መነሻ ገጽዜናወቅታዊየዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች በነገ መንገድ

የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች በነገ መንገድ

በኢትዮጵያ ቀደም ባለው ገዜ የሚቸግረው የትምህርት ዕድል ማግኘት ነበር። አሁን ከሆነ ደግሞ የትምህርት ዕድል ሰፊ ሆኖ የጠፋው የሥራ ዕድል ነው። ኢትዮጵያ በየዓመቱ በርካታ ወጣቶችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከሆኑ ከኮሌጆችና ከዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች ታስመርቃለች።

የተመራቂዎች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ እንደሚሄድ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን፣ የሚመረቁ ወጣቶች ቁጥርና ያለው የሥራ ዕድል ግን ተመጣጣኝ እንዳልሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነው።

በተለይ ከኹለት ዓመት ወዲህ ጀምሮ በአገሪቱ በተበራከተው ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች የተነሳ ያለው የሥራ ዕድል ዝቅተኛ ሆኗል። ይልቁንም የዜጎች ከቦታ ቦታ በነጻነትና ያለስጋት መንቀሳቀስ ችግር ላይ መውደቁን ተከትሎ ደግሞ ለተመራቂዎች በዚህ መልክ እንደወትሮው ሥራ መፈለግ በጣም አዳጋች መሆኑ ይነሳል።

ይህን ተከትሎም ብዙ ተመራቂ ተማሪዎች በተለይ በዚህ ወቅት መመረቃችን ከደስታ ይልቅ ፍርሃትና ጭንቀት ይፈጥርብናል ባይ ናቸው።
ስምኦን ተሻገር (ሥሙ የተቀየረ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ ትምህርት ክፍል ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ በቅርቡ ከተመረቁ ብዙዎች መካከል አንዱ ነው።

የመመረቂያ ቀናችን እየቀረበ ሲመጣ ብቻዬን ማውራት ጀምሬ ነበር ይላል ስምኦን። ‹‹ሆዴን እየራበኝ ምግብ አልበላኝ ስላለም ወደ ክሊኒክ ስሄድ ሐኪሙ ጭንቀት ታበዛለህ ወይ ብሎ ሲጠይቀኝ፣ ከተመረቅኩኝ በኋላ ምንድን ነው የምሆነው የሚለው በጣም እንደሚያስጨንቀኝ ነገርኩት። እሱም ያለውን ሁኔታና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ስለመከረኝ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንደተረጋጋሁ ይታወቀኛል።›› ሲል ይናገራል።

አስቀድሞ ጓደኞቹ ብዙ ጊዜ ሥራ የሚገኘው በሰው እንደሆነ እንደሚነግሩት ያወሳል። ሥራ ያገኙትም በሚከፈላቸው ክፍያ ራስን ችሎ ለመኖር እንደማይበቃ ሲያወሩ እንደሚሰማም ጠቅሷል። በድምሩ ‹‹የማያስጨንቀኝ ነገር የለም ነበር›› ይላል። አሁን ላይ ከምን መጀመር እንዳለብኝ አላውቅም ብቻ ግን በዚህ ወቅት ተመራቂ መሆን ከምንም የባሰ አስጠሊታ ሳይሆን አይቀርም ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

ከሐዋሳ በቋንቋ የተመረቀች አንዲት ወጣትም ለአዲስ ማለዳ አስተያየት ስትሰጥ፤ ‹‹እንዲሁ ቤተሰቦቼ ትልቅ የምርቃት ድግስ ለማዘጋጀት ሲጥሩ ዐያለሁ። ይሁን እንጂ እኔ በዕለቱ የእነሱን ያህል ደስታ ሊሰማኝ እንደማይችል ቀድሞ ይሰማኛል።›› ነው የምትለው።

‹‹እነሱ ሥራ ማግኘት እንደማያቅተኝና ሥራውን ካገኘሁ በኋላም ብዙ ቀዳዳዎችን እንደምሸፍንላቸው ያምናሉ። ይህ እምነት እኔ ጋር አለመኖሩ ጭንቀትና ድብርት ነው እየፈጠረብኝ ያለው። ስለሆነም፣ የእኛ የብዙዎችቻን የአፍላነት እድሜ በዚህ መልኩ ማለፉ ይበቃል። ስለሌሎች የበለጸጉ አገራት ወጣቶች የምንሰማው እኮ በጣም የሚያስገርም ነው፣ ቢያንስ ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለች አገር እንድትኖር ብንጥር ምናለበት?›› ስትልም ትጠይቃለች።

