መነሻ ገጽዜናየእለት ዜናአሜሪካ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የ55 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ተገለጸ

አሜሪካ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የ55 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ተገለጸ

ሐምሌ 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) አሜሪካ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ በዓለም አቀፉ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት በኩል የ55 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል፡፡

የአሜሪካው ዓለምአቀፍ ተራድዖ ድርጅት፤ ተጨማሪው የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ ወቅታዊውን የምግብ አቅርቦት ችግር ለመቋቋም እና ወደፊት ከምግብ ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ አቅም እንደሚገነባላት አስታውቋል፡፡

ፈንዱ የተገኘው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፈረንጆቹ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በጀርመን በቡድን 7 የመሪዎች ጉባዔ ላይ ቃል በገቡት መሠረት የተፈጸመ ነውም ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በጉባዔው አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምግብ ዕጥረት ቀውስ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች 2 ነጥብ 76 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸው ተገልጿል፡፡

የአሜሪካው ተራድዖ ድርጅት የገንዘብ ድጋፉን ከኹለት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለምግብ እና ውሃ አቅርቦት ችግር ለተጋለጡ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም ቀሪ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለመደገፍ እንደሚያውለው አስታውቋል፡፡

የተራድዖ ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን የውሃ አቅርቦት መሠረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባት፣ ለግብርናው ዘርፍ የብድር አገልግሎት ለማቅረብ እንዲሁም የህብረት ሥራ ማህበራትን ለማጠናከር እና ሥልጠና ለመሥጠት እንደሚያውለውም ተመልክቷል፡፡

የዘር እና የማዳበሪያ ማከፋፈያ ሥርዓት እንደሚዘረጋና አርሶ አደሮች አስፈላጊ የሚሏቸውን የእርሻ መሳሪያዎች እንዲገዙ እና የምግብ ምርት አቅርቦታቸውን እንዲያሳድጉ እንደሚያግዝም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ተራድዖ ድርጅቱ፤ ከ3 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ የግብርና ቢዝነስ ተቋማት እና በድርቁ ለተጎዱ አርብቶ አደሮችን እና የማህበረሰቦች ክፍሎችን ለማቋቋም ድጋፉን እንደሚጠቀምበትም አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በፈንዱ ከ8 ሚሊየን በላይ ሰዎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ በሴፍቲ ኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ተመላክቷል፡፡

የአርብቶ አደሮችን ሕይወት ለመቀየር፣ የብድር አገልግሎት ለማመቻቸት እና ለመሳሰሉት ተግባራት ፈንዱ ጥቅም ላይ እንደሚውልም መገለጹን ኢፍ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡

አሜሪካ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለማሻሻል በልማት እና በሰብዓዊ ሥራዎች 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ ማድረጓም ተነግሯል።

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች