የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2014 በጀት ዓመት በተለያዩ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለረጅም ጊዜያት የቆሙ ዩኒቶችን ጠግኖ ወደ ሥራ በማስገባት ውጤታማ ሥራ ማከናወኑን የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ጽሕፈት ቤት ማስታወቁ ተዘግቧል።
በጢስ አባይ 2ኛ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለስምንት ዓመታት ያህል በብልሽት የቆመ 36 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል፤ በቆቃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለ10 ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ቆሞ የነበረን አንድ ዩኒት በመጠገን ወደ ሥራ አስገብቷል ነው የተባለው።
በግልገል ጊቤ 2ኛ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በራስ አቅም የኹለት ዩኒቶችን የኖዝል ጥገና በማከናወን በሙሉ አቅማቸው 210 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ ከማስቻሉም በተጨማሪ፣ ተቋሙ ለውጭ ባለሞያ ያወጣ የነበረውን እስከ 650 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ማስቀረት መቻሉም ተመላክቷል።
በግልገል ጊቤ 1ኛ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የመጠባበቂያ ዲዝል ጀኔሬተር ተከላና በጊቤ 3ኛ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሳሊኒና ዴክ ከተሰኙ ድርጅቶች ጋር በተፈጠረው ስምምነት መሠረት የግድብ ሊኬጅ ጥገና መከናወኑ ተሰምቷል።
በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማስተካከል የሚረዱ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱ ተገልጿል የተባለ ሲሆን፤ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና መስመሮች ጥገናና ፍተሻ ሥራ የኤሌክትሪክ መቋረጥን በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዳስታወቀ ተዘግቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014


