የብርቱካን ሚዴቅሳ ሹመት ቀጣይነት አጠራጣሪ ሊሆን ይችላል

0
758

የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ ሲሻሻል የቦርዱ አባላት አባል ከመሆናቸው በፊት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ያላደረጉ መሆን እንደሚገባቸው የሚያደነግግ አማራጭ ሐሳብ አቀረበ።
ጉባኤው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር 13 የሕግ ምሁራን እና የህግ ባለሙያዎች ስብስብ የተዋቀረ ሲሆን፣ በተቀናጀ መልኩ የሕግ እና የፍትሕ ስርዓት ተሐድሶ ለማድረግ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉን እንዲያማክር የተቋቋመ ነው። ጉባኤው በሥሩ የተለያዩ ሕጎችን ለማሻሻል ጥናት እና ምርምር አድርገው በሥራ ላይ ያሉ ሕጎችን የሚያሻሽሉና አዲስ የሕግ ማዕቀፎችን የሚጠቁሙ የሥራ ቡድኖችን አዋቅሮ በመሥራት ላይ ይገኛል። ጉባኤው ከለያቸው ስምንት የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን እና የእምባ ጠባቂ ተቋም ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ውስጥ ያሉ የአቅም እና የተአማኒነት ዙሪያ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶችን ለማሻሻል የተዋቀረው የሥራ ቡድን ይገኝበታል። በዚህ ቡድን የማሻሻያ ጥናት እየተደረገባቸው ካሉ ሕጎች መካከል የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንዱ ነው።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብርቱካን ሚዴቅሳን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ በሾመበት ዕለት ሐሙስ፣ ኅዳር 13 የጉባኤው የዴሞክራሲ ተቋማት የሥራ ቡድን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ ማሻሻያ ዙሪያ ከባለድርሻዎች ጋር ውይይት ሲያደርግ ውሏል። በውይይቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፣ የምርጫ ቦርድ እና የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተወካዮች ተገኝተው ነበር።
በውይይቱ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ውይይቱ በሚደረግበት በተመሳሳይ ሰዓት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ቦርድን ሰብሳቢ ሹመት ለማፅደቅ መቀመጡ ውይይቱን ውጤት አልባ አያደርገውም ወይ የሚለው ይገኝበታል። ለጉዳዩ ከመድረክ የተሰጠው ምላሽ የሕግ ማሻሻያው ወደፊት በአገራችን ለሚኖረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሠረት የሚሆኑ አማራጭ ሐሳቦችን ማቅረብ በመሆኑ አሁን የተደረገው ሹመት ላይ ምንም ማለት እንደማይቻል ነው።
በውይይቱ ከቀረቡ የመነሻ ሐሳቦች መካከል የቦርዱ አባላት ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ አባላቱ የፖለቲካ ድርጅቶች አባል ያለመሆናቸው፣ የፖለቲካ ድርጅቶች አባል ሆነው አለማወቃቸው ወይንም በሕግ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎ ያልነበራቸው መሆናቸውን የሚደነግጉ አማራጮች ይገኙበታል። ይህም ማለት አንድ ለምርጫ ቦርድ አባል ለመሆን የሚታጭ ሰው በወቅቱ የፖለቲካ ድርጅት አባል ካለመሆን ባለፈ በቀደመ ሕይወቱ ያደረገው የፖለቲካ ተሳትፎ ከግምት ሊገባ የሚችልበትን ሁኔታ ይጠቁማል።
በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚንስትሩ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሆኑ ብርቱካን ሚዴቅሳን ለፓርላማው በእጩነት ባቀረቡበት ወቅት ከፓርላማ አባላት የተነሱት ጥያቄዎች ግለሰቧ የነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። አንድ የፓርላማ አባል “ግለሰቧ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ለማጣራት ምን ተደርጓል?” ብለው ሲጠይቁ ሌላው ደግሞ “ከ1997ቱ ምርጫ ጋር ተያይዞ ከነበራቸው ሚና አንፃር ገለልተኝነታቸው እንዴት ይታያል?” ሲሉ ጠይቀዋል። ምክር ቤቱ በ330 ድጋፍ፣ በአራት ተቃውሞ እና በሦስት ድምፀ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ የብርቱካን ሚዴቅሳን ሹመት ቢያፀድቅም የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ የሚያቀርበው የሕግ ማዕቀፍ ምን ዓይነት አቋም ይዞ እንደሚወጣ ለማወቅ ጊዜው ገና መሆኑ ጉዳዩን አጓጊ አድርጎታል።
በዚህ ነጥብ ላይ ጉባዔው ባዘጋጀው ውይይት ወቅት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች የቦርዱን አባላት ገለልተኝነት መረጋገጥ እንዳለበት አፅንዖት ሰጥቶ ከመናገር ውጪ የቀረቡት አማራጮች ላይ አቋም እንዳልያዙም ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀ መንበር ይልቃል ጌትነት እንደሚሉት ሰው ማኅበራዊ እንስሳ እንደመሆኑ መጠን ፖለቲካዊ አቋም ከመያዝ ሊገደብ ስለማይችል በሕግ ማዕቀፉ ውስጥ ጥብቅ ክልከላ ማድረግ ብቻውን የቦርዱን አባላት ገለልተኝነት አያረገግጥም። “ከዛ ይልቅ” ይላሉ ይልቃል “የቦርዱ አባላት በሕይወታቸው ያሳዩት ግለሰባዊ ባሕሪ እና ሕግ አክባሪነት መታየት ይኖርበታል። በተጨማሪም ከግለሰባዊ ገለልተኝነት በላይ ላለፉት ዓመታት በአገራችን ችግር ሆኖ የቆየው የምርጫ ቦርድ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ የገዢው ፓርቲን ዓላማ ማስፈፀሚያ መሆኑ ነው። ገለልተኛ የሚባል ሰው ራሱ የቦርዱ አባል ወይም ሰብሳቢ ሆኖ ቢገባ የሚያሰራው መዋቅር አልነበረም።”
የኢዴፓ ሊቀ መንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) የገለልተኝነት ጉዳይ ወሳኝ ቢሆንም በተለይም አሁን የተመረጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ላለፉት ረጅም ዓመታት ከፖለቲካ ተሳትፎ ርቀው መቆየታቸውን እንደሚያውቁና ለሕግ የበላይነት ካላቸው ቁርጠኝነት አንፃር ያለ መድሎ ሊሠሩ ይችላሉ ብለው እንሚያምኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይልቃል ጌትነት እንደሚሉት የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች የቦርድ አባል ሆነው ቢመረጡ እንኳን እንደ ገዢው ፓርቲ የአስፈፃሚና የደኅንነት ተቋማትን ስለማይቆጣጠሩ ምርጫውን የማጭበርበር እና ተፅዕኖ የማሳደር አቅም አይኖራቸውም። ይልቃል እንደተናገሩት ጉዳዩ አሳሳቢ የሚሆነው አባላቱ የገዢው ፓርቲ አባል ሆነው በቀጥታ ትዕዛዝ የሚቀበሉ ሲሆኑ እንጂ የተዋሚ ፓርቲ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች መንግሥትን የማጭበርበር ጉልበት አይኖራቸውም።
በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ መሰንበት አሰፋ (ዶ/ር) “የሕግ ማዕቀፉ ምርጫ ቦርድ አባል የሚሆኑ ግለሰቦችን የፖለቲካ ተሳትፎ መገደብ የሚችለው ከተቋማዊ የአባልነትታቸው አንፃር ብቻ ነው። ግለሰቦቹ በግላቸው ከሚይዙት የፖለቲካ አቋም መገደብ የማይቻል ስለሆነ የቦርዱ አባላት የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልነበሩ መሆን አለባቸው የሚል ሕግ ቢኖር እንኳን የአባላቱን ግለሰባዊ አቋም መቆጣጠር አይቻልም። ስለሆነም ትኩረት መደረግ የሚገባው በአባላቱ የሙያ ብቃት፣ በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተዓማኒነት እና ሕግን የማስከበር ቁርጠኝነት ላይ ነው” ብለዋል።
የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ የምርጫ አዋጁን ሲያሻሽል የምርጫ ቦርድ አባላት አዋጁንም ጨምሮ የምርጫ ቦርድን አደረጃጀት እና ስያሜ እንዲሁም ተቋማዊ ቅርፅ ላይ ማሻሻያ ሐሳቦችን አቅርቦ ለባለድርሻ አካላት የሚያወያይ ሲሆን ተቀባይነት ያገኙ ማሻሻያዎች በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርበው በፓርላማ የሚፀድቁ ይሆናል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here