ባለሀብቶች ከወሰዱት የእርሻ መሬት 1 ነጥብ 2ሚሊዮን ሄክታሩ አለማም

0
397

ባለፉት ኹለት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ለሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት 2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለባለሀብቶች ቢሰጥም በተጨባጭ መልማት የቻለው 800 ሺሕ ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን አስታወቀ።

በሚኒስቴር መዓረግ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ያዕቆብ ያላ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት መሬት እና ፋይንንስ ቢቀርብም እየተገኘ ያለው ዓመታዊ አማካይ ምርት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል የዘለለ አይደለም።

የባለሥልጣኑ ጥናት እንደሚያመለክተው የተለዩ ማነቆዎች ወደ ዘርፉ ለሚገቡ አዳዲስ አልሚዎች በተሟላ ሁኔታ ወደ ልማት መግባት አለመቻልና የእርሻ ኢንቨስትመንት በሚካሔድባቸው አካባቢዎች ለልማት ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር ከችግሮቹ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ዘላቂ የአካባቢና ማኅበራዊ ደኅንነት ማዕከል ያደረገ ልማት አለማካሔድ፣ አስፈላጊውን የገበያ ትስስር በመፍጠር የሎጅስቲክ አገልግሎት እንዲሟላ አለማድረግና ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት አለመዘርጋትም የዘርፉ ችግሮች ናቸው ሲሉም አክለዋል።

ዘርፉን መንግሥትና በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት በሚገባ አለመደገፋቸው እንዳለ ሆኖ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚፈጥሩዋቸው ችግሮች መኖራቸውም ታውቋል። ከነዚህም መካከል የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው አናሳ በመሆኑ በሔክታር የሚያገኙት ምርት በአርሶ አደር ማሳ ላይ ከሚገኘው ምርት ጋር ሲነፃፀር ብዙም ፈቀቅ ያለ አለመሆን፣ በመንግሥት የሚሰጠው ማበረታቻ ለታለመለት ዓላማ አለማዋልና የተሰጠውን መሬት ለ3ኛ ወገን አሳልፎ መስጠት ጭምር ይገኙባቸዋል።

ያዕቆብ እንደሚሉት፣ ዘርፉ እነዚህን ችግሮች በመፍታት አሁን እየለማ ካለው መሬት ብቻ በዓመት በአማካይ 60 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት ይቻላል። የተለየው መሬት ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት ማስገባት ከተቻለ ደግሞ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ኩንታል የማምረት አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

በጅምር ቢሆንም በነቀምቴ አካባቢ በሔክታር 100 ኩንታል በቆሎ ማምረት ተችሏል። ራያ አካባቢ በሔክታር አንድ ሺሕ ኩንታል ቲማቲም የተገኘበት አጋጣሚም አለ። ከዚህ አንጻር ሰፋፊ እርሻዎችን በዘመናዊ መንገድ ለማምረት የተነሱት ባለሀብቶች ውጤታማ አለመሆናቸውን አመላካች ነው ብሏል ጥናቱ።

የግብርናና የእንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር)፣ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂና ግብዓት ተጠቅመን ምርታማነታችን በሦስት እጥፍ ብቻ ማሳደግ ብንችል እንኳን በዓመት አንድ ቢሊዮን ኩንታል ማምረት እንደሚቻል አስታውቀዋል።

እንደ ኢያሱ ገለጻ፣ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ መንግሥት በአንድ በኩል የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ በሌላ በኩል ደግሞ ለሰፋፊ እርሻዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ የሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፉ ግን በበርካታ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ የታሰበውን ያክል ውጤት አልታየበትም። ችግሩን ለይቶ መፍትሔ በማስቀመጥ ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ደግሞ አንድ ዓመት የፈጀ የዳሰሳ ጥናት መጠናቱንና ያንንም ወደተግባር ለመቀየር እየተሠራ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከተቋሙ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here