መነሻ ገጽአምዶችዓውደ-ሐሳብወደኒውክለር ዛቻ ያደገው የዩክሬኑ ጦርነት

ወደኒውክለር ዛቻ ያደገው የዩክሬኑ ጦርነት

ሩስያ እና ዩክሬን ማለቂያ አልባ የመሰለ ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ጦርነት ኹለቱን አገራት ቀጥተኛ ባለጉዳይ ያድርግ እንጂ፣ በተዘዋዋሪ የዓለም በርካታ አገራት በተለያየ መንገድ ሥማቸው አብሮ የተነሳበት ነው። ይህ ጦርነት ለአፍሪካ ድህነቷ ላይ እንደ ጆሮ ደግፍ የተጨመረ መከራ ሆኖ ኢኮኖሚዋን ሲያጎሳቁለው፣ ያደጉ አገራት ደግሞ በተቀናቃኞቹ በየአንዳንዳቸው ወገን እየቆሙ ጦርነቱ ውስጥ ለመሳተፍ የቋመጡ ይመስላል። ዛቻውም እርስ በእርሳቸው ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የሚያሰጋ መሆኑ እየጨመረ መጥቷል። አለቃ ዩሐንስ ይህን ጉዳይ በማንሳት ተከታዩን ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

ሩስያ እና ዩክሬን በምዕራባውያን ቆስቋሽነት ወደ ጦርነት ከገቡ ወራት ተቆጥረዋል። በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ሲገመት የነበረው ውጊያ እያደር አድማሱ እየሰፋ የሰለባዎቹን ቁጥር እየጨመረ ሁሉን ዐቀፍ ወደሆነ ጦርነት ተሸጋግሯል።

በአጭር ዘመቻ የዩክሬንን መንግሥትና ፀብ አጫሪነትን አስወግዳለሁ ብላ የተነሳችው ሩሲያ፣ ፍላጎቷ እየተነነ ሐሳቧ እየተጓተተ የሚያስከፍላትም መስዋዕትነት እየጨመረ መጥቷል። ከዘመቻው መነሻ አንስቶ ድል በእጇ እንደሚሆን ስትተማመን የነበረችው ይህች ልዕለ ኃያል አገር፣ እያደር መቋጫው እየራቃት ተስፋዋም እየተሟጠጠ ይመስላል።

በሌላ በኩል ጦርነቱ ምድሯ ላይ እየተካሄደ ሕዝቧንም ከተማዎቿንም እያጣች ያለችው ዩክሬን በጦርነቱ መነሻ ከነበራት ተስፋ በተሻለ አሁን በጥሩ ሂደት ላይ እንዳለች እየተናገረች ትገኛለች። የምዕራባውያኑን ተማፅኖ ያላቋረጡት የቀድሞ ቀልደኛ የነበሩት የአገሪቱ መሪ፣ አገሬን አልለቅም በሚል የሞት ሽረት ትግሉን ቢያጠናክሩም፣ ምዕራባውያኑን ተማምነው ከማይታገሉት ግዙፍ ጋር ወደ መላተም መግባታቸው ያስተቻቸዋል።

ያም ሆነ ይህ፣ ሩስያ ያላትን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች እየተጠቀመች ድልን እየተጎናፀፈች ስትመጣ ዩክሬናውያኑ ወታደሮች ደግሞ የመዋጋት ሞራላቸው እየላሸቀ እያደር ምዕራባውያኑ ላይ ጥገኛ እየሆኑ ታይተዋል። አዳዲስ ዘመናዊ የጦር መሣሪያን አሜሪካና አጋሮቿ ሲለግሱ የተወሰነ ፋይዳ ቢያመጣላትም፣ በምርኮ እየተገኙ ስለቴክኖሎጂው ለሩስያ ግብዓት መሆናቸው ደጋፊዎቿን አላስደሰተም።

አውሮፓውያኑ ከሚያደርጉት የጦር መሣሪያ ድጋፍ በተጨማሪ ሩስያን ለማዳከም ያስፈልጋል ያሉትን ማዕቀብ ቢጥሉባትም፣ የተወሰደባቸው ኢኮኖሚያዊ የመልስ ምት ግን ያልጠበቁት ሆኖ ኢኮኖሚያቸውን ክፉኛ አናግቶባቸዋል። አሜሪካም ሩስያን ከዓለም ገበያ ለማስወጣት አስባ ያደረገችው የኢኮኖሚ ማዳከሚያ ዘዴ፣ “ባሏን ጎዳሁ ብላ…” እንደሚባለው ዶላሯ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሚኖረው ተቀባይነት ላይ ችግር ፈጥሮባታል።

የኔቶን መስፋፋት ለመገደብ በሚል የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ የሆነ ውል በተደጋጋሚ ተጥሷል ብላ ወደ ጦርነቱ የገባችው ሩስያ ላይ ዓለም ዐቀፍ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ቢከፈትም፣ ከጉዳቱ ይልቅ ዝናን ጭምር እያተረፈላት መሆኑም ይነገራል። በተለይ በምዕራባውያን ጭቆና ስር ለዘመናት የቆዩ አገራት ሽኩቻውን ተገን አድርገው ድጋፋቸውንም ሆነ ወገንተኝነታቸውን ለምሥራቁ ጎራ ዐሳይተዋል።

በኹለቱ ኃያላን ጎራ መካካል የሚደረገውን የተፅዕኖ ግዛት የማስፋፋት ዘመቻ መፋጠጫ ሆና የሙት መሬት እየሆነች የምትገኘው ዩክሬን፣ እያደር እየወደመች ዜጎቿንም እያጣች ትገኛለች። ሩስያም በበኩሏ ብዙ ሀብት ማፍሰስ ብቻ ሳይሆን በርካታ የጦር ሠራዊቶቿን በዚህ በዘመናዊ የጦር መሣሪያ በታጀበው ጦርነት ማጣቷ እየተነገረም ይገኛል።

በዘመናዊ የጦር መሣሪያ እየተመራ የሚገኘው የኃያላኑ ሽኩቻ ወዲያው ከሚገድል መሣሪያ በተጨማሪ አደህይቶ ወደሚያጠፋ መሣሪያም ተሸጋግሯል። ምንዛሬን ሥልታዊ ማጥቂያ ማድረጋቸው ሳያንስ የኃይል አቅርቦትን እየተለዋወጡም ውጊያውን እያፋፋሙት ይገኛሉ። ዓለም ዐቀፍ ሕግን ተንተርሰው ሕጋዊ መተላለቅን እያፋጠኑ ያሉት እነዚህ ወገኖች፣ የጦርነቱ ዳፋ በእነሱ ላይ ብቻ እንዲቀር አላደረጉም።

በኃያላኑ ሽኩቻ ሳቢያ ሩቅ ያለው በተለይ ድሃው አፍሪካዊ የችግሩ ገፈት ቀማሽም እየተደረገ ነው። አይደርስብኝም እንዳለችው እንቁራሪት ኩሬው ውስጥ የቆዩ አገራት በኑሮ ውድነት እንዲሰቃዩም ሆነዋል። በተለይ ኹለቱ ተፋላሚ አገራት በማዳበሪያና ስንዴ ምርት ግንባር ቀደም እንደመሆናቸው፣ ውጊያ ላይ መቆየታቸው የእነሱ ምርት ላይ ተማምኖ ለሚጠብቀው የዓለም ሕዝብ ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› ሆኖበታል።
ዩክሬን ያመረተችውና ለዓለም ገበያ ይቀርብ የነበረ እህል እንዳይወጣ ሩስያ አድርጋለች በሚል ድሃ አገሮች ጥፋቱ የሩስያ ነው ብለው እንዲያስቡ ምዕራባውያኑ የሸረቡት ሴራ ባይሳካላቸውም፣ ሁኔታው ግን ብዙዎችን ይበልጥ እያሳሰበ ይገኛል። የስንዴው ክምችት እንዳይወጣ እኔ አላደረግሁም የምትለው ሩስያ፣ ማውጫ መንገዶቹን የዩክሬን መንግሥት በተቀበሩ ፈንጂዎች ስላጠራቸው ነው በሚል ጥፋቱ የእሷ እንዳልሆነና የማውጣት ሂደቱ በእሷ በኩል እንደማይስተጓጎል ስትናገር ቆይታለች።

የስንዴውን ፍጥጫ ለማርገብ የቱርክዬው መሪ ኤርዶጋን ኹለቱን ወገኞች ለማገናኘት እቅድ የያዙ ሲሆን፣ በቅድሚያ በጦር መሪዎች በኩል መንገድ ለመፈለግ ባለሥልጣኖችን ሩስያ በመላክ መላ ይፈልጋሉ ተብሏል። ይህ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ወደ ጥቁር ባሕር የሚያሳልፉ መተላለፊያዎች አካባቢ የተቀበሩ ፈንጂዎች የሚፀዱበት ሁኔታ ላይ ስምምነት እንዲደረስም ይጣራል ተብሏል።

ይህን ለማከናወን በዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ውትወታ ዩክሬን የቀበረችበትን ቦታ እንድታሳውቅ የተጠየቀች ቢሆንም፣ በካርታ ላይ ያልሰፈሩ የማይታወቁ ቦታዎች ላይ መቅበሯ ሌላ ስጋትን ፈጥሯል። ይህ የስንዴ ክምችት ሳይበላሽና የዓለምንም የስንዴ ገበያ እንዳይመለስ አድርጎ ከማዛባቱ በፊት በቀጣይ ሳምንት እልባት ያገኛል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል።

የኒውክለሩ ፍጥጫ
ኹለቱ ተፋላሚ ወገኖች ገቢያቸው እንዳይመናመን ገበያቸው ተጠብቆላቸው ውጊያውን እያካሄዱ ባሉበት በዚህ ወቅት ሌላ ትኩሳት ተፈጥሯል። አገራቱ ጅምላ ጨራሽ የሚባሉ ያልተከለከሉ የጦር መሣሪያዎችን ቴክኖሎጂን ተጠቅመው እየተገዳደሉ ቢገኙም፣ ይህም እንዳላረካቸው እየታየ ይገኛል። ሩስያኖች ኒውክለር ቦንቦችን መጠቀም እንደሚችሉ ማስጠንቀቅ የጀመሩት በቅርቡ ባይሆንም፣ ለማንም እንደማይጠቅምና ማንም እንደማይተርፍ በባለሥልጣኖቻቸው በኩል ሲመክሩ ነበር።

ከሠሞኑ ግን የኒውክለሩ ዛቻ ጦፎ፣ የኒውክለር ጦርነት ከተጀመረ እንግሊዝ የምትባል አገር እንደማትኖር ሩስያ በልሂቃኗ አማካኝነት ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች። በሌላ በኩል የጀርመን የአየር ኃይል አዛዥ ደግሞ ምዕራባውያን ሩስያ ላይ የኒውክለር ቦንብ እንዲጠቀሙ መወትወታቸው ተነግሯል። እኚህ ጄነራል ከሰሞኑ በተደረገ የጦር ጉባዔ ላይ ተናገሩ እንደተባለው፣ አገራቸውም ሆነ ምዕራባውያን ለኒውክለር ጦርነት ዝግጁ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የጀርመን ልሂቃን አገራቸው ልዕለ ኃያል እንድትሆን ካላቸው ጉጉት የተነሳ በአገራቸው የሚገኙ የአሜሪካ ኒውክለር ቦንቦችን ሩስያ ላይ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን አቅም እየገነቡ ይገኛሉ። በኹለቱ የዓለም ጦርነቶች ወቅት በሚሊዮኖች እንዲያልቁ ምክንያት የነበሩ የጀርመን ፋሺስት አመለካከት ያላቸው አንዳንድ ባለሥልጣናት ጭምር ወቅቱን ተጠቅመው አገራቸውን እንደቀድሞው ዘመን ጉልበተኛ ማድረግ እንደሚሹ ተነግሯል።

ዛቻውን የሰነዘሩት እኚህ የጦር መሪ ያለምንም ፍራቻ የኒውክለር ቦንብ ጥቅም ላይ እንዲውል መቀስቀሳቸው አውሮፓን ሰው አልባ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ከምድር ላይ መጥፋትም ምክንያት ይሆናል የሚል ስጋት አሳድሯል። የጦር ጄነራሉ ኒውክለር አረርን መጠቀም የሚያስችል ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ብቃት ሊኖረን ይገባል ማለታቸው፣ ጦርነቱ በዚሁ ከቀጠለ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከዛቻ ወደ ተግባራዊነት ይለወጣል የሚለውን ስጋት እውን ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ተገምቷል።

- ይከተሉን -Social Media

በሌላ በኩል፣ አገራቱ የታጠቁት የኒውክለር ቦንብ እንደብዛቱና ጉልበቱ ጥቅም ላይ ሊውል ካልቻለ ማስፈራሪያ ሆኖ ብቻ አይዘልቅም በሚል አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ። ነገሮች ከከፉ በየትኛውም ወታደራዊ ሕግ ያለን የጦር መሣሪያ ለመጠቀም መቼም ቢሆን ዝግጁ መሆን ተገቢ ነው በማለት የዛቻውን አስፈላጊነትም የሚደግፉ አሉ። ጀርመን የጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆናለች እስኪያስብላት ድረስ ዘመን አፈራሽ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ጭምር ለዩክሬናውያኑ በማቅረብ የጦርነቱ ገፈት ተቋዳሽ ያደርጋታል የሚሉ አሉ።

በናዚው የሂትለር ዘመን 30 ሚሊዮን ሩስያውያን ያለቁበት የኹለቱ አገራት ጦርነት አሁንም ተደግሞ ሚሊዮኖች ከኹለቱም ጎራ እንዳይጠፉ የብዙዎች ጭንቀት ለመሆን በቅቷል። እንደ ዩክሬናውያኑና ሩስያኖች የጦርነቱ ቀጥተኛ ሰለባ እንደማይሆኑ ገምተው ኒውክለር ጥቅም ላይ እንዲውል የሚወተውቱ፣ ጦሱ ለእነሱም እንደሚተርፍ አያውቁም ለማለት ይከብዳል።

በሌላ በኩል፣ የእንግሊዝ የጦር መሪ እየመሩት የሚገኝ የኔቶ ጦር የሩስያ የንግድ መተላለፊያ የሆነውን በሉቱዋኒያ በኩል ያለ መንገድን መዝጋቱን ተከትሎ የሰጡት አስተያየት ነው ለፍጥጫው መንስዔ የሆነው። እንግሊዛዊው የጦር መሪ ከፈረንጆቹ 1941 ወዲህ አጋጥሞ የማያውቅ ጦርነት ነው የሚጠብቀን በማለት በቀጣዩ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሩስያን ለመደምሰስ ጦሩ እንዲዘጋጅ ነበር ጥሪ ያቀረቡት።

የጦር መሪውን ጥሪ ተከትሎ የሩስያ የቀድሞ የጦር መሪና ወታደራዊ አማካሪ ቁጣቸውን ገልፀዋል። የሦስተኛው የዓለም ጦርነት የኒውክለር እንደመሆኑ የሚካሄድ ከሆነ እንግሊዝ የምትባል የደሴት አገር አትኖርም በማለት አስጠንቅቀዋል። የእንግሊዙንም ወታደራዊ አዛዠ ዘር ማንዘራቸው እንደማይኖር ጭምር የእንግሊዛውያን መጥፊያ እንደሚሆን በማሳሰብ፣ የሩስያ መሪ ቭላድሚር ፑቲን የኒውክለር ቦንቦችን ውጥረቱ ወደነገሠበት ምዕራብ ሩስያ እንዲያስጠጉና በተጠንቀቅ ጦሩ እንዲጠብቅ ጥሪ እንዲያስተላልፉ ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩስያ ፕሬዝዳንት የኒውክለር ጦር መሣሪያቸውን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የሚያስችላቸውን ኮድ ማስገቢያ ቦርሳ ይዞ ኹሌ አብሯቸው ይጓዝ የነበረ የ53 ዓመት ሰው በመኖሪያ ቤቱ በጥይት ተመቶ መገኘቱ ፍጥጫውን ይበልጥ አባብሶታል። በጡረታ የተገለለው ይህ የቀድሞ ኮሎኔል በሙስና ወንጀል ተከሶ ክሱን እየተከታተለ የሚገኝ ነበር። የቀድሞ የሩስያ መሪ ቦሪስ የልሲን ቦርሳ ያዥ የነበረውን ይህ ሰው ማን ሊገለው እንደፈለገ፣ አልያም ግድያው ከሥራው ጋር እንደሚገኛኝ እስከ አሁን ምንም የተባለ ነገር አለመኖሩን ሚረር አስነብቧል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች