መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበቀይ ቀበሮዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ውሾችን በኹሉም ፓርኮች መከተብ አለመቻሉ ተነገረ

በቀይ ቀበሮዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ውሾችን በኹሉም ፓርኮች መከተብ አለመቻሉ ተነገረ

እስከ አሁን 1ሺሕ 932 ውሻዎች ተከትበዋል

በተለያዩ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ ቀይ ቀበሮዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የውሾችን ክትባት በተመለከተ በኹሉም ፓርኮች አለመደረጉን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለሥልጣን ገለጸ።

በቀይ ቀበሮዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ውሾች ተለይተው የሚከተቡ ሲሆን፤ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ዙሪያ ከሚገኙት ውጪ በኢትዮጵያ ፓርኮች ዙሪያ የሚኖሩ ውሾች ስለመከተባቸው መረጃው እንደሌላቸው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ሰለሞን ወርቁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በዱር እንስሳት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ተብለው የተለዩና ክትባት የተሰጣቸው በባሌ ብሔራዊ ፓርክ ዙሪያ ብቻ ባለው የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ የሚገኙ የቤት ውሻዎች መሆናቸውን ነው ማወቅ የተቻለው።

በ2014 ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ወራት ውስጥ በፓርኩ በሚገኙ ቀይ ቀበሮዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ የተባሉ አንድ ሺሕ 932 ውሻዎች መከተባቸውን ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውጪ ባሉት ብሔራዊ ፓርኮች፣ በብርቅዬ እንስሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት የሚያስችለውን የውሻዎች ክትባት በተመለከተ ግን የወጣ በጥናትና የታወቀ ቁጥር ባለመኖሩ መረጃው እንደሌላቸው ነው ሰለሞን የተናገሩት። በሌሎች ፓርኮች ዙሪያ የሚገኙና ጥቃት ያደርሳሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ውሻዎች ጥናት ተደርጎ ሲለዩ እንደሚከተቡም ጠቁመዋል።

በዝርያቸው ካልሆነ በስተቀር የዱር እንስሳት ቁጥር መቀነሱን ወይ መጨመሩን ማወቅ አይቻልም ያሉት ሰለሞን፤ የቀይ ቀበሮን ዝርያ በተመለከተ እስከ አሁን ባለው መረጃ መሠረት የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የዱር እንስሳት ስደትን በተመለከተም በኦሞ፣ በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ እንስሳት በወቅታዊ ሁኔታ እንደሚሰደዱና ተመልሰው ወደተለመደው ፓርካቸው እንደሚመጡ አብራርተዋል።

በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከኹለት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ፓርኩን የሚጻረሩ ሕገ ወጥ ቤቶች መኖራቸው የሚነገር ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ የሚያሳድጓቸው የቤት ውሾችም በተለይ በቀይ ቀበሮዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ተብሏል።

ውሻዎቹ ‹የእብድ ውሻ በሽታ› ያለባቸው ከመሆናቸው አንጻር በእንስሳቱ ላይ ከሚፈፅሙት የንክሻ ጉዳት በተጨማሪ ለእብደትም እንደሚዳርጓቸው ነው የተመላከተው። የውሻ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰውም እንደሚታላለፍ የሚነገር ሲሆን፤ በፓርክ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ውሾቻቸውን ሊያስከትቡ እንደሚገባ ተመላክቷል።

የእብድ ውሻ በሽታ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ‹ጆርናል ኦፍ ትሮፒካል ሜድሲን› የተሰኘው ድረ ገጽ ላይ የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአምስት ዓመታት ውስጥ (2015 እስከ 2019) 87 ሰዎች የእብድ ውሻ ምርመራ አድርገው ሁሉም በቫይረሱ የተያዙ መሆናቸውን አስቀምጧል።

የእብድ ውሻ ጥቃት፣ የሰደድ እሳት፣ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች የሚያደርሱት የደን ጭፍጨፋ፣ ልዩ የሆነ የግጦሽ ቦታ እንዲሁም ሕገ ወጥ ቤቶች በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሚገኙ የዱር እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ ችግሮች መሆናቸውም ይነገራል።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከኹለት ሺሕ በላይ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚያካልል ሲሆን፤ ዩኔስኮ በ2009 እንደመዘገበው እንዲሁም ከሰባት ሺሕ የሚበልጡ የቤት እንስሳት በፓርኩ አጠገብ በመኖራቸው የዱር እንስሳቱን ለአደጋ እንደሚያጋልጡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ባለፈው ዓመት ገልፆ ነበር።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች