የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት የአፍሪካ ዓለም ዐቀፍ ኦፕሬሽኖች ዳይሬክተር ስቴላ ፉቡራ በኢትዮጵያ ይገኛሉ

0
652

ዕረቡ ሐምሌ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ዱባይን የዓለም ኢኮኖሚ ዋና ማዕከል፣ የኢንቨስትመንት እንብርትና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየሠራ የሚገኘው፤ የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት (DET) የአፍሪካ ዓለም ዐቀፍ ኦፕሬሽኖች ዳይሬክተር ስቴላ ፉቡራ በኢትዮጵያ ይገኛሉ።

ስቴላ በአፍሪካ ውስጥ የዱባይ ቱሪዝም አገልግሎትን እንዲያስተዳድር ኀላፊነት ከተሰጠው “ሪቬክሴል ሊሚትድ” (Rivexcel Limited) ከተሰኘው፤ የናይጄሪያ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቶኒ ፕሪንስዊል ጋር በጋራ በመሆን ነው በኢትዮጵያ የተገኙት።

የዳይሬክተሯ የጉብኝት ዓላማም፤ የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት (DET) የቱሪዝም ዘርፎች ላይ እየሠራ የሚገኘውን ሥራ ለማስተዋወቅና በኢትዮጵያ ባሉ የቱሪዝም አማራጮች ላይ በመወያየት ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እና አጋርነት ለመፍጠር ሲሆን፤ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚገኙ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶች ንግዳቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍ እና ሥልጠና የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው።

የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት፤ በዱባይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የቱሪዝም ሐሳብ ለአፍሪካውያን ቱሪስቶች የማሳየት እንቅሰቃሴን እያደረገ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ስቴላ፤ ናይጄሪያን፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያን፣ ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ዲፓርትመንቱ ትኩረት አድርጎ እየሠራባቸው የሚገኙ ዋነኛ የአፍሪካ አገራት መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ዲፓርትመንቱ፤ በቀጣይ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቱሪዝም ተኮሮ ኹነቶችን በማዘጋጀትና የልምድ ልውውጦችን ዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የአገሪቱን የቱሪዝም ኢኮኖሚ ለማሳደግና ተወዳዳሪነትን ለመጨመር እንደሚሠራም ኀላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል።

ዲፓርትመንቱ በኢትዮጵያ ሊያዘጋጃቸው ካሰባቸው ኹነቶች መካከልም፤ በመስከረም 2015 ሊከናወን የታሰበው የመንገድ ላይ ትዕይንት አንዱ ሲሆን፤ ለቁልፍ የጉዞ አጋሮች፣ ወኪሎችን እና አስጎብኚ ድርጅቶችም በቱሪዝም እድገት ዙሪያ ሥልጠናዎችን ለመስጠት መታቀዱን ከዳይሬክተሯ መገለጫ አዲስ ማለዳ ተረድታለች።

እንዲሁም የዱባይ ቱሪዝም ድረ ገፅ ላይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎችንና የአስጎብኚ ድርጅቶችን መረጃ በመጫን አገሪቷን የማስተዋወቅ ሥራም በዲፓርትመንቱ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በቅርቡም የተለያዩ የአገራችን አርቲስቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎችን ሙሉ ወጪ በመሸፈን በዱባይ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ መዘጋጀቱንም ዳይሬክተሯ ጨምረው አስረድተዋል።

እንዲሁም የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት ለ12 አፍሪካውያን፣ የኢኮኖሚ ክላስ ደርሶ መልስ ቲኬት፣ ለ 5 ቀናት በዱባይ ማረፍያንና ምግብን ጨምሮ ከታዋቂዎቹ 4ቱ ናይጄርያዊያን (‘ዱባይ ገርልስ’) ጋር በመሆን አስደናቂ ጉብኝትን የሚያስገኝ ዕጣ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

የዕድሉ ተሳታፊ ለመሆንም፤ ዕድሜያቸው 30 እና ከዛ በላይ መሆን፣ https://instagram.com/visitdubai.af?igshid=YmMyMTA2M2Y= የሚለውን የኢንስታግራም ገፅ መከተል እንዲሁም በገፁ ‘ዱባይ ገርልስ’ የሚለቋቸው ቪድዮች ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተያየት መስጠት እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

በዚህም በኢንስታግራም በቀጥታ ሥርጭት በሚደረግ ምርጫም፤ ከአጠቃላይ አስተያየቶች ውስጥ የሚመርጡ ሲሆን፤ አሸናፊው አፍሪካ ውስጥ ሕጋዊ ነዋሪ ሆኖ ቢያንስ ከመስከረም 2022 ጀምሮ ለ 6 ወራት የሚያገለግል ሕጋዊ ፓስፖርት ሊኖረው እንደሚገባም ዳይሬክተሯ ለአዲስ ማለዳ ተነግረዋል።

ይህ ዕድል የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት፤ ዱባይን ቁጥር አንድ የንግድ ማዕከል፣ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከሚሠራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑንም ነው ስቴላ የገለፁት።

ስቴላ ፉቡራ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት እና ውይይት አጠናቀው የፊታችን ዓርብ ወደ ዱባይ የሚመለሱ ሲሆን፤ በቀጣይም በጉብኝታቸው ባገኟቸው ግብዓቶች ዙሪያ ከዲፓርትመንቱ ጋር ተወያይተው ለኹነቶቹ ትግበራ ወደ ኢትዮጵያ ዳግመኛ እንደሚመለሱም ታውቋል።

የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት በዱባይ ውስጥ ለሚገኙ ሆቴሎችና ለኹሉም የንግድ ዓይነቶች ፈቃድ እና ምደባ የሚሰጥ፤ የቱሪዝም እና የንግድ ግብይቶች፣ ፌስቲቫሎች እና የችርቻሮ ንግዶችን ጨምሮ የዱባይ ኢንዱስትሪዎችን፣ ላኪዎችን እንዲሁም የዱባይ ኢንቨስትመንት ልማት ኤጀንሲን የሚቆጣጠር፣ ዕቅድ የሚያወጣ እና የሚያለማ ዋና ባለሥልጣን ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here