መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅየቴክኖሎጂን ተቀባይነት አታሳጡ!

የቴክኖሎጂን ተቀባይነት አታሳጡ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ዝርፊያና ሌብነት በወንበዴ እንጂ በባለሥልጣናትና በባለሀብቶች መታየት የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሆነ ይታመናል። የቀደሙት ገዢዎች እጅ መንሻ ሲጠይቁና ሲቀበሉ በአደባባይ እንጂ እንደአሁኖቹ በየቦታው እየተልከሰከሱ እንዳልሆነም ሲነገር ይደመጣል።

ሙስና እየተባለ ጉቦ ይባል የነበረ አስነዋሪ ተግባር የዳቦ ሥም እየወጣለት ሕዝቡ እንዲለማመደውና ተቀባይነት እንዲያገኝም ሲሠራ ቆይቷል። በእንቁላሉ ጊዜ ያልተቀጡ ሹመኞች፣ ስንሻር ይቆጨናል ብለው ሊሰውሩ የሚችሉትን መርከብና አውሮፕላን ሰረቁ መባሉ ሳያንስ፣ አሁን አሁን ሊሰወር የማይችል ሕንፃና ቤት በጠራራ ፀሐይ ሲዘርፉ እየተመለከትን እንገኛለን።

አዲስ ማለዳ እንዲህ ዓይነት የሕዝብን አመኔታ እስከመጨረሻው መንግሥት በሚባል አካል ላይ እንዲጠፋ የሚያደርግና ወደ ስርዓት-አልበኝነት እንዲያመራ ኅብረተሰቡን የሚገፋፋ ድርጊትን መንግሥት ጥብቅ የሆነ መቀጣጫ ተግባር በመፈፀም ለራሱ ሲል ሊያስተምር እንደሚገባ ታምናለች።

ሹመኞችም ሆኑ ገዢዎቻቸው ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው ለራሳቸውም ሆነ ለዘመዶቻቸው ከድሃ ኅብረተሰብ ላይ መዝረፋቸው አዲስ ባይሆንም፣ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው አወናብደው መዝረፋቸው ግን መዘዙ እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ግልፅ ነው። ቴክኖሎጂን ለመጠቀም እያመነታ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ ገና ምኑም ሳይያዝ በመንግሥት ባለሥልጣናት ለዛውም ዋስትና ሊሆኑ በሚገባቸው አካላት ይህ መደረጉ ኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረው የሥነልቦና ጉዳት እንዲሁም መንግሥት ላይ የሚያስከትለውም መጠነ ሰፊ ችግር ሊጤን ይገባዋል።

የኮንዶሚኒየም እጣ ይወጣልኛል ብሎ መንግሥትን አምኖ ከ17 ዓመት በላይ ሲቆጥብ የኖረ ድሃ ማኅበረሰብ፣ እየተዘረፈም ቢሆን የቀረው ይደርሰኛል ብሎ እየተጠባበቀ ባለበት የሰቀቀን ሕይወት ይህን መሰል የዝርፊያ ዜና መስማቱ ሰቅጣጭ ነው። ከዚህ ቀደም ላልቆጠቡ ባለሥልጣናትና ለካድሬዎች ሲሰጥ እያየ ይህም ያልፋል እያለ ሲጠባበቅ የነበረ ኅብረተሰብ፣ አሁን እንዲህ እድሉ ሲመዘበር ዐይቶ ዝም ብሎ ይጠብቃል ማለት ሞኝነት ነው።

የሕዝብን ትኩረትም ሆነ የአገር ሀብትን እንዲህ ሊያባክንና ሊመዘብር በሚችል ድርጊት ላይ አንድ ግለሰብ ብቻ ታምኖ፣ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ሥራው ለእሱ እንዲሰጥ ሲደረግ ሊታሰብበት በተገባ ነበር። ግለሰቡ እንዴት ተመረጠ? እንዴትስ መራጩንም ሆነ ሂደቱን የሚከታተል የመንግሥትም አካል ይሁን የቆጣቢው ተወካይ እንዲሳተፍ አልተደረገም? የሚሉ ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

በአንድ ሰው ይሁንታ ተመሥርቶ እንደፈለገ ሲደረግ፣ ያለምንም ቁጥጥር እጣ የማውጣት ሂደት ደርሶ ሕዝብ እስከሚሰማው መጠበቁ አስፈላጊነትም ሊታወቅ ይገባል። የሕዝብ ትኩረትን ከሌላ ጉዳይ ወደዚሁ ለመሳብ ነው ብለው የሚናገሩን ሐሳብ በሚያረጋግጥ መልኩ፣ የቴክኖሎጂው ታአማኒነትን የሚያጎድፍ ተግባር ይፋ እስኪወጣ መጠበቁ አጠራጣሪ ያደርገዋል።

ቴክኖሎጂውን ከማበልፀጉ ጀምሮ እስከ እጣ አወጣጡ ሂደት ችግር አለበት የተባለውን የእጣ አወጣጥ ሂደት ተግባራዊ እንዲሆን ያደረጉ በወንጀሉ የተጠረጠሩ ግለሰቦችና ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆን መጠየቅ ያለባቸው፣ መቆጣጠር እያለባቸው ሕዝብ ሰምቶ እስኪያፍር ድረስ የጠበቁ እንዲሁም መንግሥትም እንዲዋረድ ያደረጉና መቆጣጠር የነበረባቸው የከተማው አስተዳደርን ጨምሮ በተዋረድ መጠየቅ እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በማጭበርበር ሂደቱ በቀጥታ የተሳተፉ፤ እጣ አወጣጡ ፍትኃዊ እንዲሆን አድርገው መሥራት የነበረባቸውም ሆኑ የመቆጣጠር ኃላፊነቱ ያለባቸው ግለሰቦችም ሆኑ ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆኑ በየትኛውም መንገድ ንክኪ ያላቸውም ሊጠየቁ ይገባል። ሥማቸው መካተት ሳይገባው እጣው ውስጥ እንዲገባ የተደረጉት 100 ሺሕ ገደማ ሰዎች እንደተሳትፏቸው ሊጠየቁና ቅጣትም ሊጣልባቸው ይገባል።

በሰሞኑ ሂደት የታወቀ ነገር ቢኖር የዝርፊያ አፈፃፀሙ መንገድ ነው። ሥልጣንን ተጠቅሞ መዝረፍ የተሰለቸ አሁንም ያልተወገደ ድርጊት ቢሆንም፣ ይህ ሳይቀረፍ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ በአደባባይ በግላጭ ለመዝረፍ መሞከሩ የማንአለብኝነቱን ደረጃ የሚያመላክት ነው።

ኅብረተሰቡ ከወረቀት ገንዘብ ተላቆ ዘመናዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገዶችን፣ የተለያዩ ሰው ሠራሽ መተግበሪያዎችን ተጠቅሞ እንዲያከናውን በሚቀሰቀስበት በዚህ ዘመን፣ የተገኘው ለውጥ ላይ ውሃ የሚቸልስን የባለሥልጣናትን ተግባር አቅልሎ ማየቱ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው የሚሆነው።

የተለያዩ መንግሥታዊ ክፍያዎች ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ እንዲከፍል በሚነገረው በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ ራሱ መንግሥት ባዘጋጀው ከሰው ንክኪ ነጻ ነው በተባለ ሂደት ይህን ያህል ለማጭበርበር መቻሉን ማሳየት የኅብረተሰቡን አመኔታ ወደኋላ መጎተት እንዳይሆን ሊታሰብበት ይገባል።

ኤ.ቲ.ኤም. ካርድ ለማውጣትና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የራሱንም ሆነ የመንግሥትን ሥራ ለማቅለል እምነት የሌለውን ሕዝብ፣ በቆጠብከው ገንዘብ የምታገኘው እድል በእኛው ሰዎች ተጭበረበረ ማለቱ ለወደፊት እመኑን ለማለት አዳጋች ያደርገዋል። አንዴ የጠፋ ሥምን መልሶ ለማደስ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ፣ “የቻይና እቃ” እየተባለ ቀሽምነቱ ሲሰበክ ስለኖረው የአገሪቱ ምርት አሁን ለማሻሻል ምን ያህል እንዳዳገታት መመልከቱ በቂ ነው።

በስንት ዘመን ልፋት መንግሥትን አምኖ ብሩን ከመቅበር ይልቅ ባንክ የከተተውን ማኅበረሰብ አመኔታ የሚያሳጣ፣ ዘመናዊነትን እንዲጠራጠረው የሚያደርግ እንዲህ ዓይነት አስነዋሪ ወንጀል መፈጸሙ እንዳለ ሆኖ ተጠርጣሪዎችን የመያዙ ተገቢነቱ ባያጠራጥርም፣ ለሕዝብ ይፋ የተደረገው ዝርዝር የወንጀሉ ድርጊት ለኅብረተሰቡ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ይልቅ ጉዳቱ እንዳያመዝን ጊዜ ተወስዶ ሊመከርበት በተገባ ነበር።

“መንግሥታዊ ሿሿ” እየተባለ እየተገለፀ ያለው ይህ ድርጊት ለብዙዎች ሀዘኔታ መንስኤ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለአንዳንዶችም የቀልድ መነሻ መሆኑን በመመልከት ምን ያህል ኅብረተሰቡ ተስፋ እንደቆረጠ አመላካች ነው ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያዊያን ከዚህ የበለጠ ተስፋ የሚቆርጡበት ክስተት ከመደገሙ በፊት መንግሥት ሹመኞቹንም ሆነ የተለያዩ ሂደቶችን በመፈተሽ፣ ኅብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ ተስፋ እንዳይቆርጥና የራሱን ውሳኔ ብቻ እንዳይከተል ሊታሰብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

- ይከተሉን -Social Media

የተቀደደ በርሜልን ሊሞላ የሚሞክር ብቻ ሳይሆን፣ እንደተቀደደ እያወቀም በርሜሉን ያልቀየረ እና እንዳይቀዳ ያላደረገም እኩል ተጠያቂ እንጂ ቀጂው ብቻ ተወቃሽ ሊሆን አይገባም። ሌላ ቀዳዳ በርሜል የተተካ እንደሆነም፣ ሌላ ጤነኛ በርሜል የላቸውም ስለሚያስብል መቅዳቱ ከናካቴው እንዳይቆም ማደስ ብቻ ሳይሆን መያዣውና መቅጃው እንዲሁም መራጩም በሚገባ ሊፈተሽ ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች