የቀንጢቻ ታንታለም ፋብሪካ ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ 132 ሚሊዮን ብር እርዳታ ጠየቀ

0
694

ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድረው የቀንጢቻ ታንታለም ፋብሪካ ላለፉት ኹለት ዓመታት ሥራ በማቆሙ ለሠራተኞቹ ደሞዝ እንዲሁም ለሥራ ማስጀመርያ የሚሆን 132 ሚሊዮን ብር ከገንዘብ ሚኒስቴር እርዳታ ጠየቀ።

በኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ቡልቲ ወዳጆ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ፋብሪካው ከተዘጋ አንስቶ ምንም ዓይነት ገቢ ባለማግኘቱ ላለፉት ስድስት ወራት ከመንግሥት በተገኛ 47 ሚሊዮን ብር የሠራተኞቹን ደሞዝ ሲከፍል የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ለሠራተኞቹ የሚከፍለው ገንዘብ የለውም። በመሆኑም ከሦስት ወር በፊት ለገንዘብ ሚኒስቴር ለሠራተኞቹ ደምወዝ እንዲሁም ፋብሪካው ከተከፈተ የሥራ ማንቀሳቀሻ የሚሆን እርዳታ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም “እስካሁን ምላሽ አልተሰጠንም፤ ውሳኔውን በፍጥነት ካላገኘን የአንድ ሺሕ ሠራተኞች ኅልውና አደጋ ውስጥ ገብቷል” ሲሉ አስታውቀዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ጉዳዩ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ባለ ድርሻ አካለት ጋር ምክክር እየተደረገበት እንደሆነና በአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘም በባለሙያዎች ጥናት እየተካሔደበት ነው። ሆኖም እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተገኘና መንግሥትም በዚህ ጉዳይ ፈጣን ውሳኔ ካልሰጠ በፋብሪካዎቹ ሲያገለግሉ የነበሩ ሠራተኞችን ማሰናበት ግዴታ እንደሚሆን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ተናግረዋል።

የድርጅቱን 90 በመቶ በላይ ገቢ የሚሸፍነው ከአዲስ አበባ 550 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የቀንጢቻ ፋብሪካዎች በመዘጋታቸው፣ ድርጀቱ ባለፉት 22 ወራት ከታንታለም ምርት ማግኘት የነበረበትን 520 ሚሊዮን ብር ገደማ አጥቷል።

በተጨማሪም ለውሃ ማጣርያ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን የሚያመርተው ፋብሪካው፣ አካባቢው ላይ ባለ አለመረጋጋት የተነሳ እንዲዘጋ በመደረጉ በውስጡ ያለውን 264 ቶን ምርት በመጋዘን ውስጥ ይገኛል። ሆኖም ግን ይህ ምርት በመጋዘን ውስጥ እያለ አገሪቱ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ምርቱን ከውጪ ታስገባለች። ይህ ተገቢ አይደለም ሲሉ ቡልቲ ተናግረዋል።

በ2010 በኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ በተጻፈ ደብዳቤ መሰረት የተዘጋው የታንታለም ማምረቻው፤ ዝቃጭ ማስወገጃ ግድቡ በመሙላቱ ወደ ውስጥ የሚገባው አሸዋ እና አፈር ወደ ውጭ በመፍሰስ አካባቢ እና ሰው ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ እንደተዘጋ ይታወቃል።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንገሥት በጉጂ ዞን፣ ሰባቦሮ ወረዳ በ5 ነጥብ 3 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ የተንጣለለውና ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ ማምረት እንዲያቆም ትዕዛዝ የደረሰው የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ፣ በየወሩ ወደ 10 ቶን ታንታለም ያመርት ነበር።

ለ28 ዓመታትም በምርቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ የመንግሥት ልማት ድርጀቶች አንዱ ሆኖ የቆየ ሲሆን ሥራ ካቆመ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here