በአንጻሩ የተሻለ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ምሩቃን ያለምንም ደላላና ዘመድ አዝማድ ተፈልገው የሚቀጠሩ አሉ። እነዚህ ምሩቃን ተቋም መርጠው በጥሩ ደሞዝ ከመሥራት ባለፈም የራሳቸውን ሥራ ለማቋቋም ራዕይ የሰነቁ መኖራቸው አይካድም።

ከፋይናንስና ከችግር ፈቺነት ጋር አያይዘው ትምህርትን በሚሰጡ አገራት ላይ ምሩቃን ሥራ አጥ የመሆናቸው ጉዳይ ያለ ግን ደግሞ በቀላሉ የሚፈታ ችግር ነው።

በዳበረ የትምህርት ስርዓት በዓመት ብዙ ተማሪዎች እንደሚመረቁ ብሎም ሰፊ የሥራ አማራጮች እንዳላት በምትታመነው አሜሪካ እንኳን፣ በዓመት ከ350 ሺሕ ያላነሱ ምሩቃን የሥራ ሕይወታቸውን የሚጀምሩት ባልተመረቁበት የሥራ ዘርፍ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዚህም በቋንቋና ሥነ ጽሑፍ፣ በሕግ፣ በሕክምና ወይም በምህንድስና የተመረቀ አንድ ወጣት ለወራት አልያም ለዓመታት በጥበቃ፣ ጽዳት፣ መስተንግዶ እንዲሁም ሌሎች የሥራ ዘርፎች ውስጥ መሰማራት ይጠበቅበታል። ይህም ኹሉም ሥራ የተከበረ መሆኑን በማመን ከጥገኝነት ለመላቀቅ የሚረዳ ሲሆን፣ ጠንካራ የሥራ ባህል በመፍጠር ረገድም የጎላ ሚና እንዳለው መጥቀስ ይቻላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ኹሉንም ሥራ እኩል የማየት ችግር በስፋት የሚስተዋል ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ብዙዎች ያገኙትን በመሥራት ቀስ በቀስ ራሳቸውን ወደመቻልና ወደሚፈልጉት የመሄድ አዝማሚያዎች ይታያሉ።

በዚህ ኑሮ ውድነት በዝቅተኛ ክፍያ ተቀጥሮ መሥራት ያለው ችግር እንዳለ ሆኖ፣ ያንንም ማግኘት አስቸጋሪ የሆነበት ወቅት እንደሆነ በርካቶች ይገልጻሉ።

በአሁኑ ወቅትም የመንግሥት የሥራ ቅጥር በብዙ ተቋማት እንደ በፊቱ አይደለም። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለወትሮው በርካታ የሰው ኃይል በቅጥር የሚያስገቡት የመንግሥት ተቋማት ቅጥር ሳያወጡ ከርመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2014 በጀት ዓመት ከአንዳንድ አስፈላጊ ቦታዎች ውጭ አዲስ ቅጥር አልፈጽምም ማለቱ የሚዘነጋ አይደለም። አማራ ክልልም በተመሳሳይ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የበፊቱን ያህል አዲስ ቅጥር ሲፈጽም አልነበረም።

የሥራ አጥነት ቁጥሩ በየዓመቱ ምን ያህል እንደሆነ ትክክለኛውን አኃዝ ማግኘት ባይቻልም፣ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚሄድ አመላካች ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ቀድሞ ያልነበሩ የሥራ አጥነት ሁኔታዎች ሲጨምሩ ይስተዋላሉ። እንደ ምሳሌም የሕክምና ተማሪዎች ለረዥም ጊዜ ሥራ አጥ ሆነው ማየት እየተለመደ መጥቷል።

- ይከተሉን -Social Media

በሌላም በኩል ከአንድ እና ከኹለት ዓመት በፊት የተመረቁና ሥራ ለማግኘት ተስፋ ቆርጠው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተዳብለው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው።

ሥሜ ይቅር ያለችና ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረገች ወጣት፤ በ2010 በግብርና ሳይንስ ከታወቀ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ከሦስት ነጥብ በላይ በማምጣት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች። ይሁን እንጂ የሥራ ማስታወቂያዎች ሲወጡ ሴት በመሆኗ በየአውራጃዎች እየዞረች በኹሉም ለመወዳደር አልቻለችም። በአቅራቢዋ በሚወጡ የሥራ ዕድሎች ደጋግማ ብትሞክርም በአንዱም ግን ተጠርታ አታውቅም።

