ከዲላ ቡሌ አስከ ሀሮዋጮ የሚደርስው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሊጀመር ነው

0
686

ከዲላ እስከ ሀሮዋጮ ከተማ 68.2 ኪ.ሜ የሚደርስ የጠጠር መንገድ ወደ አስፋልት ለማሳደግ 64.2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቦ ግንባታ ሊጀመር መሆኑ ታውቋል።

አዲስ ማለዳ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባገኘችው መረጃ መሰረት፣ ለሚገነባው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ከመንግሥት 22.2 ሚሊዮን ዶላር እና ከአረብ ባንክ 20 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን በተጨማሪም ከነዳጅ አምራችና ላኪ ሀገራት ፈንድ በተገኘ 22 ሚሊዮን ዶላር የሚሸፈን ይሆናል። ግንባታውም 68.7 ኪ.ሜ ርዝመትና 7.0 ሜትር ስፋት ይኖረዋል።

በመንገዱ ላይ የነበረውን አስቸጋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት በማሻሻልና ይወስድ የነበረውን ረጅም ቆይታ ጊዜ በማሳጠር በገንዘብ፣ በጊዜ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎችን እንዲቀንስ በማስቻል ለተጠቃሚዎች ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት በማቅረብ እንዲሁም በጌድዮ እና ጉጂ ዞን መካከል የሚኖረውን የንግድ እንቅስቃሴ የተሻለ ለማድረግ ነው ተብሏል።

ለግንባታው የተመደበው ብድርም ከነዳጅ አምራችና ላኪ ሀገራት የተገኘው የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ23 ዓመታት ውሰጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከአረብ ባንክ የተገኘው ብድር ደግሞ የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ27 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

ዲላ ቡሌ ሀሮ ዋጩ ፕሮጀክት በመንገድ ዘርፍ የልማት ፕሮግራም ውስጥ ከተካተቱ የመንገድ ግንባታዎች አንዱ ሲሆን ፕሮጀክቱም በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በኹለት ክልሎች ማለትም በኦሮምያ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ከዲላ በመነሳት ቡሌ ሀሮ ዋጮ የሚደርስ ሲሆን በከተሞቹ መካከል የሚኖረውን የኢኮኖሚ ትስስር በማሻሻል በንግድ እና ሌሎች ሴክተሮች ተጠቃሚ ያደርጋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here