ለማንነት ጥያቄዎች ዴሞክራሲያዊ መልስ

0
589

ኢትዮጵያ የተለያዩ ስርዓተ መንግሥታትን በተለያየ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እና በተለያየ የተፅዕኖ አድማስ ውስጥ ማለፏን የታሪክ መዛግብት እና አርኪዮሎጂያዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። በረጅሙ የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ የውጪ ወራሪ ኃይልን ለጋራ ደኅንነትና ለአገር ሉዓላዊነት ለመመከት ሲባል ብዙ ኢትዮጵያውያን መስዋትነት ከፍለውበታል። አገራዊ ሉዓላዊነትን ከውጭ ጠላት በመከላከል ላይ ያለንን ቁርጠኝነት ያክል ግን የርስ በርስ ግኙነታችን ላይ አይንፀባረቅም። ይልቁንም፣ ለንግሥና እና ለበላይነት በተደረጉ ቀደምት ትግሎች የተፈፀሙ በደሎች እና መድሎዎች እንዲሁም የተዛቡ ግንኙነቶች ላይ በመመሥረት እና እነዚህን ታሪካዊ ቁርሾዎች በመቆስቆስ ዛሬም ድረስ የፖለቲካ ዓላማ ለማስፈፀሚያነት ማዋል የተለመደ ነገር ግን መራር የፖለቲካችን ነባራዊ ሁኔታ ሆኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እዚህም እዚያም እያገረሹ ያሉት ማንነትን መሠረት ያደረጉ አቤቱታዎች ወይም ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች ለዚህ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው ብለን እናምናለን።
ከሰሞኑ የተከሰቱትን እንደምሳሌ ብንገልጽ በሞያሌ፣ በድሬዳዋ፣ በደቡብ ክልል እና በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙት ግጭቶች የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ የአካል ጉዳት ደርሷል፤ ንብረትም ወድሟል። ባሳለፍነው ሳምንትም ማንነትን ማዕከል ባደረገ ግጭት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ሦስት ተማሪዎች ተገድለዋል፤ 31 ሌሎች ደግሞ ለጉዳት መዳረጋቸው ብዙዎችን አሳዝኗል።
ዜጎች ማንነትን (ማለትም ፆታ፣ የቆዳ ቀለም፣ ቋንቋ እና/ወይም ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ማኅበራዊ አመጣጥን፣ ውልደትን፣ የፖለቲካ አመለካከትን ወይም ሌላ መለያን) መሠረት ካደረገ ማናቸውም ዓይነት ጥቃት፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም አስተዳደራዊ መገለል ወይም በደል ሊፈፀምባቸው አይገባም። ይህም መብት ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው የሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎች – በተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ፣ የአፍሪካ የሰብኣዊ እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር – እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጥበቃ እንደሚደረግለት የተወሰነ ነው።
ይሁንና አሁንም በሚያሳዝን ሁኔታ በማንነታቸው ምክንያት በተለያዩ መንገዶች መገለል እና መድልዖ እየተደረገባቸው እንደሆነ የሚሰማቸው ዜጎች አሉ። ይሁንና የማንነት ጥያቄዎች ሲነሱ በአንድ በኩል አፈና ይደርስባቸዋል። በሌላ በኩል የፖለቲካ ልኂቃን ከሚገባው በላይ ለጥጠውት የግጭት መንስዔ ከማድረግም ባሻገር፣ የማይታረቁ ልዩነቶች እያስመሰሉ ግጭቶቹን ያጋግሉታል።
የማንነት ጥያቄዎችን በቀናነት ማስተናገድ እና ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ማፈላለግ ሁለት ጠቀሜታዎች አሉት። አንደኛው በማናቸውም ሁኔታ መገሰስ የሌለባቸውን የሰብኣዊ መብቶችን ማክበር ሲሆን፣ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግሮች ለዘለቄታው መፍትሔ ይሆናል።
የፖለቲካ ልኂቃን በኢትዮጵያ ያሉትን የማንነት ጥያቄዎች የሚበይኑበት ምልከታ በራሱ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ እናምናለን። ልኂቃኑ የማንነትን ብያኔ የገዢ እና ተገዢ፣ የጨቋኝ እና ተጨቋኝ፣ የበላይ እና የበታች፣ የተጠቃሚ እና የተበዝባዥ፣ የበይ እና የበይ ተመልካች ሁለትዮሽ ግንኙነት ብቻ ወደ መፍትሔው በመቅረብ ፈንታ የችግሩን ትክክለኛ ምንጭ ለመረዳት በሚያስቸግር መልኩ መፍትሔውም እንዳይገኝ እንቅፋት እየሆነ ነው።
ችግሩን በተሳሳተ መንገድ መበየን መፍትሔውንም በተሳሳተ መንገድ ለመበየን ዳርጓል። ብዙ የፖለቲካ ልኂቃን ብሔርተኝነትን ለማንነት ጥያቄዎች ብቸኛው መልስ ማግኛ መፍትሔ በማድረግ “የእኛ” እና “የእነሱ” የሚል ክፍፍል በማበረታታት እና የቂም በቀል ተረኮችን በማግነን ቅራኔዎችን እያባባሱ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሥልጣን መሠረቱ የዘውግ ማንነት መሆኑ በአንድ በኩል፣ የተለያዩ ክልሎች ሕገ መንግሥታት የክልል “መሥራች” የሚሏቸው የተወሰኑ የዘውግ አባላትን ብቻ መሆኑ በሌላ በኩል ይህንን “የእኛ” እና “የእነርሱ” ቅራኔ ከማባባሱም ባሻገር የሌሎች ዜጎችን ተዘዋውሮ የመሥራት እና የመኖር ሰብኣዊ መብቶች እንዳይከበሩ እንዲሁም የመምረጥ እና የመመረጥ ብሎም እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ባለማስገኘቱ የልዩነት እና የግጭት መንስዔ እየሆነ ነው። በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ የማንነት ቡድን የራሱን ዞን፣ ክልል ወይም አስተዳደር ወሰን በማግኘት የተጠቃሚነት አድማሱን ማስፋት እንዲፈልግ ሆኗል። ይህም የምጣኔ ሀብት ጥያቄዎችን የማንነት መልክ እንዲሰጡ ሰበብ ሆኗል።
ኢትዮጵያን ከዚህ ፈታኝ ሁኔታ ለማውጣት እና ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ለጥቃት እና መድልዖ ተጋላጭ የማይሆኑበትን ስርዓት ለመዘርጋት የመጀመሪያው እርምጃ የፖለቲካዊም ይሁን የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት በተለይም ዜጎች በምርጫቸው በማይወስኑት ነገር ግን በደም ቆጠራ በሚገኝ የማንነት ብያኔ እንዳይኖር እና ሕጋዊ ከለላ እንዲደረግለት ማድረግ ነው። በመቀጠልም ሕዝባዊ ተሳትፎን ያረጋገጠ ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ መፍትሔን ተፈፃሚ ማድረግ ያስፈልጋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here