የተመረቀችበት የሥራ መስክ ደግሞ ወደ ከተማ ገብታ ሥራ ለመፈለግ የሚያስችላት አይደለም። እናም ከአራት ዓመት በላይ ገጠር ውስጥ ከቤተሰቦቿ ጋር እንደምትኖር ገልጻለች። በከፍተኛ ተስፋ ማጣት ውስጥ ሆና ቀጣይ ሕይወቷም ምን እንደሚመስል የማታውቅ መሆኗንም አልደበቀችም። ‹‹ቤተሰቦቼ በሌላ የትምህርት ዘርፍ ተመርቀው ሥራ ላይ ያሉ እኩዮቼን ሲያዩ ይቀናሉ። እኔም አለቅሳለሁ።›› ስትል ትናገራለች።

ትውልድና እድገታቸው ገጠር የሆኑ በተለይም ደግሞ ሴቶች ዲግሪ ይዘው ያልተማረ አግብተው በዝቅተኛ ሥራ የሚተዳደሩ በርካቶች መኖራቸው የሚታወቅ ነው። ከተማ ያደጉ በርካታ ወጣቶችም በሥራ ዕጦት የተሰደዱ፣ ለሱስና ለወንጀል የተዳረጉ እጅግ ብዙ መሆናቸው አይካድም።

በተለይ ደግሞ የብዙ ሥራ ፈላጊዎች መናኽሪያ በሆነችው አዲስ አበባ ከዩኒቨርሲቲ፣ ተመርቀው ጥላ የሚያዞሩ፣ ጥበቃ፣ ጽዳት የሚሠሩና በጥቅሉ ሥራ ያገኙትም ቢሆኑ የተመረቁበትና የሚሠሩት አራምባና ቆቦ የሆነባቸውና ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መመሳቀል የተጋለጡ እልፍ ናቸው።

ለዚህ ኹሉ የትምህርት ስርዓቱም በብዙዎች ተወቃሽ ነው። ክፍል በመቁጠር ከመመረቅ በዘለለ የተመረቁበትን የሙያ መስክ ምንነት ትንሽም የማያውቁ ብዙ ተመራቂዎች ይኖራሉ። ይህ ደግሞ በተግባር ያልታገዘው፣ በጽሑፍና በቃል ብቻ የተመሠረተው ብዙ ጉድለቶች የተሞላው የትምህርት ስርዓትም ተጠያቂ ነው።

ስለሆነም፣ ተመራቂዎችን ከሥራ ፈጣሪነትና ችግር ፈቺነት ይልቅ የሰው እጅ ጠባቂ የሚያደርገው የትምህርት ስርዓት ላይ መፍትሄ እንደሚሆንም ይታመናል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በቅርቡ፣ ባለፉት 11 ወራት ከ2 ሚሊዮን 900 ሺሕ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ ለ2 ሚሊዮን 137 ሺሕ ገደማ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ሲል አስታውቋል። ከተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ውስጥ የሴቶች ድርሻ 35 በመቶ እንደሆነና የወጣቶች ድርሻ 70 በመቶ መሆኑንም ገልጿል።

- ይከተሉን -Social Media

ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 49 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው በገጠር እንዲሁም 50 ነጥብ 3 በመቶ በከተሞች የተፈጠረ ሲሆን፣ በተፈጠረበት ዘርፍ ሲታይ ደግሞ 43 በመቶ በአገልግሎት ዘርፍ፣ 32 በመቶ በግብርና ዘርፍ፣ 22 በመቶ በኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ ሦስት በመቶ ደግሞ በውጪ አገር ሥራ ሥምሪት ነው፤ ብሏል ተቋሙ።

በኢትዮጵያ ያለው ሰፊ የሥራ አጥነት ቁጥር የብዙ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑም፣ በኹሉም ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ፖሊሲዎች እንዲጸድቁና እንዲተገበሩ ማረጋገጥ አስፈላጊ ስለመሆኑ በዚህ ዘርፍ የሚሠሩ አካላት ይገልጻሉ።

የአገሪቱ የትምህርትና ሥልጠና ስርዓትም የሥራ ገበያውን የክህሎትና ሥነምግባር ፍላጎት ያሟሉ ምሩቃንን እንዲያሠለጥን ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ይታመናል።

ለሥራ ፈለጊዎች፣ ለቀጣሪዎችና ለፖሊሲ አውጪዎች የሚያገለግል ጠንካራ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት መገንባትም አስፈላጊና ትልቅ መፍትሄ መሆኑም ይገለጻል።

ከወራት በፊት ጀምሮ እስከ አሁን በአዲስ አደረጃጀት ላይ ነኝ የሚለው ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ወጥ የሆነ ማብራሪያ ለመስጠት እቸገራለሁ ብሏል። የ2014 በጀት ዓመት የሥራ አጥነት ምጣኔ፣ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችም ገና አልተሠሩም ነው ያለው።

በትግራይ ክልል ከነበሩ ዩንቨርሲቲዎች የተዛወሩ ተመራቂዎች
የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ብዙ ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል። በተለይ የመከላከያ ሠራዊት ትግራይ ክልልን ለቆ ሲወጣ እነሱን ይዞ ባለመውጣቱ ቀጣይ ምን ያጋጥማቸው ይሆን የሚለው ትልቅ ስጋት ፈጥሮ ነበር።

ሆኖም ከብዙ ጥረት በኋላ ብዙዎች በሰላም ወጥተው ከአዲግራት፣ መቀሌ፣ አክሱምና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መመደባቸውም የሚዘነጋ አይደለም።

ይሁን እንጂ፣ የቀራቸውን ትምህርት በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተከታትለው የተመረቁ ተማሪዎች ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ ናቸው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አጠቃላይ መረጃ የሚያስቀምጥ ማእከላዊ የመረጃ ቋት ባለመኖሩ የአብዛኛው ሴሚስቴር የውጤት መረጃቸው እዚያው ክልሉ ውስጥ በመቅረቱና እዚህ ማግኘት ባለመቻሉ ተማሪዎችን ለእንግልት ዳርጓል።

- ይከተሉን -Social Media

ሥሟን መጥቀስ ያልፈለገች እና ቀድሞ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስትከታተል የነበረውን የባዮሎጂ ትምህርቷን አጠናቃ ለመመረቅ ወደ አምቦ ዩንቨርሲቲ የተመደበችው ምሩቅ፣ ባለፈው ሰኔ ወር ብንመረቅም፣ ዩንቨርሲቲው ትምህርት ሚኒስቴር ያዘዘውን አልፈጽምም በማለቱ እከ አኳሁን ብቻችንን ቀርተን እየተጉላላን ነው ብላለች።

በዚህም ትምህርት ሚኒስቴር ከትግራይ ክልል ለመጡ ተማሪዎች የአንድ ሴሚስቴር ውጤት ተሠርቶ እንዲሰጣቸው ቢያዝዝም፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ግን ያለፍላጎታችን አዲግራት ዩኒቨርሲተ ሳላችሁ የነበራችሁን የስድስት ሴሚስቴር ውጤት የምትችሉትን ያህል አስታውሳችሁ ሙሉ ብሎናል ትላለች።

ይህን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲው፣ ‹‹ተማሪዎች በሰጡን መረጃ መሠረት›› ብሎ ስለጻፈበት እና ኃላፊነቱን አልወስድም በማለቱ ተማሪዎች በማናስታውሰው ውጤት በኋላ ተጠያቂ አንሆንም በማለት ቅሬታችንን ለትምህርት ሚኒስቴር አቅርበን ነበር ነው ያለችው።

‹‹ትምህርት ሚኒስቴርም ለሥራ ቅጥር መወዳዳሪያ የሚሆን ድጋፍ እሰጣችኋለሁ ካለ በኋላ፣ የምሰጣችሁ ግን ዩኒቨርሲቲው የአንድ ሴሚስቴር ውጤት ከሠራላችሁ ነው ብሎናል። እናም የላክናቸው ተማሪዎች ሄደው ከተመለሱ በኋላ ለድጋፍ ወረቀቱ ፎቶ ላኩ ብለውን ልከናል። እስከ አሁን ግን ያወቅነው ነገር የለም።›› ስትል ነው የተናገረችው።

ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ የእነሱ ዕጣ ፈንታ የገጠማቸው ተማሪዎችም የአንድ ሴሚስቴር ውጤት እና ከትምህርት ሚኒስቴር የድጋፍ ደብዳቤ እንደተሠራለቸው ገልጻ፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ የተለየ አሠራር ለመከተል መሞከሩን ነው ያነሳችው።

በዚህ መልኩ የድጋፍ ወረቀት እና የአንድ ሴሚስቴር ውጤት ቢሰጠንም፣ ግን ቀጣሪዎች እኛን ሊቀበሉ ስለመቻላቸው ስጋት አለኝ ባይ ነች። በመንግሥት ቢታዘዙም ቁጥጥር ስለማይደረግባቸው እኛን በሆነ ሰበብ ማስቀረት ይችላሉ የሚል እምነት አላት።

ለአብነት ብላም ስትጠቅስ፤ ‹‹ከሰሞኑ አንድ የማላስታውሰው ከተማ አስተዳደር፣ ‹ከትግራይ ክልል የመጡ ተመራቂዎችን አናሳትፍም› የሚል ማስታወቂያ በግልጽ ለጥፎ ነበር።›› ስትል ተደምጣለች።

አዲስ ማለዳ ከትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የስልክ ማብራሪያ ለማግኘት ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች