የኢትዮጵያ ቤተ- እስራኤሎች 5780ኛ አዲስ ዓመታቸውን አከበሩ

0
466

ቤተ- እስራኤላዉያንን ጨምሮ አይሁዳዉያን 5780ኛ «ሮሽ ሃሻናህ» በአማርኛ «ርዕሰ ዓመት» አዲስ ዓመታቸዉን ከመስከረም 18 እስከ መስከረም 21/2012 ድረስ አክብረዋል።

አይሁዶች በተለይ ወራቸዉን በጨረቃ ዓመታቸዉን በፀሃይ ይቆጥራሉ ያሉት የኢትዮጵያውያን ቤተ- እስራኤላዉያን የመብት ተሟጋችና አክቲቪስት መስፍን አሰፋ፣ እናም በጨረቃ አቆጣጠር መስከረም 18 ቀን አዲስ ዓመታቸዉን ያከብራሉ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ይህ ማለት፤ በፀሃይ መስከረም ሁለት፤ በጨረቃዉ መስከረም 18 አዲስ ዓመታቸዉ ነዉ ብለዋል።

«የአይሁዳዉያን አዲስ ዓመት አከባበር ከኢትዮጵያ እንቁጣጣሽ አከባበር ጋር ፈፅሞ የሚገናኝ አይደለም። አይሁዳዉያን አዲስ ዓመትን የምናከብረዉ በመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ መሰረት ነዉ። በአከባበሩ የመግብያ ፀሎቶች ይካሄዳሉ፤ መጭዉ ዘመን የተባረከና ጣፋጭ እንዲሆን ጣፋጭ የሆኑ ነገሮችን በመብላት አዲስ ዓመትን እናከብራለን። አዲስ ዓመትን «ሾፋር» በመንፋት ማለትም መለከት በመንፋት እናከብራለን።» ሲሉም አክለዋል።

በአይሁዳዉያን አዲስ ዓመት «የእስራኤል ህዝብ የበላይ እንጂ የበታች አታድርገን፤ «ራስ እንጂ ጅራት አታድርገን» በሚለዉ ስርዓቱ ከእርድ በኋላ የበጉን ጭንቅላት በመያዝ ፀሎት ይደረጋል። አምላክ በመጭዉ ዘመን ራስ እንጂ ጅራት እንዳያደርገን፤ ከሁሉ በላይ እንጂ በታች እንዳያደርገን በሚል ስርዓት እርድ ያከናውናሉ ይጸልያሉ።» ሲሉም ትውፊቱን ያወጋሉ።

ከትላንት አርብ ምስከረም 23/2012 ጀምሮ እስከ ሰኞ መስከረም 26/2012 ድረስ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ወጥተው ወደ ከነዓን ምድር የገቡበትን የዳስ በዓል (ሱኮት) በማከበር ላይ እንደሚገኝም አክቲቪስት መስፍን ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here