳታሚዎች ቀድመን የመጠን ለወጥ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበናል በተጨማሪም እኛጋር ለሚታተሙ ጋዜጦች በየቢሯቸው በመሔድ አሳውቀናል ያሉ ሲሆን የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አማረ አረጋዊ ለውጡ በድንገት ተደረገ ነው ምንም ዓይነት ቅድመ ማስጠንቀቂያ አልደረሰንም የመጠን ለውጡ በደንበኞቻችን ላይም ቅሬታ ፈጥሯል ይህንንም በተመለከተ ከሌሎች ጋዜጦች ጋር በተደራጀ መልኩ በጽሑፍ ጥያቄ ለማቀረብ በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል።

በጋዜጦቹ የሚነሳውን የኅትምት ጥራት ችግር በተመለከተም በማተሚያ ቤቱ የሚገኙ የኅትመት መሣሪያዎች ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ በመሆናቸው ብልሽት ሲያጋጥም አልፎ አልፎ የኅትመት ጥራት ችግር ያጋጥማል የተባለ ሲሆን ከዘመኑ ጋር የሚሔዱ አዳዲስ መሣሪያዎችን እና ለጥገና የሚውሉ ግብዓቶች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የውጪ ምንዛሬ እጥረት እክል መሆኑ ተገልጿል።

በድርጅቱ ከ17 በላይ የግል እና የመንግሥት ጋዜጦች እንደሚታተሙ የገለፁት ዳንኤል ኀይሉ የኅትመት ግብዓት ችግሩ ከተቀረፈ ከደንበኞች ጋር በመነጋገር የጋዜጦችን የኅትመት መጠን በደንበኞች ፍላጎት መሰረት ለማድረግ ማተሚያ ቤቱ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

አታሚ ድርጅቱ ከጋዜጦች በላይ እንደ ባንክ ቼክ፣ ሲፒዮ፣ የሎተሪ ቲኬት ያሉ ምስጢራዊ ኅተመቶች እንዲሁም የባቡር እና አወቶብስ ቲኬቶችን ማተም ካላቸው ብዛት አንጻር የማተሚያ ቤቱን ትልቅ ገቢ እንደሚይዝ ገልፆ ነበር።

ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በ2010 የበጀት ዓመት ከ203 ሚሊዮን ብር በላይ ያተረፈ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት በኅትመት ውጤቶች ላይ ከ60 በመቶ በላይ ጭማሪ አድርጓል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here