ኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ከአዲስ አበባ ቀጥታ ጅቡቲ የነበረውን የጉዞ መስመር ሊቀይር ነው

0
1229

በሳምንት ኹለት ቀናት ከአዲስ አበባ በመነሳት ጅቡቲ የሚዘልቀውን የባቡር ትራንስፖርት በማስቀረት አዲስ የጉዞ መስመር ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጨረሱን የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ጥላሁን ሳርካ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ዋና ስራ አስኪያጁ እንደተናገሩት ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ እና ከድሬዳዋ ጅቡቲ ያለው የመንገደኞች ቁጥር ተመሳሳይ በመሆኑ ከወጪ አንፃር ስለ ማይመጣጠን አዲሱን የጉዞ መስመር ተግባራዊ ለማድረግ እንደታሰበ አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት በሳምንት ኹለት ቀናት የነበረው ከአዲስ አበባ የሚነሳው እና ጅቡቲ የሚዘልቀው የባቡር መስመርን በየቀኑ በማድረግ መጀመሪያ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ማድረግ ቀጥሎ ሌላ ተቀባይ ባቡር ከድሬዳዋ በመነሳት እስከ ጅቡቲ መዝለቅ እንዲችል መርሃ ግብር ተይዞለታል። ኢንጅነር ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ አንዱ ባቡር ሠላሳ ፉርጎዎች ያሏቸው ሲሆን በአንድ ጊዜ 2ሽሕ መንገደኞችን በተለያየ በሦስት የተለያዩ ማዕረጎች ማጓጓዝ እንደሚችሉ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ አሁን በአማካኝ በየቀኑ አምስት መቶ መንገደኞችን ብቻ እያስተናገደ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልፀዋል።

የ19 ወራት ዕድሜ ያለው ኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር፤ በሳምንት ኹለት ቀናት ከጅቡቲ በመነሳት ወደ አዲስ አበባ በሚያደርገው ጉዞ አዲስ አበባ የሚደርስበት ሰዓት ከምሽቱ 4 ሰዓት አንዳንዴም 6 ሰዓት ድረስ ስለሚቆይ መንገደኞች ላይ ትልቅ የደኅንነት ስጋት እና የትራንስፖርት ችግር እንደሚገጥማቸው ለማወቅ ተችሏል። አዲስ የሚጀመረው መስመር ግን ከድሬዳዋ አዲስ አበባ ስለሚሆን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ የሚደርስ ስለሚሆን በጊዜ መንገደኞች ወደ ቤታቸው መግባት እንደሚችሉም ጥላሁን ሳርካ ተናግረዋል።

በቻይናው የግንባታ ኩባንያ ሲሲኢሲሲ እና ሲአርኢሲ የተገነባው የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር መንገደኞችን ከማጓጓዝ ባለፈም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እና ወጪ ምርቶችንም በማመላለስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here