ዳሰሳ ዘ ማለዳ ሐሙስ መስከረም 22/2012

0
833

 

1- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ከጋንቤላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ የአሳ ማቀነባበርና ግብይት ማዕከል ማቋቋምና ዘላቂ ልማት ፕሮጀክትን ወደ ተግባር ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታዉቋል።ፕሮጀክቱ የክልሉን የዓሳ ሃብት ልማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ የክልሉን ዩኒቨርሲቲ የአገሪቱን የዓሳ ሃብት ልማት የልህቀት ማዕከል በማድረግና የዓሳ ፍላጎትን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት በዘርፉ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዲኤታ ጀማል በክር ገልጸዋል።(አዲስ ማለዳ)

………………………………………………

2–የሱዳን ዜግነት ያለዉ አንድ ግለሰብ ትላንት መስከረም 21/2012 1300 የክላሽ ጥይት ከሰሜን ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ሊገባ ሲል በጅማ ጉምሩክ አልመሀል መቆጣጠሪያ ጣቢያ በጣቢያዉ ሠራተኞች እና በፌደራል ፖሊስ ትብብር በቁጥጥር ስር ውሏል።የኅብረተሰቡን ሰላም የሚያደፈርሱና የሚያውኩ ሕገ ወጥ መሳሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስ ከሕግ እንደማያስመልጥ በማሰብ ሕገወጦች ከዚህ መሰል ተግባር መታቀብ እንዳለባቸው የገቢዎች ሚኒስቴር አሳስቧል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………

3- የኢፌዲሪ ገንዘብ ሚኒስቴርና የዐረብ ኢኮኖሚ ልማት በአፍሪካ በኢትዮጵያ የአግሮ ፕሮሰስ መርሃ ግብር በተመለከተ  ከአፍሪካ  ልማት ባንከ ጋር በጋራ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የስምምነት ፊርማ ተፈራረሙ ።(አዲስ ማለዳ)

………………………………………………

4-በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት  ቤት የተገነባው የቁስቋም ብርሃን የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ፣ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር  ታከለ ኡማ እና ሌሎች የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ መስከረም 22/2012  ተመርቋል። የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከሉ 12 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን 96 ህፃናትን ተቀብሎ የሚያስተናግደው ይህ ማዕከል በውስጡ ላይብረሪ ፣ የመኝታ ክፍሎች ፣ የመመገቢያ አዳራሽ ፣ ምቹ የመማሪያ ክፍሎች እና ሰፊ የመጫወቻ ቦታን ያካተተ ነው።(አዲስ ማለዳ)

………………………………………………

5-«በሕዝብ ትግል የተገኘው ውጤት በጥቂቶች ሊቀለበስ አይገባም»በሚል 70 የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ከጥቅምት 5 እስከ 6 የረሐብ አድማ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን  አስታወቁ። ፖለቲከኞቹ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓመቱን መደበኛ ሥራ በሚጀምርበት ጊዜ ስለ ምርጫ አዋጁ ያቀረብነውን ሐሳብ ተቀብሎ ካልመከረ በረሐብ አድማው እንቀጥልበታለን ብለዋል። ሌሎች ሠላማዊ የትግል ስልቶችንም እንከተላለን ሲሉ አክለዋል።(ዶች ቬሌ)

………………………………………………

6-በተጠናቀቀው ዓመት 2011  የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 7 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚገመት ስራ መከናወኑን ዛሬ መስከረም 22/2012 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ ተገልጿል።በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 12 ነጥብ 7 ሚሊየን ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዶ 12 ነጥብ 9 ሚሊየን ወጣቶች ማሳተፍ የተቻለ ሲሆን በ13 መስኮች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መሰጠቱን ታዉቋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

………………………………………………

7-በትግራይ ክልል ‘ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ'(ዓዴፓ) የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ተመስርቶ መንቀሳቀስ ጀመረ። የፖለቲካ ድርጅቱ በዋነኝነት የኢሮብ ብሔረሰብ አባላት በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ይዞ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ መሆኑ ተገልጿል።(ዶች ቬሌ)

………………………………………………

8- የሕዝብ ቤተ መፃህፍትን ወደ ዲጂታል የመቀየርና ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ አስታወቀ።እንደ አገር የትውልዱን የንባብ ባህል ለማሳደግ ጠቃሚ የሆኑ መፃሕፍትን በዲጂታል መንገድ ለመቀየር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር  ሽመልስ ታዩ ገልጸዋል።(ኢቢሲ)

……………………………………………………………………….

9-  በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በ2011 በጀት ዓመት 53 ነጥብ 3 ቢሊዮን  ብር አተረፉ። 69 ነጥብ 5 ከታክስ በፊት ለማትረፍ ታቅዶ ነበር። (አዲስ ማለዳ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here