ዳሰሳ ዘ ማለዳ ሐሙስ መስከረም 29/2012

0
459

1-የተባበሩት መንግስታት ንግድና ልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ገምግሞ ማጠናቀቁን ገልጿል።ቡድኑ የአገራትን የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ፣የተቋማቱ እንቅስቃሴና አደረጃጀት በመገምገም ላይ ሲሆን እስካሁን በ15 አገራት ላይ ግምገማው አድርጓል።(አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………………..

2 -የኢትዮጵያ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ረቂቅ አዋጅ ተቃውሞ ገጠመው። ረቂቅ አዋጁ የጤና አገልግሎት ወጪ የከበዳቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማገዝ በሚል የተዘጋጀ ሲሆን፤ አዋጁ ያካተተው የገንዘብ አስተዳደር ሂደት ግን በተለይ ከኦሮሚያ ክልል በኩል ከወዲሁ ቅሬታ አስነስቷል። አዋጁ የፌዴራል ሥርዓቱን ታሳቢ አላደረገም የሚል ወቀሳም ቀርቦበታል።(ዶቼ ቬሌ)

……………………………………………………………..

3–በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረዉ 12ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል “ሰንደቅ አላማችን የብዝሀነታችን ድምር ውጤትና የአንድነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 3/2012 እንደሚከበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታዉቋል።(ዋልታ)

……………………………………………………………..

4-በያዝነዉ በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው16 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል።ፕሮጀክቶቹ ከ15 እስከ 40 ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው ታስቦ እየተገነቡ የሚገኙ ሲሆን ከ35 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑት የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡም በመዲናዋ ትራንስፖርት ፍሰት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎ ይጠበቃል።(ፋና ብሮድካሰቲንግ)

……………………………………………………………..

5-በኦሮሚያ ልዩ ዞን ገላን ከተማ በ42 ሚሊዮን ብር የተገባዉ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሺመልስ አብዲሳ እና ሌሎች የፌደራል እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ መስከረም 29/2012 ተመረቋል።ፋብሪካው በኦሮሚያ ግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፌዴሬሽን የተገነባ ሲሆን ለ200 ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የበቆሎ ሰብልን እሴት በመጨመር ወደ ዱቄት በመቀየር በቀን 120 ኩንታል እንደሚያመርት ታዉቋል።(ኢቢሲ)

……………………………………………………………..

6 -የኢትዮጵያ ብሄራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ የደኅንነት አገልግሎት በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ።በአፍሪካ ቀንድ የሽብር እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉትን የአልሸባብና የአይኤስ የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴን ለመግታት ኹለቱ አገራት የጀመሩትን የመረጃ ልውውጥ አጠናክረው በመቀጠል በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን የሽብርተኝነት አደጋ ለመከላከል በጋራ እንደሚሰሩ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።(ዋልታ)

……………………………………………………………..

7-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ኢትዮጵያ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ እያደረገች ያለውን እንቅቃሴ አደነቀ።ከመስከረም 26-30/ 2012 ስዊዘርላንድ ጄኔቭ በመካሄድ ላይ የሚገኘው 70ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምን ለማስፈንና ስደተኞችን ለመርዳት እያደረገች ያለው እንቅቃሴ ውጤታማ መሆኑን አሳውቋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

……………………………………………………………..

8  ለበርካታ ዓመታት እድሳት ሳይደረግላቸው በመቆየታቸው ጉዳት የደረሰባቸው የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና ሰኞ ጥቅምት 3/2012 ይጀምራል። ለጥገናው 36 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ ታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here