መነሻ ገጽሌሎችማኅበረሰብ አንቂ – የተከፈለበትአገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል

አገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል

ርዕይውን የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች የበለጠ ተስማምተው እና ትርጉም ያለው ውህደት ሲኖሩ ማየት ያደረገው የብሔራዊ እና ቀጠናዊ ውኅደት ጥናት ማዕከል (Center for National and Regional Integration Studies/CeNRIS/) ሰኔ 14 ቀን 2011ዓ/ም አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሆኖ ተመሰረተ።

የጥናት ማዕከሉ በዋናነት በአገር ዐቀፍና በክፍለ አህጉር ደረጃ በሰላምና መግባባት፣ በዴሞክራሲና አካታችነት ላይ እንዲሁም ፖሊሲ አግባብነት ያላቸውን የምርምርና ፕሮጀክቶች ዙሪያ በትኩረት በመሥራት ላይ ይገኛል።

በዚህ ገጽ ላይ የተካተቱት ሐሳቦች የብሔራዊ እና ክፍለ አህጉራዊ ውህደት ጥናት ማዕከልን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

በትውልድ መካከል ያለን ልዩነት ማጥበብ

አገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ማዕከል በቅርቡ ፖለቲካ አዋቂዎች፣ ተማሪዎች፣ ጋዜጠኞችንና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማካተት ባካሄደው መድረክ በቀደመውና በአዲሱ የፖለቲካ ትውልድ መካከል ያለን ልዩነት እንዴት ማጥበብ (Bridging the divided between the old and the new political generation) እንደሚቻል ምክረ ሃሳቦችና ውይይቶች ተካሂደዋል።

በዚህም በተለይ ከአብዮቱ ቀደምና በአብዮቱ ወቅት የነበረው ትወልድ፣ ከአብዮት በኋላ (post revolutionary generation) ካለው ትውልድ ጋር ሰፋ ያሉ ልዩነቶች እንደሚስተዋሉበትና ይህም ጠንካራ አገረ መንግስት በመገንባቱ ሂደት ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር መኖሩ ተነስቷል።

በየትኛውም ጊዜ ውስጥ የነበሩ ትውልዶች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በማጥበብ ወደ ጋራ አገራዊ ዓለማ እንዲመጡ በርካታ ሥራዎች መሰራት እንደሚኖርባቸው ታምኖበታል። በዚህም በመድረኩ ላይ የነበሩ ተሳታፊዎች በርካታ ሃሳቦችን ያነሱ ሲሆን፣ ለአብነትም የትምህርት ተቋማት በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የውይይትና የሰላም የምርምር ማዕከል መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ፣ የትምህርት ተቋማት ኢ-ፍትሃዊነትን የማይታገስና በውይይት የሚያምን ስልጡን ማህበረሰብ መፍጠር ተቀዳሚው ተግባራቸው ሆኖ ሳለ በአሁኑ ወቅት እያደረጉት ያለው ከዚህ ጋር የሚስማማ ድርጊት ነው ለማለት ግን እንደማይቻል ተመላክቷል።

ከትውልድ እየተንከባለሉ የመጡ አሁን ላይም ይሁን ወደፊት የሚኖሩ ትውስታዎች በራሳቸው የትናንትን ችግር ለመዘንጋት እድል የማይሰጡ በመሆናቸው፣ ስርየት እንዲያገኙና እንዲሽሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የተገለጸው። ይህንም የተጎዱት ፍትህ እዲያገኙ በማድረግና ተቀራርቦ በመነጋገር የትናንት ችግሮች እንዲሽሩ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ስለመኖሩ ሳይጠቀስ አላለፈም።

በትውልድ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ ከምንም በፊት በየጊዜው ውይይቶች መደረግ ያለባቸው ሲሆን፣ ውይይቶች በስፋትና በጥቅልቀት መደረግ ያለባቸው ግን እውነታውን ለማወቅ በማለም ሳይሆን አንዳችን ለሌላችን እውቅና ለመሰጣጠትና የትናንት ቁስሎችን ለማድረቅ ነው።
በድሮውና በአሁኑ ትውልድ መካከል ለውጦች ተፈጥረዋል። እነዚህ ለውጦችም በመካከል ያለውን ልዩነት እንዲሰፋ ያደረጉት ሲሆን፣ ባለፈውና በአሁኑ ትውልድ መካከል ያለው ግንኙነት ተቋርጧል ወይስ ግንኙነት አለ የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።

ለዚህም እርግጠኛ ሆኖ መልስ መስጠት ባይቻልም፣ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያኛው ትውልድና አሁን ያለው ትውልድ ተመሳሳይ ዕይታ አለው ብሎ መውስድ አስቸጋሪ ነው። ተመሳሳይ ባይሆን እንኳን በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ ዕይታ ስለመኖሩም ለማወቅ ጥናቶችን ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

በትውልድ መካከል የሚፈጠር ልዩነት በኢትዮጵያ ያለ ብቻ ችግር ሳይሆን በተለያዩ ወቅቶች ዓለምን ያዳረሰ እክል ስለመሆኑ በመድረኩ ተነስቷል። ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ፣ በ1960ዎቹ የነበረውን ያደጉ ካፒታሊስት አገራት ወጣቶች አመለካከት በእጅጉ በመቀየር ከቀደመው ትውልድ ጋር ሰፊ ልዩነት እንዲኖረው ያደረጉ ክስተቶች መኖራቸው ነው የተጠቀሰው።

ለአብነትም የቬትናም ጦርነት፣ የላቲን አሜሪካ አገራት ማህበራዊ አብዮት (social revolution)፣ የአፍሪካ አገራት የነጻነት ትግል እንቅስቃሴ በእነዚያ በቅኝ ግዛት እና በብዝበዛ በሚያምኑ አገራት ወጣቶች ላይ ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ ፈጥሯል ነው የተባለው።
በተጨማሪም ቴክኖሎጂ፣ የፖለቲካ አብዮት እንቅስቃሴዎች፣ የማህበራዊ ህይወት የለውጥ እንቅስቃሴዎች፣ የአንድን ዘመን ትውልድ አመለካከት ተፅዕኖ በማሳረፍ በቀደመውና ባለው መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።

መሰል ድርጊቶች በዓለም ላይ በነበሩ የየዘመናት ትውልዶች መካከል የአመለካከት ልዩነት የፈጠረ ሲሆን፣ ለማጣቀሻ ይሆን ዘንድም በፊት ፍልስጤማውያን በእስራኤሎች በየጊዜው ሲገደሉ አውሮፓ ውስጥ ታላላቅ ሰልፎች ይደረጉ ነበር። አሁን ግድያው እንደቀጠለ ይሁን እንጂ የፍልስጤማውያን ግድያ ይቁም ብሎ ማንም ሰልፍ አይወጣም። ስለዚህም በፊት ይሰለፍ የነበረው ህዝብ አሁን ለምን ዝም አለ የሚለውን መተንተን ተገቢ ይሆናል።

በኢትዮጵያም ትውልዱ በእነዚህ ተፅዕኖ ውስጥ መግባቱና የአመለካከት ለውጥ መኖሩ አይካድም። በተለይ በንጉሡ ዘመን የነበረው ትውልድ አለምዓቀፍ ትስስርና ዕሳቤ እንደነበረው ተነስቷል። ለአብነትም የአፍሪካና የሌሎች ጥቁሮችን የትግል እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ የፍልስጤማውያንን ግድያና የቬትናም ጦርነትን አጀንዳ ማድረግ ያገባኛል የሚል እና መሰል አለም አቀፍ ሁነቶችን የሚቃረንና የሚደግፍ ትውልድ በአንድ ወቅት እንደነበር ተጠቅሷል።

በአንጻሩ አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ ከዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ጋር መጓዙ ቀርቶ፣ አገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ እንኳን በደንብ መግባባት የማይችልና ወደ ጎሳ የወረደ አመለካከት የያዘ ስለመሆኑ ሳይጠቀስ አላለፈም። ይሁን እንጂ የአሁኑም ትውልድ ወደደም ጠላም ከተፅዕኖ ነጻ ሆኖ ጠንካራ አገር ለመመስረት ወደዚያ መግባት እንዳለበት ነው የተነሳው።

- ይከተሉን -Social Media

በትውልድ መካከል ሁሌም ለውጥ አለ፣ ለውጡም የሚያስከትለው ውጤት አለ። በዓለም ላይ ከ100 ዓመታት በፊት የሴቶች መብት ጥያቄ ያነሳው ትውልድና አሁን ያለው ትውልድ በዚሁ የሴቶች መብት ጥያቄ ላይ ያለው አመለካከት ተመሳሳይ አይደለም። መጀመሪያ ጥያቄው ሲነሳ የጥያቄው አራማጆች ለእስር ተዳርገው ነበር። ጥያቄው ተቀባይነት ለማግኘትም በርካታ አመታትን አልፏል። አሁን ላይ በዓለም ላይ ብዙ ፈተና አልፎ የመጣው የሴቶች መብት ጥያቄ የተከበረ ጥያቄ ነው።

ሆኖም ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ የተከበረ ቢሆንም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ፈቷል ማለት ባይቻልም በትውልድ መካከል የአመለካከት ለውጥ እንዲኖር ግን ምክንያት ሆኗል። ሌሎች እንደ ቅኝ ግዛት እሳቤዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ዕሳቤ እና በየጊዜው የሚነሱ የመብት ጥያቄዎች ባለፈውና አሁን ባለው፣ ወደፊት በሚመጣውም ትውልድ መካከል ልዩነት እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው።

በመድረኩ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያው ጥያቄ አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ የትውልድ ገፅታ ስለመኖሩ ምላሽ የሚጠይቅ ነበር።

ለዚህ ጥያቄ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች አሁን ያለው የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ የትናንት ትወልድ ገፅታ አለው ብለው የሚያምኑ ሲሆን፣ ጥቂቶች ደግሞ ችግሮችን በምርጫችን ራሳችን የፈጠርናቸው እንጂ ከዚያኛው ትውልድ የተቀበልናቸው ናቸው ብለው አያምኑም።

ለዚህም ማሳያ የሚሉትን ሲያስቀምጡ፣ የትውልዱ የአርቆ አሳቢነት ማነስ፣ የመነጋገር ፍላጎትና ልምድ አለመኖር፣ የቡድን ዕሳቤ መኖር እንዲሁም ፖለቲካ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች አገር ለማገልገል ሳይሆን የግል ሀብት ለማካበትና ጥቅማቸውን ለማሳካት (political entrepreneur) የሚገቡ መሆናቸው ነው ብለዋል።

በአንጻሩ ከትናንቱ ትውልድ የወረስናቸው ጉዳዮች ለዛሬው የፖለቲካ ቀውስ ዳርገውናል የሚል እምነት ያላቸው ተሳታፊዎች፣ በወቅቱ በጥያቄ መልክ ተነስተው ምላሽ ሳያገኙ እኛ ዘንድ የደረሱ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ እንዲሁም ከሠራተኛው የመጡ ዛሬም ድረስ ምላሽ ያልተሰጣቸው ችግሮች ስለመኖራቸው ጠቁመዋል።

ኹለተኛው ጥያቄ አሁን ላይ አብረው የሚኖሩ የየዘመኑ ትውልዶች በዚህ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች መሻገር ይችላሉ ወይ የሚል ነበር። ይህን አስመልክቶም አንዱ የአንዱን ጠንካራ ጎን በመጋራት ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኝነት ካለ መሻገር የማይቻልበት ሁኔታ እንደማይኖር ነው የተገለጸው። በተለይ ከ1983 በፊት የነበረው ትውልድ የእውቀት ምጥቀትንና መነጋገርን እንደበጎ ባህል የሚወስድ ስለነበር የአሁኑ ይህን መማር አለበት።

ተቀራርቦ በመነጋገር መስራት ከተቻለ የነበሩ ቂሞችንና የሚነሱ ችግሮችን መፍታት ሊቻል ይችላል፣ ሆኖም እንዴት መያዝ እንዳለብንና ማወቅ እንችላለን። ይህም ከችግሮቻችን በላይ ሆነን እንድንሻገር ይረዳናል የሚል አንድምታ ተላልፏል።

- ይከተሉን -Social Media

ተጨማሪ አዳዲስ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማፍለቁ ተገቢ በመሆኑም፣ የባህል ለባህል ትስስሮችንና ውይይቶችን ማድረግ (intercultural dialogue)፣ የፌደራል ከተሞችን ማብዛት እና ሌሎች አማራጮች ችግሮችን ለመሻገር እንደሚያግዙ ነው የተነሳው።

ሶስተኛ ጥያቄ ሆኖ የቀረበው ብሔራዊ ምክክሩ የትውልድ ቅራኔውን ሊፈታ ይችላል የሚል ነው። ሆኖም ለጦርነት የተቀሰቀሰው ማህበረሰብ ለሰላምም መቀስቀስ አለበት። የአብዮቱ ትውልድ ተብሎ እንደሚታወቀው ሁሉ ይህም ትውልድ የብሔራዊ ምክክሩ የሰላም ትውልድ ተብሎ የሚጠራ ትውልድ መሆን አለበት። ስለሆነም፣ ምክክሩ ቅራኔዎችን በመሉ ነቅሶ በማውጣት ሽረት እንዲያገኙ ማድረግ የሚችል ባይሆን እንኳን የመነጋገርን ባህል እንዲሁም ትልቅ አሻራ አስቀምጦ የሚያልፍ ሁነት መሆኑ ታምኖበታል።

በማጠቃለያ ከተነሱ ሃሳቦች፣ በዓለም ላይ ያሉ የቴክኖሎጂ፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ካሉን ያልተፈቱ አዳሪ ችግሮቻችን ጋር ተዳምረው በቀደመውና በአሁኑ ትውልድ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲሰፋ ያደርጉታል።

ሆኖም በማውራት፣ በመሞገት፣ በጋራ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል። ባይቻል እንኳን ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ፣ የተነጋገርንበትን እናስቀምጠውና መጭው ትውልድ የበለጠ ተወያይቶበት መፍትሄ እንዲሰጠው እናድርግ። ይህም በቀደመውና በአዲሱ ትውልድ መካከል ያሉ ልዩነቶችን እንዲሁም የአሁኑን ትውልድ የጎንዮሽ ልዩነቶች ቀስ በቀስ በመድፈን፣ በመነጋገር መግባባትን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚቻል ታምኖበታል።

እንዲሁም፣ በአገራችን በብዛት ውሳኔዎች ከላይ ወደ ታች እየወረዱ የጎንዮሽ ንትርክ መፍጠር እንደሌለባቸውና ከታች ወደ ላይ የሚሄዱ ውሳኔዎችም በመካከል ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ የተሻለ አገረ መንግስት ለመገንባት አስተዋፆአቸው የጎላ መሆኑ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዘመናት የሚታየው የፖለቲካ ቀውስ፣ ስር የሰደደው የአገሪቱ ድህነት አንዱ ገፅታ ሊሆን ስለሚችልም ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን ለማጠንከር ስልጣኔና እድገት ላይ መስራት የግድ እንደሚል በመድረኩ ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች