መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበመስቀል አደባባይ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት 2 ሚሊዮን ብር ይከፈላል ተባለ

በመስቀል አደባባይ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት 2 ሚሊዮን ብር ይከፈላል ተባለ

ለሰርግና ለምረቃ ፕሮግራም 250 ሺሕ ብር ነው ተብሏል

በመስቀል አደባባይ የሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) ለማዘጋጀት እስከ ኹለት ሚሊዮን ብር እንደሚያስከፍል የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በአደባባዩ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለማድረግ የኪራዩ ዋጋ የተለያየ ነው የተባለ ሲሆን፤ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማድረግ ክፍያው እስከ ኹለት ሚሊዮን ብር መሆኑን የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን ታደሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ክፍያው ኹለት ሚሊዮን የሆነው ኮንሰርት ብዙ ወጪ ስለሚጠይቅ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው አክለው ተናግረዋል። ኮንሰርቶችን በተመለከተም ብዙ ሰዎች እየጠየቁና ፕሮግራም እየተያዘላቸው መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው አንስተዋል።

ሰርግን በተመለከተ እስከ አሁን ለሰርግ ፕሮግራም መጥቶ ያነጋገረን ሰው የለም ያሉት ጥላሁን፤ ለሰርግ እና ለምርቃት እስከ 250 ሺሕ ብር ነው የምናስከፍለው ብለዋል። በአደባባዩ የሰርግ ፕሮግራም ተደርጎ ባያውቅም የክፍያ መጠኑ ግን 250 ሺሕ ብር እንዲሆን መወሰናቸውን አብራርተዋል።

የምረቃ መርሃ ግብርን በተመለከተ ግን አድማስ ኮሌጅ ከዚህ በፊት በአደባባዩ ፕሮግራም አካሂዶ እንደነበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለአብነት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በአደባባይ ፎቶ ለመነሳት ክፍያው 2 ሺሕ 500 ብር መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል። ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪም የመኪና ፓርኪንግ ፓኬጅ አገልግሎት እንደሚሰጥ የተመላከተ ሲሆን፤ ክፍያውም በሰዓት 10 ብር መሆኑን ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አደባባይ ማለት በአብዛኛው ሕዝባዊ በዓላት እና የተለያዩ ኹነቶች የሚደረጉበት መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ አደባባዩን ከከተማ አስተዳደሩ ንግድ ማኅበራት ለማስተዳዳር ሲቀበሉ፣ ትልቁ ሥራቸው የተለያዩ ኹነቶች ሲዘጋጁ ፓርኪንግ ማድረግ፤ ወደ 30 የሚሆኑ ሱቆችን ለማከራየት፤ ስድስት እስከሪኖችን በቦርዱ ሥም በፓኬጅ ለማስጠቀም ነው ብለዋል።

መስቀል አደባባይ የአዲስ አበባ ትልቁ መገለጫ ነው የሚሉት ጥላሁን፤ በከተማው መሃል በፓኬጅ ደረጃ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን፤ የኮሌጅ ምርቃቶችን፤ የባንክ ዓመታዊ ሪፖርት መርሃ ግብሮችን ለማድርግ ኪራይ እንደሚያስከፍሉም ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ከላይ በተዘረዘሩት ፕሮግራሞች ተጠቃሚዎች ለኪራይ ብር ቢከፍሉም ምንም ክፍያ የማይጠይቁበት በአደባባዩ የሚደረግ መርሃ ግብር እንዳለም አንስተዋል።

ለአብነትም ሀይማኖታዊ እንዲሁም ሕዝባዊ በዓላትና ክዋኔዎች ጋር በተያያዘ በአደባባዩ ለሚደረጉ ዝግጅቶች ብር እንደማያስከፍሉ ገልጸዋል። እንዲሁም አንዳንድ ለማኅበረሰቡ የሚጠቅሙ መርሃ ግብሮች ማለትም እንደ ኦቲዝም፤ ደም ልገሳና ሌሎች መሰል መርሃ ግብሮችን ለሚያዘጋጁ አካላትም አደባባዩ ነጻ አገልግሎት እየሰጠ ነው ተብሏል።

የኑሮ ውድነቱን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እስከ አሁን የተሻሻለ የፓኬጅ ዓይነት አለመኖሩንም አክለው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በመዲናዋ ውስጥ በሚገኙ ሌሎች አዳዲስ ፓርኮች ገብቶ የሰርግ ፎቶ ለመነሳትም ክፍያው 35 ሺሕ ብር መሆኑን ማወቅ ተችሏል። ለአብነትም ወዳጅነት አደባባይ ውስጥ የሰርግ ፎቶ ለመነሳት ክፍያው 35 ሺሕ መሆኑን አዲስ ማለዳ በቦታው ያገኘቻቸው ሰዎች ተናግረዋል። ወዳጅነት አደባባይ ከዚህ በፊት ለሰርግ ፎቶ 40 ሺሕ ያስከፍል ነበር።

መስቀል አደባባይ በመንግሥትና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መካከል ክርክርን ያስነሳ መሆኑ ይታወሳል። ይኸው አደባባይ በ2.5 ቢሊዮን ብር የተደረገለት የእድሳትና የግንባታ ሥራ ሰኔ/2013 መጠናቀቁም አይዘነጋም።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች