መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛያልተማረው የህግ ታራሚ

ያልተማረው የህግ ታራሚ

ግለሰቡ ከ13 ዓመታት በፊት መነጋገሪያ የነበረ ሰው ነው። ታዋቂ የሆነው በሰራው ዘግናኝ ግፍ ነበር። ካሚላት የምትባል እህት ላይ አሲድ በመድፋቱ ነበር አገር መነጋገሪያ ያደረገው።

ይህ ሰው በወቅቱ በሰራው አሰቃቂ ድርጊት ሳቢያ ሰው በመግደል ሙከራ ወንጀል ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት ሲከራከር ከቆየ በኋላ ነበር የሞት ፍርድ ተፈርዶበት የነበረው። በኋላ ላይ ቅጣቱ ወደእድሜ ልክ እስር ተቀይሮለት እንደነበር ተወርቷል።

ከእሱ ድርጊት በኋላ ተመሳሳይ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ይሰማ እንጂ ስለግለሰቡ ምንም ሳይባል ቆይቶ ሠሞኑን በድጋሚ መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል። በደንቡ መሰረት የእድሜ ልክ እስራት ብያኔ ቢያንስ 20 ዓመታትን በማረሚያ ቤት እንደሚያስቆይ የህግ ምሁራን ቢናገሩም በእሱ ላይ ግን ተፈፃሚ አልተደረገም።

ስነምግባሩ ተሻሽሏል ብለው ይሁን ወይስ በሙስና ባይታወቅም፣ ከ12 ዓመት እስር በኋላ በይቅርታ ተለቆ እንደነበር ተነግሯል። ይህ ከስህተቱ ተምሯል ተብሎ የሚገመት ሰው ግን ሴት እህቶች ላይ ይብሱኑ ቂም ቋጥሮ እንደቆየ የሚያመላክት መረጃ ይፋ ተደርጓል።

ማረሚያ ቤትን ከለቀቀ በኋላ በአንድ አመት ውስጥ ከ30 በላይ እንስቶችን መርጦ ማጭበርበሩ ተነግሮ በተጠርጣሪነት ዘብጥያ መውረዱ ጉድ አስብሏል። ውክልና ሰጥታው ንብረቷን በሸጠባት እንስት ጥረት ለእስር የበቃው ይህ ሰው፣ ከፀጥታ አካላት ጋር እየተመሳጠረና እየተባበረ ያጭበረበራቸውን ጭምር እንደወንጀለኛ ሲያሳስር ነበር ተብሏል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ ፈፀመ ከተባለው ድርጊት በላይ ብዙዎች አስተያየት የሰጡት ለምን ተፈታ በሚለው ላይ ነው። ከጥፋቱ ያልተማረ ሰውን መልሶ ማሕበረሰቡ ውስጥ መልቀቅ አደጋው የከፋ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነም በቁጭት ጭምር የተናገሩ አሉ። በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ተረባርበው የነበሩ አካላት ምን እንደተሰማቸው ባይነገርም ብዙዎች በፍትህ ሥርዓቱ ማዘናቸውን ገልፀዋል።

አንዳንዶች፣ በማረሚያ ቆይታው የባሰ ክፋትን ተምሮ የወጣ ነው በሚል ምስሉን አስደግፈው እንደተስማማው በመግለፅ፣ ሌላ እስር ከተወሰነበት የበለጠ ሊፋፋና ስራውን ሊያስፋፋ ይችላል በማለት ሐሳባቸውን በስላቅ ገልፀዋል።

ሌሎችም የተለያየ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። “የፈታው ነበር በምትኩ መታሰር ያለበት፤ አሁን ለሶስተኛ ጊዜ ነው የታሰረው” የሚሉና “የፍትሕ አካላቱ ተባባሪዎቹ የተባሉት ግብረ አበሮቹ ናቸው” የሚሉ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል። “አሁንም መልሰው ስለሚፈቱት አታሳሙኝ” በማለትም ሥርዓቱን በቃላት የገለፁም ነበሩ።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች