መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየአዋሽ - ኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ከሥራ ተቋራጩ ጋር...

የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ከሥራ ተቋራጩ ጋር ድርድር እየተደረገ ነው

ድርድሩ ካልተሳካ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሊያቀና ይችላል

የተቋረጠውን የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ከሥራ ተቋራጩ ያፒ መርከዚ ጋር ድርድር እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር አብዱልከሪም መሐመድ፣ የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ በጦርነቱ በደረሰበት ውደመት የሥራ ውሉን አቋርጦ ወደ አገሩ መመለሱን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ተመልሶ ወደ ሥራ እንዲገባ ድርድር እየተደረገ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰበት የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ሆኖም የጉዳት መጠኑን የሚያውቀው የሥራ ተቋራጩ ነው ብለዋል። በመሠረተ ልማት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት በማካሄድ ላይ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

ኮሚቴው ሥራ ተቋራጩ ወድመት ደረሰብኝ ብሎ ያቀረበውን የገንዘብ መጠን ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን እያጠና ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የገንዘብ መጠኑ ብዙ ስለሆነና መረጃዎችን ማጠናቀር ስለሚያስፈልግም የድርድር ሂደቱ ብዙ ጊዜ ይወስዳል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ኹለት ነገሮች ሊሟሉ ይገባል የተባለ ሲሆን፣ የመጀመሪያውም ድርድሩ በስምምነት ማለቅ ከቻለ ነው። ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ይሄድና ረዥም ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ነው የተባለው።

ኹለተኛው መሟላት ያለበት ሁኔታ ደግሞ ስምምነት የተፈጸመበትን የገንዘብ መጠን መክፈል የሚችል አቅም ካለ መሆኑ ተመላክቷል። ይሁን እንጂ የተጠየቀው ገንዘብ ይከፈላል አይከፈልም የሚለውን የሚወስኑት የበላይ አካላት ናቸው ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል።

ስለሆነም ፕሮጀክቱ መቼ እንደሚጠናቀቅ ሊታወቅ አልያም ሊገመት የሚችለው እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር መነሻ በጀት ተይዞለት፣ ግንባታው በኹለት ምዕራፍ ተከፍሎ ሲከናወን የቆየ ነበር።

በዚህም ምዕራፍ አንድ ከአዋሽ ኮምቦልቻ 270 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሆኖ፣ ሥራው ያለቀው ከኹለት ዓመት በፊት ነው። ይሁን እንጂ የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ እስከዛሬ ድረስ አገልግሎት መስጠት አልጀመረም። አጠቃላይ አፈጻጸሙም የኃይል አቅርቦት ብቻ ስለሚቀረው 99 በመቶ መድረሱ ነው የተገለጸው።

ኹለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ከኮምቦልቻ ወልድያ (ሃራ ገበያ) ድረስ ሲሆን፣ 120 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑ ተመላክቷል። ይህም አፈጻጸሙ 84 በመቶ ነው። አጠቃላይ የኹለቱ ምዕራፍ ተጠቃሎ 94 በመቶ ሊደርስ እንደቻለም ለማወቅ ተችሏል።

መጠናቀቂያ ጊዜው የነበረው ምዕራፍ አንድ በታቀደለት ጊዜ ቢጠናቀቅም የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ አልቋል ማለት በማይቻልበት ሁኔታ ላይ እንዳለ ነው የተገለጸው። በአንጻሩ ምዕራፍ ኹለት የፕሮጀክቱ ግንባታ ጦርነቱ ባይኖር ኖሮ ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደነበር ተመላክቷል።

ፕሮጀክቱ አሁን ላይ በአፋር ልዩ ኃይልና በፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ እየተደረገለት እንደሚገኝም ተነግሯል። የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት (AKH Railway Project) በቱርኩ የግንባታ ድርጅት ያፒ መርከዚ (Yapi Merkezi) በመገንባት ላይ የነበረ ሲሆን፣ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በኮንትራክተሩ ንብረትና በባቡር መሠረተ ልማቱ ላይ በደረሰ ጉዳት ተቋርጧል። ፕሮጀክቱ በጦርነቱ ጉዳት ካስተናገደ በኋላ ያፒ መርከዚ ሠራተኞቹን አሰናብቶ ከኢትዮጵያ ወጥቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች